>

የአስቸኳይ አስቸኳይ - አስቸኳይ (ከይኄይስ እውነቱ)

የአስቸኳይ አስቸኳይ – አስቸኳይ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በርእሱ የተመለከተው አባባል ሆን ብሎ ትኩረትን ለመሳብ የተመረጠ ሳይሆን በተበላሸው የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ የተለመደና በአገር ላይ የሚፈጸም ፌዝ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህንን ቧልት የቅድሚያ ቅድሚያ ቅድሚያ ሲሉም ይገልጹታል፡፡ በመንግሥት የአስተዳደር መ/ቤት (በሲቪል ሰርቪስ) ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ለሠራ የመንግሥት ሠራተኛ ቃሉ እንግዳ አይመስለኝም፡፡  ነገሩ ላይ ላዩን ሲታይ አስቸኳይና ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት መፈጸም ያለበትን አጣዳፊ ‹ሥራ› ይመለከታል፡፡ አንዳንዴ የጉዳዩ ይዘት አስቸኳይም ሆነ ቅድሚያ የሚሰጠው ላይሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ወሳኙ ነገር የጉዳዩ ክብደት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ትእዛዙ የመጣበት ምንጭ ነው ጉዳዩን ‹የአስቸኳይ አስቸኳይ አስቸኳይ› (አአአ) የሚያደርገው፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት መ/ቤት እንደ አቂሚቲ በበላይ ኃላፊው የሚተላለፍ የራሱ የአአአ ጉዳይ አለው፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ከአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ዋና አስፈጻሚ አካል (አሁን ባለው አገዛዝ ከጠ/ሚ/ጽ/ቤት) የሚወርድ ትእዛዝን ነው፡፡ ይህም አስተያየት አቅራቢ ለማካፈል የሚፈልገው ለሁለት ዐሥርት ገደማ በሲቪል ሰርቪሱ የተለያዩ መ/ቤቶች ባገለገለበት ጊዜና አሁንም በአገልግሎት ላይ ካሉ ወዳጆቹና ትውውቆቹ በዓይኑ ያየውንና የሰማውን ተሐዝቦቱን ነው፡፡ በተጨማሪም በዚህ አስተያየት ውስጥ ሁለት ተያያዥ ጉዳዮችን ባጭሩ ለማየት ይሞከራል፡፡ እነዚህም፣ አርቆ የማሰብና ዘላቂውን የማስተዋል ችግር እና ብሔራዊ ጥቅምን ከማስቀደም ይልቅ ምዕራባውያን ተቋማት ባስቀመጡልን አጀንዳ በሚል እንመለከታቸዋለን፡፡  

1ኛ/ የአስቸኳይ አስቸኳይ አስቸኳይ አባዜ (Urgency Syndrome)

ባንድ ወቅት ከዋነኞቻችን አንዱ የሆኑት ጋሼ መሥፍን በመዓዛ ራዲዮ ላይ ቃለ መጠየቅ ሲደረግላቸው በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ባለሥልጣን ንጉሠ ነገሥቱን አስቆጥቶአቸው በጥፊ ሲመቱት ጥፊው እስከ ታችኛው ሹም በተዋረድ እንደሚተላለፍ የሚገርም ትዝብታቸውን አካፍለውን ነበር፡፡ የአአአ ትእዛዝም በውሸት ሪፐብሊክ ሽፋን ባሉ ዘመናዊዎቹ የኢትዮጵያ‹ነገሥታትም› ዘንድ እንደ ንጉሡ ጥፊ ያለምንም ማንገራገር (ጉዳዩ ለአገር የማይበጅ መሆኑን ወይም በቂ ጊዜ ተወስዶ በጥናትና ምርመር ላይ ተመሥርቶ መታየት እንደሚገባው አእምሮና ኅሊና እያወቀው) እስከ ታችኛው የቢሮክራሲው መዋቅር ይወርዳል፡፡ ተመክሮ ተዘክሮ በጥንቃቄ መታየት ያለበትን አገራዊ አንኳር ጉዳይ አናት ላይ ያለው ‹ነብር› ጉዳዩ ባንድ ወይም በሁለት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቅቆ እንዲቀርብለት ቀጭን ትእዛዝ ሲያስተላልፍ፣ በየደረጃው ያሉ ‹ግስሎች› ደግሞ እንደ ባለአእምሮ ቆም ብለው ከነብሩና ጭፍሮቹ ጋር ከመማከር ይልቅ እነሱም በተራቸው ተገሥለው ትእዛዙን ያወርዳሉ ከቀደመውም ያጠረ የጊዜ ሰለዳ አስቀምጠው፡፡ የአአአ ውጤት በአመዛኙ የሚደመደመው ውሱን አገራዊ ሀብትን በማባከን ይሆናል፡፡ ሥራው በዘመቻ መልክ የሚካሄድ፣ የይድረስ ይድረስና የጊዜ ሰሌዳን ለማሟላት ብቻ ያለመ በመሆኑ መቋጫውም የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ይሆናል፡፡ ይህ ሁናቴ ለዓመታት ሲደጋገም አገራዊ ጥፋቱን አስቡት፡፡ ይህ አሳሳቢ ሕማም የአእምሮ እክል እንጂ ጤነኝነት ሊሆን አይችልም፡፡ 

ጉዳዩን ሾላ በድፍኑ ከማድረግ አንድ የቅርብ ምሳሌ ለማሳያነት ላቅርብ፡፡ የዐቢይ ‹መንግሥት› በፖለቲካውም ሆነ ማኅበረ ኢኮኖሚያው ዘርፍ አገራችን የምትጓዝበትን ፍኖተ ካርታ ሳያስቀምጥ፣ በተለይም የምናራምደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን እንደሆነ በውል ሳይታወቅ (በስም ‹የለውጥ መንግሥት› ነኝ እያለ በተግባር የወያኔ ትግሬን አገዛዝ አሠረ ፍኖት እየተከተለ)፣ በምርጫ የተሰየመ ቋሚ መንግሥትም ሳይኖር፣ የወያኔን የከሸፈ ‹የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ› ይዞ እያንዳንዱ የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤት የዐሥር ዓመታት ብሔራዊ ዕቅድ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ቀጭን ትእዛዝ የሰጠበትንና በተዋረድ ቢሮክራሲው ላገር በማይጠቅም የሱሪ ባንገት የግብር ይውጣ ሥራ ተጠምዶ መሰንበቱን አስተውለናል፡፡ በዚህ የአአአ አጀንዳ ምክንያት ቢሮክራሲው እጁ ላይ ያለ ሥራ እንዲቆም ተደርጎ ያለአንዳች ጥናት አምጣችሁ ውለዱ ማለት ምን ዓላማን እንደሚያገለግል ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሩጫውና ሽሚያው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ እውነቱን ለመናገር በተለይም በዘመነ ወያኔ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ በአብዛኛው የአእምሮ ድኩማን ካድሬዎች መፈንጫ ስለነበርና በአዲሶቹም ተረኞች ይኸው ስለቀጠለ፤ ሠራተኛው በአገዛዙና በኑሮም የተማረረ በመሆኑ፤ አብዛኛው የሥራ ጊዜ አሰልቺና ጥቅም በሌላቸው ፖለቲካ ነክ ስብሰባዎች ስለሚያዝ፤ አገዛዙ ከትምህርት የተጣላ በመሆኑ ሠራተኛው ከአድልዖ የፀዳ ተከታታይነትና አግባብነት ያለው የሥራ ላይ ሥልጠናም ሆነ ተጨማሪ ትምህርት ስለማያገኝ፤ የሥራው ጠባይ በአመዛኙ ተራና ለተጨማሪ ንባብና ፈጠራ የማይጋብዝ ከመሆኑ ሌላ አንዳንድ አልፎ አልፎ ጥናትና ምርምር የሚጠይቁ ሥራዎች ሲያጋጥሙ ፍላጎትንና ጥረትን ማትጊያ ዘዴዎች ባለመኖራቸው፤ ለዕድገትና ሹመት ከብቃትና ልምድ ይልቅ የፖለቲካ ታማኝነትና የዘር ቈጠራ ዋና መመዘኛ መሆኑ፤ ከግልገል እስከ አውራ አለቃ ገንቢ ትችትን የማይፈልግ፣ ከድፍረት የሚቆጥር እና ተወያይቶ ከመተማመን ይልቅ አሸማቅቆ ሃሳብ በነፃነት እንዳይንሸራሸር የሚያደርግ በመሆኑ፤ አብዛኛው ሠራተኛው ስንፍናውን ለመሸፈን እንደሚነገርለት በዋናነት አገዛዙን በመቃወም ሳይሆን (አገዛዝን ለመቃወም የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ እናድርግ ሲባል ከጉለሌ ቦሌ በእግሩ ተጉዞ ሥራ ቦታ በማውደልደል ጊዜውን የሚያሳልፈው ቊጥሩ ቀላል እንዳልሆነ በወቅቱ ታዝበናል) ብቃት ባለመኖር፣ ልግምንና ስንፍናን ባህል በማድረጉ በዚህም አእምሮው በመዛጉ ፣ ለኅሊናው ታምኖ ለአገርና ለወገን ከመሥራት ይልቅ አለቃን መጠባበቁ ልማድ በመሆኑ፣ የተሻለ ሃሳብ÷ አዲስ መንገድ ለማሳየት የሚተጋ ሰው ሲገኝ በአድመኝነት ለማግለል መተባበሩ፣ ከውጭ ሲያመ ቈይቶ በሥራ አመራር ስብሰባዎች ላይ የለየለት አድርባይ መሆኑ፣ የተጫነውን ሳይፈትሽና ሳይመረምር እንዳለ ተቀብሎ ለማውረድና ለመተግበር ዝግጁ መሆኑ፤ አገዛዙ ሲቪል ሰርቪሱን በታላቅ ንቀት መመልከቱ (በወያኔ ዘመን የነበረ የንግድና ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባንድ ስብሰባ ላይ ‹የመንግሥት ሠራተኛ ቋንጃው የተሰበረ ባሪያ ነው› ሲል ተደምጧል፡፡) ላገርና ለወገን አገልግሎት በመስጠት የሚገኘውን ክብር ማቃለሉ (ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለዕዳው አይሸከመውም እንዲሉ) ወዘተ. ቢሮክራሲውን ውጤት አልባ አድርጎታል፡፡ ይህ ሲባል ግን ጥቂትም ቢሆኑ ዕውቀት፣ ልምዳቸውንና ጊዜአቸውን በታማኝነትና በቅንነት ላገርና ለወገን የሚያውሉ ትጉህና ታታሪ ሠራተኞች አልነበሩም፣ አሁንም የሉም ማለት አይደለም፡፡ 

የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻል ያለመ ሥራ ለብዙኃን መገናኛ ፍጆታና ለተራ ዝና ሲባል በጥድፊያ ይሠራ እየተባለ አገራዊ ሀብት በከንቱ መባከን የለበትም፡፡ መነቀፍ ያለበት ሥራን ማጓተት እንጂ የሥራው ጠባይ የሚፈልገውን ተገቢ ጊዜ ወስዶ ዘላቂ ውጤት ያለው ተግባር መፈጸም አይደለም፡፡ መቼ ይሆን መንግሥታዊ ሥልጣንን የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻል የምንጠቀምበት?

2ኛ/ የዕለቱን እንጂ ዘለቄታውን ያለማስተዋል ችግር (lacking foresight) እና የምዕራባውያን ተቋማት አጀንዳ ፈጻሚነት

ቢሮክራሲውን በቅርብ የሚከታተል ሰው ጎልቶ የሚታይ አንድ የአሠራር ዘይቤ ያስተውላል፡፡ ይኸውም አመዛኝ ትኩረቱ የእሳት አደጋ የሚመስል ሥራ ላይ ወይም መንግሥት ከአጭር ጊዜ አኳያ ማግኘት የሚፈልገው ውጤት ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዘላቂውን ለጊዜያዊው መሠዋት፡፡ ለዚህም ምሳሌ ላቅርብ፡፡ መንግሥት በዘመቻ መልክ እየካሄድኩ ነው በሚለው የሲቪል ሰርቪሱ ተቋማት የአሠራር እና የሕግ  የማሻሻያ መርሐግብር (‹ሪፎርም›) ነው፡፡ በነገራችን ላይ በወያኔ ዘመን ጥናትና ምርምር ሳይደረግ በደመነፍስ (ለግሉ ዘርፍ ተብለው በውጩ ዓለም ሥራ ላይ የዋሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎች የመንግሥታዊውን ዘርፍ ልዩ ገፅታዎች ግምት ውስጥ አስገብተው ሳይስተካከሉ ( properly customize ሳይደረጉ) ከፍተኛ ሀገራዊ ሀብት ባክኖ ተግባራዊ የተደረገው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መርሐ ግብሮች በክሽፈት መጠናቀቃቸውን አገር እንገዛለን ያሉትና መርሐግብሩን ሲመሩ የነበሩት ባለሥልጣናት በተለያዩ ጠባብ መድረኮች ሲናገሩ ተደምጠዋል (ለብዙኃን መገናኛዎች ፍጆታ የሚነገረው የተለየ ቢሆንም)፡፡ 

‹አዲሱ ሪፎርም› ከሚመለከታቸው መ/ቤቶች አንዱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡ የሚኒስቴሩ መ/ቤት በዋናነት ከተጠመደባቸው ጉዳዮች መካከል ወደ ውጭ የሚላኩ የገበያ ሸቀጦችን (ኤክስፖርትን) በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች የንግድ ሥራን ምቹ ማድረግ (ease of doing business) እና አገራችን የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የሚደረገው ሩጫ ይገኙበታል፡፡ የፊተኞቹ ሁለቱም መርሐግብሮች ባለፉት 25 ዓመታት ተሞክረው ይህ ነው የሚባል ውጤት አላስገኙም፡፡ ባንድ በኩል ወደ ውጭ የሚላኩ የተለመዱ የገበያ ሸቀጦች (traditional commodities) ውሱንነት÷ እሤት ያልጨመሩ መሆናቸውና በዓለም አቀፉ ገበያ የሸቀጦቹ ዋጋ መዋዠቅ፣ በሌላ ወገን አርሶ አደሩ ሕዝባችን በምግብ ራሱን ችሎ ዋስትና የሚያገኝበትን የእህል ምርቶች ከማምረት ይልቅ መላ ትኩረቱን ወደ ውጭ በሚላኩ የገበያ ሰብሎች ወይም በሰፋፊ እርሻዎች /plantations/ ላይ የሚደረግ የሸንኮራ አገዳ እንዲሁም የአበባ ተክል ልማት ላይ ማድረጉ፣ ብሔራዊ ገንዘባችንን ከዶላር ወይም ዩሮ ጋር በማያያዝ በራሳችን ገንዘብ ዕድገትም ሆነ ልማት ሊመጣ እንደማይችል ያለው ሥር የሰደደ የተዛባ አመለካከት የንግድ ፖሊሲያችን በተለይ÷የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ባጠቃላይ ያለበትን የተሳሳተ መስመር የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ 

በአንፃሩም የንግድ ሥራን ማቀላጠፍ ወይም ምቹ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም የቅድሚያ ዓላማው የአገር ውስጥ ባለሀብቱን እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ፈጥሮ ለማበረታታት ሳይሆን የምዕራቡ ካፒታሊዝም ጠበቃ በሆኑት የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ንግድ ድርጅት እንደ መድኃኒት የሚታዘዙትን ብሔራዊ ጥቅምን የማያስጠብቁ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የማስፈጸም ተልእኮ የያዙ ናቸው፡፡ 

የኢኮኖሚ በተለይም የዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚ ባለሙያዎች የብሬተን ውድስ ተቋማት በመባል የሚታወቁት የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (እርጥባንን እና ብድርን መያዣ በማድረግ፣ በማዕቀብም በማስፈራራት) የፖለቲካ ልሂቃኑን በጥቅም በመያዝና ውዥንብር ውስጥ በመክተት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ ለሚገኙ አገራት ላለፉት 50 ዓመታት ድህነትና ችጋርን በቋሚነት የሚያስቀጥሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማዘጋጀት በአገራቱ ለተከሠቱ የኢኮኖሚ ቀውሶች ዋነኛ ተጠያቂ እንደሆኑ በማስረጃ ይገልጻሉ፡፡ አገራቱ በሕዝብ የተመረጠና ተጠያቂነት ያለው መንግሥት አቁመው÷ ዜጎች በነፃነት የሚያሰቡበትንና ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበትን ከባቢ በማመቻቸት፣ ያለ ውጭ ተቋማት ጣልቃ ገብነት ከተጨባጭ ችግራቸው በመነሳት (ልዩ ገጽታቸውን – ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ እሤቶች ወዘተ ግምት ውስጥ በማስገባት) እና ዕውቀትን መሠረት አድርገው፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ የራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ደጋግመው ያሳስባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አገርና ወገንን የሚያስቀድሙ ባለሙያዎች ጠፍተው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች አብዛኛው የአፍሪቃ አገራት የሕዝብን ደም በሚመጡ አምባገነኖች አዙሪት ውስጥ በመውደቃቸው እና የፖለቲካ ልሂቃኑ በጎ ፈቃድና ቁርጠኝነት ታጥቶ እንጂ፡፡ 

ባለፉት 50 ዓመታት የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪቃ አገሮችን የቤተሙከራ አይጥ በማድረግ ያዘዙልን ‹መድኃኒቶች› በሙሉ (the so-called “Import Substitution Industrialization; the Basic Needs Program; the Structural Adjustment Program; Compact Africa”የመሳሰሉት) ዕድገትንና ልማትን ከማምጣት ይልቅ ድህነትንና ሥራ አጥነትን በማባባስ በውድቀት ተደምድመዋል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ብዙዎቹ የአፍሪቃ የፖለቲካ ልሂቃን እነዚህን ፖሊሲዎች ካለመረዳታቸውም በላይ በ‹ኢንቨስትመንት› ስም ከሚመጡ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ጋር በመመሳጠር የየአገራቸውን ሀብት ይዘርፋሉ/ያዘርፋሉ፡፡ ዛሬም የአውሮጳ ኅብረት እና ሌሎች ምዕራባውያን ተቋማት የነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ በስመ እገዛ የፕሮጀክት ገንዘብ መድበው የንግድና ኢንዱስትሪ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ወዘተ ባሉ መ/ቤቶች ውስጥ በ‹ሪፎርም› ስም በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች እጃቸውን አስገብተው ይገኛሉ፡፡ ባለሥልጣኖችም ሆኑ ለባለሥልጣኖች ‹አማካሪ› ሆነው የሚመደቡት ‹ኤክስፐርቶች› ብሔራዊ ጥቅማችንን ለምዕራባውያኑ ፍላጎት አስገዝተው ለፕሮጀክቶቹ ከሚመድቡት ዶለር/ዩሮ ተቋዳሽ በመሆን በሥራ ሽፋን የበደሉ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ 

የዚህ አስተያየት አቅራቢ የኢኮኖሚ ባለሙያ አይደለም፡፡ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአኮኖሚ ባለሙያዎች አድማጭ አላገኙም እንጂ ጩኸታቸውን በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች አሰምተዋል፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ዋነኞቻችን በጽሑፍም ሆነ በቃል ምክር ለዓመታት የጮኹት ጩኸት አድማጭ እንዳለገኘ ኹሉ፡፡ እናዳምጣቸውና የሚበጀንን መክረን ዘክረን እንውሰድ ለማለት ነው፡፡ ተከራክረን፣ ተፋጭተን፣ ተመካክረን፣ተደማምጠን በሁለንተናዊ ሕይወታችን የደረሰብንን ቀውስ ማስተካከል ካልቻልን የምዕራባውያኑም ሆነ ሌሎች የዓለም አቀፍ ጉልበተኛ ኃይሎች ባሪያና መጫወቻ ሆነን መቅረታችን አይደለም ትላላችሁ?

Filed in: Amharic