>
5:13 pm - Thursday April 19, 1100

የኖቤል ሽልማቱ ከሸክም ይልቅ ጌጥ እንዲሆን...!?! (በፍቃዱ ኃይሉ)

የኖቤል ሽልማቱ ከሸክም ይልቅ ጌጥ እንዲሆን…!?!

 

በፍቃዱ ኃይሉ
ኢትዮጵያ በዘመኑ ቋንቋ ስትደመር ስትቀነስ ይኸው ሁለት ዓመት ሊሞላት ነው። ሰሞኑን ብዙ ሰዎች መልሰው የተደመሩበት ሰሞን ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማት ሲቀበሉ ከሞላ ጎደል የነበረው ስሜት ጮቤ የመርገጥ ነበር። ስሜቱ ብሔርተኝነት በጣም የተጫነው ስለሆነ ድጋፉ ዘላቂ ይሁን አይሁን ለመገመት ይቸግራል።

የብዙዎች ደስታ አገራቸው በዓለም ዐቀፍ መድረክ ሥሟ በመልካም ሲነሳ ማየታቸው ነበር። ለዚህ ያበቋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆናቸው የተደሰቱባቸውም አይጠፉም። የሆነ ሆኖ ተቃውሞም አልጠፋም። እዚያው የኖቤል ሽልማቱ የሚካሔድበት ከተማ ላይ የትግራይ ተወላጆች “ትግራይ ትገንናለች” የሚል መፈክር ይዘው ዐቢይን ሲቃወሙ ነበር።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተገባው የሰላም ሥምምነቱ በጣም ምሥጢራዊ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተነግሯል። የተከፈቱት ድንበሮች መዘጋትም አሳሳቢ ነው። ይሁንና ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ ከጦርነት ወዲህ፣ ከሰላም ወዲያ ውጥረት ላይ የከረመው የሁለቱ አገራት ግንኙት ቢያንስ ጦርነት የማያሰጋበት ደረጃ መድረሱ አንድ በጎ እርምጃ ነው። ብዙው ርምጃ ገና ወደ ፊት የሚጠብቅ መሆኑ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያውያን ግን የዐቢይን መሸለም ከውስጣዊ ሰላምም አኳያ ነው ሲመለከቱት የከረሙት። ለመሆኑ ዐቢይ በአገር ውስጥ ሰላም ማስፈን ሆኖላቸዋል? ከሆነስ ወደ ፊት ይዘልቅላቸዋል?

የትግራይ ፀጥታ

በቅርቡ በጉባዔ የፈረሰው ኢሕአዴግ “ለሰላም፣ ለልማት እና ዴሞክራሲ” መቆሙን ይናገር ነበር። ሰላም በድርጅቱ ርዕዮት ቅድሚያ ይሰጠው ስለነበር በሥሙ ልማት እና ዴሞክራሲ ይጨፈለቁለት ነበር፤ ለልማት ዴሞክራሲ ይጨፈለቅ እንደነበረው ማለት ነው። በአገሪቷ ውስጥ ለነበረው ከፍተኛ ጭቆና እና አፈና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰበብ “ሰላምን ማስፈን” የሚል ነበር።

ፖለቲካዊ ሒደቱ በተቀለበሰ ማግስት አገሪቷ ትርምስ ውስጥ የገባች መሰለ፤ ሚሊዮኖች ተፈናቀሉ፣ ግለሰቦች ለደቦ ፍርድ ተጋለጡ፣ ንብረት እዚህም እዚያም ወደመ። ይህንን ሁኔታ “የሰላም ማጣት ነው” ያሉት ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሰላም ማምጣት ያልቻሉ የሰላም ሎሬት ናቸው” እያሉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገር ውስጥ ሰላም ማምጣት አለመቻላቸውን ከሚናገሩት ውስጥ የሕወሓት መሪዎች እና ደጋፊዎች ግንባር ቀደም ናቸው። እንደ ምሳሌ የሚያሳዩትም በሕወሓት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ባለችው ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ፀጥታ ነው። ትግራይ አሁንም “ሰላምን ቅድሚያ እሰጣለሁ” በሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር ሥር ነች። እውነትም ሌሎች ክልሎች ላይ የታየውን የሚያህል መፈናቀል፣ የደቦ ፍርድ እና የንብረት ማውደም ትግራይ ክልል ውስጥ አልታየም። ነገር ግን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ “እውነት የትግራይ ፀጥታ ሰላማዊ ነው?”

ፀጥታ እና ሰላም

ዜጎች ለተቃውሞ መደራጀት የማይችሉበት፣ ሐሳባቸውን በነጻነት የማይገልጹበት፣ ሕዝባዊ የተቃውሞ ስብሰባዎችን ማድረግ የማይችሉበት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት ላይኖር ይችላል። ነገር ግን “ሰላም አለ” ብሎ ማለትም የተሳሳተ ነው።

ኢሕአዴግ፣ በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ኢትዮጵያን የመራበት መንገድ የሚገለጸው በሰላም ሳይሆን በፀጥታ ነው። ፀጥታ ግን ሰላም አይደለም። ሰላም ነው ቢባል እንኳን ዘላቂ አይደለም። ይህንን ለመረዳት በስተመጨረሻ የተነሳው የተቃውሞ ሞገድ እና መንግሥት በኃይል ለማፈን የቀጠፈው ነፍስ ማሳያ ነው።

ትግራይ ክልል አሁን ያለችበት ሁኔታ አንዳንዶች “ቀዳማይ ኢሕአዴግ” የሚሉት፣ ከ2010 ዓ. ም. በፊት የፌዴራል መንግሥቱ ይመራበት የነበረው አገዛዝ ነው። በትግራይ ፀጥታ አለ፤ ሰላም ግን የለም።

አሁን ከትግራይ ውጪ ባሉት ክልሎች ውስጥ ብዙ ግጭቶች አሉ። ዜጎች መንግሥት ለደኅንነታቸው በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ ምክንያት ፍርሃት እየተሰማቸው ነው። ነገር ግን ከሞላ ጎደል ለተቃውሞ መደራጀት ይችላሉ። እዚህ እና እዚያ ገደቦች ቢኖሩም ቅሉ ሃሳባቸውን ከበፊቱ በተሻለ በነጻነት ይገልጻሉ። ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችንም ማድረግ ይችላሉ። እነዚህ ክልሎች ውስጥ ግጭቶች በመስፋፋታቸው እና ስጋቶች በመስፋታቸው ምክንያት “ሰላም የለም” የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረስን ተሳስተናል። ሰላም አለ፤ የሌለው ፀጥታ ነው።

ፀጥታን ከሰላም ጋር ማምታት ትልቅ ፖለቲካዊ ስህተት እንደሆነ ያለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት አስተማሪ ናቸው። ይልቁንም ፀጥታ የታፈኑ ድምፆች መኖር አመላካች ነው። የታፈኑ ድምፆች አንድ ቀን መገንፈላቸው ስለማይቀር ፖለቲካዊ ትርምስ እንደሚያስከትሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይልቁንም አሁን ኢትዮጵያ ላለችባቸው ፈታኝ ሁኔታዎች አስፈላጊው ነገር፣ ትርምስ ማረቅ (chaos management) ነው።

መፍትሔ አንድ፤ ትርምስ ማረቅ

የኢትዮጵያ መሪዎች ፈተና እና ኃላፊነት ፀጥታ ማስፈን አይደለም። በኃይል የሰፈነው ፀጥታ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲከፈት በርካታ ጥያቄዎች በአንዴ እንዲፈነዱ አድርጓል። ለሁሉም መልስ ለመስጠት አቅም በሌለው መንግሥት ፊት፣ በጠንካራ ሲቪል ማኅበራት የማይመሩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች፣ በተደራጀ ሚዲያ የሚመራ ዘገባ በሌለበት ብዙ ጫጫታዎች እና ትርምሶች መወለዳቸው አያስገርምም።

ተስፋ የቆረጡ ዜጎች መንግሥት ሁሉንም ነገር በቀድሞው ዘዴ ፀጥ ለጥ እንዲያደርግ እየመከሩ ነው። አክቲቪስቶች እንዲታሰሩ የሚወተውቱም በዝተዋል። መንግሥትም ለዚህ የደቦ ግፊት መልስ በሚመስል ሁኔታ የፀረ-ጥላቻ አዋጅ እያወጣ ነው። የዚህ ዓይነቱ መፍትሔ ግን ለችግሩ መንሥዔ ወደ ሆነው አፈና መመለስ ነው የሚሆነው። ትክክለኛው እርምጃ ትርምሱን ማረቅ እና ዜጎች በነጻነት ሐሳባቸውን በስብሰባ ወይም በንግግር እንዲገልጹ ማድረግ መቻል ነው።

መፍትሔ ሁለት፤ ግጭት ማስወገድ

ምንም እንኳን ከላይ ከላይ ከላይ ሲመለከቷቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ግጭቶች አንዳንዶቹ የቡድን (communal) ቢመስሉም የሥልጣን ሽሚያ አካል መሆናቸውም የማይካድ ነው። የኢሕአዴግ አባላት መካከል ከፍተኛ የሥልጣን ሽኩቻ አለ። አባል ድርጅቶቹ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት በየክልላቸው ያለውን ብሔርተኛ ከጎናቸው በማሰለፍ ነው። ይህም የዘውግ የሚመስል ግጭት እንዲፈጠር መንሥኤ ሆኗል።

የኢሕአዴግ አባል የሆኑት ድርጅቶችም እያንዳንዳቸው ውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻም አሳልፈዋል። ኢሕአዴግ እንደ አንድ ቡድንም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብቶ ነው የሰነበተው። በእነዚህ ጥልፍልፍ ሁኔታዎች ውስጥ ፖለቲከኞቹ ለድጋፍ የሚያሰልፏቸው ንፁኀን ዜጎች ግጭት ውስጥ ገብተው ወቀሳውን ብዙ ጊዜ እነሱ ሲወስዱ ከርመዋል። ይሁንና ገዢው ፓርቲ ለብዙዎቹ ግጭቶች መንሥኤው የሥልጣን ሽኩቻው መሆኑን አምኖ መከላከል ላይ ማተኮር ይኖርበታል። ዜጎችም ከደኅንነት ሥጋት ወጥተው በነጻነት መኖር አለባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትርምሱን በማረቅ ፀጥታ ማስፈን ሳይሆን ሰላም ማረቅ ከቻሉ እና በፓርቲያቸው ውስጥ ያለውን በግጭት የታገዘ የሥልጣን ሽኩቻ ማስወገድ ከቻሉ የኖቤል ሽልማቱ ሸክም ሳይሆን ጌጥ ይሆንላቸዋል።

Filed in: Amharic