>

በርእሰ ብሔሩ " ባይነቁራኛ ሊጠበቅ ይገባል!”  የተባለለት ኃይሉ ገብረዮሃንስ(ገሞራው) !!! (ቅዱስ ማህሉ)

በርእሰ ብሔሩ ” ባይነቁራኛ ሊጠበቅ ይገባል!”  የተባለለት ኃይሉ ገብረዮሃንስ(ገሞራው) !!!

ቅዱስ ማህሉ
“ፔኪንግ ከተማ በእግር ስንዘዋወር ዝነኛውን “የበረከተ መርገም” ደራሲን ኃይሉ ገብረዮሃንስን ድንገት አገኘነው። ከማርስ ዱብ ያለ ነበር የመሰለን። ከኤምባሲው ሰራተኞች በቀር ሌላ ኢትዮጵያዊ ቻይና ውስጥ እናያለን ብለን በፍፁም አላሰብንም ነበር። ፔኪንግ ዩኒቨርስቲ እንደሚማርና ሁለት ኢትዮጵያዊያን አብረውት እንዳሉ ነገረን። የመንግስቱ ኃይለማሪያም አለቃ ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ “መንግስቱ ስለማይመለከተው ጉዳይ የሚያፍተለትል አደገኛ ሰው ስለሆነ ባይነቁራኛ ሊጠበቅ ይገባል” አሉ እንደተባለው ሲ አይ ኤም ኃይሉ ገብረዮሃንስን አስተሳሰቡ ጠማማና አፍራሽ ስለሆነ የመንግስት እይታ ሊያርፍበት የሚገባው ሰው ነው እንዳለ ሰምተናል።”
 (ምንጭ)ብዙ አየሁ፡የሕይዎት ታሪክና ትዝታ፥1998ዓ/ም፥ገፅ 216[መፅሃፉን የፃፉት በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዋና አዛዥ፥ኋላም የውጭ ንግድ ሚኒስቴር በመጨረሻም በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ታደሰ ገብረኪዳን ናቸው።] ፔኪንግ የአሁኗ ቤጅንግ የድሮ ስሟ ነው።
….የዛሬዋን ቅዳሜ ከኃይሉ ገብረዮሃንስ(ገሞራው) ስራዎች ጋር በማሳለፍ ላይ ሳለሁ ነው ከላይ ከመፅሃፉ የቆነጠርኩት ድንገት ትዝ ያለኝና ለእናንተም ለማካፈል የቻልኩት። ገሞራው ከሃገሩ ውጭ በስደት ሳለም ባዕዳኖች ሳይቀሩ ይከታተሉት ነበር። ምን ያህል ቢፈሩት ይሆን? ይህ ሁሉ ክትትል እና የስደት እንግልት ሳይበግረው በርካታ መፅሃፍትን ለንባብ ማብቃቱ በርግጥ ጥንካሬው የት ድረስ እንደሆነ ያሳያል። ገሞራው ስለ ነጻነት ጽፏል። ስለ ፍትህ ተቀኝቷል። ስለ እኩልነት ተንትኗል። ሰለ ድንቁርና አልቀረው ስለ ስርብትና ስለሁሉም ጽፏል። በጽሁፎቹ ያልዳሰሰው ጉዳይ ምን አለ? ምንም!!  ከዚህ በተጨማሪም ገሞራው ባሳተማቸው ሁሉም ስራዎቹ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ደግነትን/ቸርነትን በተግባር ያሳይዎታል። እንዲህ በማለት “የደራሲነቱን መብት አይንፈገኝ እንጅ መቶ ሽህ ቅጅዎችን ካሳተምሁ በኋላ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር እንደፈለገ ቢያደርግ አለመቃወሜንና በዚሁም ውሳኔዬ መሰረት አሳልፌ መስጠቴን አረጋግጣለሁ።” በርግጥ የኃይሉ ገብረዮሃንስ(ገሞራው) መጽሃፍት በሃገር ቤት እንደልብ አለመገኘታቸው ስራዎቹ ተደራሽ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሳይሆን አልቀርም። በነገራችን ላይ ኃይሉ ገብረዮሃንስ ድንቅ ሰዓሊም ነበር።ስዕሎቹም ቢሆኑ ታዲያ እንደ ቅኔ በሰምና ወርቅ የተዋዙ ናቸው።ለአብነት ያህል ስራዎቹን አቀናብሬ በለጠፍኩት ምስል ላይ ከታች በስተቀኝ በኩል ያለውን ይመልከቱ። እኔም ባለቅኔውን በባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “የብዕር አሟሟት ሌላ” ልሰናበተው።(ምንጭ: እሳት ወይ አበባ፣1966ዓ/ም፣ገጽ 36)
የቃለ-ልሳን ቅመሙ
የባለቅኔ ቀለሙ
ነጠበ እንጅ ፈሰሰ አንበል፤ቢዘነበል እንኳ ደሙ
ሰከነ እንጅ ከሰለ አንበል፤ቢከሰከስ እንኳን አጽሙ
የቃለ-እሳት ነበልባሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።…..” አዎ! እኔም ኃይሉ ‘ሞተ’ አልልም!!
Filed in: Amharic