>

ከኖቤል ሽልማቱ በስተጀርባ ያለው ስውር ደባ!!!  (መምህር ታሪኩ አበራ)

ከኖቤል ሽልማቱ በስተጀርባ ያለው ስውር ደባ!!! 

 

መምህር ታሪኩ አበራ
*እውነት እውነቱን እናውራ።  ለመሆኑ የኖቤል ሽልማት የሚያሸልም ሰላም ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ? 
**በዚህች ሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ የስንት ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ደም በየሜዳው ፈሰሰ? ስንቱ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ በዱላ፣በድንጋይና በሜንጫ ተገደለ? የስንት ሰው አስከሬን መሬት ለመሬት ተጎተተ? ስንት ሺህ ሕዝብ ቤቱ በላዩ ላይ ፈርሶበት በየሜዳው ተፈናቅሎ ቀረ? ስንት ቤተ መቅደስ በእሳት ጋየ? ስንት ካህናት በቁማቸው ተቃጥለው ተገደሉ፣ስንት ሕዝበ ክርስቲያን እንደ ከብት በቢላ ታረዱ?**
**በሕይወት ዘመናችን ያላየነውን ዘግናኝ ሞት ያየነው በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ነው።በኢትዮጵያ ታሪክ ሰው ቁልቁል ተሰቅሎ የተገደለው በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ነው።**
**በቡራዩ፣በሰበታ፣በከታ፣በሐረር፣በጅጅጋ፣በናዝሬት፣በዶዶላ፣በባሌ፣በኮፈሌ በሌሎችም ቦታዎች የሴት ልጅ ጡት ተቆርጧል፣የወንድ ልጅ አካል ተሰልቧል፣ሚስት በቧላ ፊት ፣ሴት ልጅ በአባቷ ፊት በጭካኔ ተደፍራለች፣ሕጻናት በገጀራ ሰውነታቸው ተቆራርጧል፣በሽተኛ አረጋውያን በተኙበት ሰውነታቸው ተከታትፏል ይህ ሁሉ ግፍ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎች ለፍርድ ባልቀረቡባት ሀገር ፣የገዳዮችን መሪ የሜንጫ አብዮተኞችን በአደባባይ አቅፎ እየሳመ በልዩ ጥበቃ የሚንከባከብ ጠቅላይ ሚንስትር የሰላም ተሸላሚ መባሉ ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛቹ የሚል የህጻን ልጅ ጨዋታ ነው።**
**ከኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ባልተናነሰ ሁኔታ ዛሬስ በየክልሉ የሥጋትና የስቃይ ኑሮ ሕዝባች እየኖረ አይደለም ወይ?
**አንዳንድ ጭፍን ደጋፊዎችና በሞቀበት ማድመቅ ልማድ የሆነባቸው ወገኖች አብይ አህመድ ግደሉ፣አፈናቅሉ አላለም እሱን አትናገሩት ይላሉ። ለመሆኑ ያፈናቀሉ፣ገዳይና አራጁን መንጋ የሚመሩትን ሰዎች ለፍርድ አቅርቧቸዋል ወይ?ስለ ፍትህና ነጻነት የሚታገሉትን እያሰረ ግልጽ ጦርነት እንገጥማለን እያለ እያሸማቀቀ፣በብሔር ፓለቲካ የሚመስሉት በደም የተጨማለቁ ሰዎችን በነጻነት የሚያስፈነጨው እሱ አይደለም? ለምን ይዋሻል? ለምን በቃላት ሽንገላ ለሚደልለን ሁሉ አጨብጫቢ ሆነን እንቀራለን? እንንቃ!!
የሰላም ተሸላሚ ብለው ነጮች ሊያታልሉን የሚሞክሩት ምን ድብቅ አጀንዳ ከጀርባ ይዘው ነው ?? 
የቀድሞ የኢቢሲ እና የኢሳት ጋዜጠኛ የነበረው፤ አሁን ደግሞ የ360 ሚድያ ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው በኖቤል ሽልማቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቋም ላይ የሰጠው ሐሳብ አስገራሚ ነው፡፡ ምናላቸው እንዲህ አለ፡-
“የኖቤል ሽልማትን አንተ (ሃብታሙ አያሌው) ከሰላም ጋር አያይዘኸዋል፡፡ ነገር ግን አብይ የወሰደው እርምጃ ኤርትራን ያረጋጋልኛል ወይም አብይ ካለ ሰላም ይሆናል ወደሚል የዋህ ድምዳሜ የሚገቡ አይደሉም እነዚህ ምዕራባውያን የሚባሉ ኃይሎች፡፡ እኔ ይሄን ሽልማት የማያይዘው ከዓለም የፖሊሲ ማስፈፀምና በዚች ሀገር ላይ ወደፊት ሊሰሩት ከሚያስቡት ነገር ጋር ነው፡፡
 እንደሚታወሰው እነ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኢህአዴግ አመራር ዘመን ምዕራባውያኑን “ኒዮሊበራሊስት” በሚል ፈርጀው፤ እነሱ የሚሉዋቸውን አላደርግም ብለው Protectionist ሆነው በጣም አስቸግሩዋቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዛ እነ መለስ ወደ ቻይና ነበር ፊታቸውን ያዞሩት፡፡ የቻይናን መሰረተ ልማት፣ የቻይናን ብድር፣ የቻይናን እርዳታ እያመጡ ምክንያቱ ምዕራባውያን በእጅ አዙር ማእድንህን ሊወስዱ ይችላሉ፣ በእጅ አዙር መሰረተ ልማትህን ሊወስድቡህ ይችላሉ፤ በእጅ አዙር ኮንትራት በሚል ሊመጡ ይችላሉ እንጂ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቬስት ያደርጋሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፤ ነገር ግን አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ አስታውሳለሁ እኔ ጋዜጠኛ ሆኜ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዳይሬክተር ከመለስ ዜናዊ ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡ ያኔ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት አስቸኳይ ስብሰባ ብለው ጫና ለመፍጠር አስበው ነበር፡፡ እናም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ ተገናኙ፡፡
 ጋዜጠኞች ልንዘግብ ሄደን ውይይቱን ስንጠበቅ ቆይተን ዳይሬክተሩ ከመለስ ፅ/ቤት ሲወጣ እጅግ ተበሳጭቶ ነበር የወጣው፡፡ ሌላ ጊዜ መለስ እንግዶቹን ካናገረ በኋላ በሩ ድረስ ወጥቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጥ እንዲሁም ይሸኛቸው ነበር፡፡ ያኔ ግን መለስ አልመጣም፡፡ ምናልባት ዋና ዳይሬክተሩን “ውጣልኝ” ሳይለው አይቀርም፡፡ ዳይሬክተሩ ተበሳጭቶ እንደመጣ ለቃለ-መጠይቅ ስንጠይቀው ፍፁም ተበሳጭቶ ፤ ፈቃደኛ ካለመሆኑ እየተከተልን ስናስቸግረው መለስ ዜናዊን ወደ መሳደብ ነው የገባው፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትራችሁ ሰዎችን አይሰማም” በማለት እየተወናጨፈ ነበር የሚናገረው፡፡ ከዛ ትንሽ ተረጋግቶ የነገረን ነገር ምንድነው “ኢኮኖሚያችሁ በፍጥነት እያደገ ነው፤ ስለዚህ ይህን ኢኮኖሚ ካላቀዘቀዛችሁት፤ የተረጨውን ገንዘብ ካልሰበሰባችሁት፤ ልማታችሁን ካልገታችሁ የኑሮ ንረቱ ይጨምርና በዋጋ ግሽበት ትመታላችሁ፡፡
 ስለዚህ ገንዘቡን ወደመሰብሰብ ሂዱ፤ ልማት ማስፋፋቱን አቁሙት፤ በብሄራዊ ባንክ የሚቀመጠውን ገንዘብ ደግሞ ምጣኔውን በማሳደግ አሁን ያለው የገንዘብ ፖሊሲያችሁን ካልቀየራችሁ የዓለም ባንክ ሆነ አይኤምኤፍ ብድር መስጠት እናቆማለን” ነው ያለው፡፡ ሰውየው ይሄን ያለው መለስ “ብድራችሁን ይዛችሁ መጥፋት ትችላላችሁ” ስላለቸው ነበር፤ ምክንያቱ መለስ Protectionist ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በረከት ስምኦን ኒዮሊበራሊስቶችን (እነ ሁዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ) በተደጋጋሚ ሲዘልፋቸው እንደነበር እናውቃለን፡፡
ነገር ግን አብይ አሕመድ ስልጣን እንደያዘ የአይኤምፏ ዳይሬክተር ክሪስቲን ላጋርድ ወድያውኑ ነበር በራ የመጣችው፡፡ እንዴት ስልጣን እንደያዘ፤ ከበስተጀርባ ያለው ታሪክ ብዙ ነገር ሊባል ይችላል፤ ከመላምትና ግምት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብዙ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ይሄ ሰውየ (አብይ) ወደ ስልጣን እንደመጣ ሁሉንም ፖሊሲ፤ የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የሚያነሱትን ፖሊሲ ተቀብሏል፡፡ ቴሌ እንዲሸጥ ወስኗል፤ መብራት ኃይል እንዲሸጥ ወስኗል፤ ግዙፎቹ የስኳር ፋብሪካዎች እንዲሸጡ ወስኗል፤ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደውን የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ በውጭ ሃይሎች ጭምር እንዲያዝ ወስኗል፡፡
መሬት መሸጥ መለወጥንም የሚጨምር ስለሆነው ቀጣይ የሰውየው እርምጃ እሱ ይሆናል፡፡ አንድ መንግስት፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ገንዘብ ወይም ደግሞ One World Order ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አብይ መሪ ተዋናይ ሆኗል፡፡ የነሱ ቤቢ (ህፃን) ሆኗል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ልጃቸውን መሸለም አለባቸው፡፡ የኖቤል ሽልማት ከክብርና ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁላችንም ያስደስተናል፡፡ ሌሎችም ህዝባቸውን ያገለገሉ ቢሸለሙ እንፈነድቃለን፤ ዜጎች ስለሆንን፡፡ አብይ የተሸለመው ከኢትዮጵያ ችግር የተያያዘና ችግሩን በመፍታት ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ በሚመለከት የተበረከተ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ሰው ቢደሰት መልካም ነው፡፡
 የዚህ ሽልማት ምክንያትና ፋይዳ ግን በደምብ ሊመረመር ይገባል፡፡ ይሄ ሽልማት ፖለቲካዊ ይዘት አለው፤ ይሄ ሽልማት ከበስተጀርባ በተሰራ የጥቅም ግንኙነት፤ ከአገር ሽያጭ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ፡፡” ነበር ያለው።
አሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ ሐገራት ፊታቸውን ላለፉት ሁለት አስርት ዐመታት የፖሊሲያቸው ዋና ማጠንጠኛ ከነበረው ”War on terrorism” በማዞር ወደ የታላላቅ ሐይላት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውድድር(Great powers competition) ወይም በሌላ አባባል ወደ “War on China, Russia and Iran” በሙሉ ኃይላቸው ገብተዋል፡፡
እነዚህ ኃይላት በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የቻይና መስፋፋት መግታት ቅድምያ የሰጡት ጉዳይ እንደሆነ የሚታይ ነው፡፡ ይህንን ስራ እንዲሰሩ ኮንትራቱ የወሰዱት ሳውዲ ዓረብያና የተባበሩ የአረብ ኤምሬቶች ናቸው፡፡ ሆኖም በተለይም አሜሪካኖቹ የቤተ-መንግስቱም ቤተኛ ሆነው ሂደቱን ከላይ ሆነው መከታተላቸው አልቀረም፤ ሂደቱን በመምራት፣ በማማከርና በስለላ ስራዎች በስፋት ገብተውበታል፡፡
እነዚሁ ሐይሎች አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቀብድነት የሰላም ሎሬትነት ካባ አልብሰዋቸዋል፤ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ታማኝ ፈረስ እንዲሆኑላቸው እንደማመቻቸት የሚቆጠር ነው፡፡ በዚያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐገር ቤት ለሚፈጽሙት መጥፎ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት (ለምሳሌ በጌዴኦ ላይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል አይነቱ ወንጀል) ባላዩ ለማለፍ ይጠቅመናል ብለው አስበዋል፡፡
ሽልማቱን ተከትሎ ደግሞ ማን መጣ- IMF-ኢኮኖሚውን ለምዕራባውያን ትላልቅ ኮርፖሬቶች ሙሉ ለሙሉ ለመክፈት 3 ቢልዮን ዶላር ብድር ተብሏል፤ በጣም ተገማች(predictable) የሆነ ውሳኔ ነው፤ እዚህ ውስጥ ዋነኞቱ የቀጠናው ተኮናታሪዎቹ ሳውዲና UAEም እንደሚኖሩበት ይገመታል።
ምዕራባውያን ወደ ራሳቸው እሳቤና እምነት አልባ ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው አንዱ ሊበራሊዝም ነው፡፡ይህ ሐሳብ ደግሞ ኦርቶዶክስ ከምትባል ሃይማኖት ጋር አልተስማማላቸው፡፡ያንን ዕቅድ Empowering female በሚል ፌዝ ፌሚኒዝም እንዲቀነቀን አድርገዋል፡፡በዚህ ዐቢይ ለሴቶች ሥልጣን ሰጥቷል በሚል ተሞካሽቷል፡፡ቀጣይ ደግሞ እንደ አንግሊካውያን እኩልነት በሚል ፕሮፖጋንዳ የሴት ጳጳስ ምንትሴ ማለት ይጀምራሉ፡፡በዚሁ በዐቢይ ዘመን ቢሊኒየሩ ቢልጌት መካን ለሆኑ ሴቶች ሕክምና ለመስጠት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር ተፈራርሞ ሥራ ከጀመረ ቆየ፡፡ቀጣይ የማኅጸን ኪራይ በቅርቡ ለመጀመር የታቀደ ነው፡፡ግብረ ሰዶማውያን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ሊያደርጉ ባቀዱ ጊዜ ዐቢይ ጉዳዩን በዝምታ ነው ያለፈው፡፡በአፉ ሌላ ይናገር እንጂ ሰውየው ዝናንና ታይታን ከነፍሱ አብልጦ የሚወድ ስለሆነ ለእሱ ከተመቸው የሚሊዮኖች መጥፋት ደንታው አይደለም፡፡
በእውነቱ ምዕራባውያን ለጊዜውም ቢሆን ጥሩ ፈረስ አግኝተዋል፤ ድሮ ያልሆነላቸውን አሁን ኢትዮጵያን ቅኝ ሊገዟት አሰፍስፈዋል፡፡ እንግዲህ የአብይ ሽልማት በምን ምክንያት እንደተሰጠ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀው ዘንድ  ይህን ብለናል። ላላነበቡትም አጋሯቸው።
Filed in: Amharic