>

¨ታላቁ ንጉሥ ሆይ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በወዳጆችህም በጠላቶችህም ዘንድ ስምህ ህያው ነው!!!¨ (መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ) 

¨ታላቁ ንጉሥ ሆይ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በወዳጆችህም በጠላቶችህም ዘንድ ስምህ ህያው ነው!¨

 

መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ 
እምዬ ምንሊክ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ነገ 106ኛ ዓመታቸው ነው። ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ሞት “ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕመሙ ጸንቶባቸው ነበርና ታህሣሥ 3 ቀን 1906 በዕለተ አርብ ሞቱ፡፡ ወዲያውኑ እንደሞቱ የግቢ ሥራ ቤቶች ልቅሶ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን የልጅ ኢያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር ሠግተው በቶሎ ዝም አሰኙአቸው፡፡ አቤቶ ኢያሱ በዚያ እለት ፍልውሃ በመታጠቢያ ቤታቸው ነበሩ፡፡
የአባታቸውን የአጤ ምኒልክ ሞት በሠሙ ጊዜ ደንግጠው ወደ ቤታቸው ወጡና ተቀመጡ፡፡  ሆኖም አገር እንዳይሸበር በማለት ሐዘናቸውን በይፋ አላሳዩም፡፡ እንዲያውም አንዳች ሐዘን አለመኖሩን ለማስረዳትና ለማሳመን ሲሉ በማግሥቱ ቅዳሜ ወደ ጃንሆይ ሜዳ ወጥተው ከአሽከሮቻቸው ጋር በፈረሰ ጉግሥ ሲጫወቱ ዋሉ፡፡  ይህም ለአገር ፀጥታ ሲባል አማካሪዎች ያቀረቡላቸው ዘዴ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ የአጼ ምኒልክ ሞት ምስጢር ሆኖ ተደበቀ፡፡
የአጼ ምኒልክን አስከሬን አሽከሮቻቸው አምሮ በተሰራ በብረት ሳጥን አድርገው በቤተመንግሥቱ ግቢ ባለችው በሥዕል ቤት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አጠገብ በልዩ ሆኖ በተሠራው ቤት ውስጥ በክብር አስቀመጡት፡፡  ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱና ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ከዚያ ሳይለዩ ዳዊት እየደገሙ ያለቅሱ ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ከተነገረው የልቅሶ ግጥም…..
ንግስት ዘውዲቱ
ቀድሞ የምናውቀው የለመድነው ቀርቶ
እንግዳ ሞት አየሁ ከአባቴ ቤት ገብቶ!
እጅግ ያስገርማል ያስደንቃል ከቶ ፥
ከሁለታችን በቀር የሚያውቀው ሰው ጠፍቶ!
ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሐዘን
ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን!
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ
አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ!
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሰኝ አገሬ
የሁሉ አባት ሞቶ ተጎድተሃል ዛሬ!
ድርቅ ሆኖአል አሉ ዘንድሮ አገራች
ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ!
ያች የሠጡኝ በቅሎ መጣባት ባለቤት
አልገዙም መሠለኝ ሊገለኝ ነው ዕፍረት!
እቴጌ ጣይቱ የተናገሩት የግጥም ቃል…
እምቢልታ ማስነፋት ነጋሪት ማስመታት ነበረ ስራችን
ሰው መሆን አይቀርም ደረሠ ተራችን!
አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ
መከራም እንደሠው ይለመዳል ወይ!
አጼ ምኒልክ ምንም ቢሞቱ በሕይወት አሉ እየተባለና እየተወራ እስከ ሠገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት አመት ከዓሥር ወር የሞታቸው ወሬ ተደበቀ፡፡  ስማቸውም ሕያው ሆኖ በምኒልክ አምላክ እየተባለ እንደ ቀድሞው ህጋዊ ማስተዳደሪያ ሆኖ ኖረ፡፡ አጼ ምኒልክ የተወለዱት በነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በዕለተ ቀዳሚት ነበር፡፡ ስለዚህም በሞቱበት ጊዜ ዕድሜያቸው ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ከሦስት ወር ከሃያ ሁለት ቀን ሆኖ ነበር፡፡
በንጉሥነትና በንጉሠ ነገሥትነት የገዙበትም የመንግሥታቸው ዘመን በድምር 47 ዓመት ከሦስት ወር ነው፡፡”
የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትውስታዬ
 ካየሁትና ከሠማሁት ከ1896-1922
እየሩሳሌም ተስፋው
Filed in: Amharic