>

የእኛና የብሄርተኞች ልዩነት! (ሙክታሮቪች) 

የእኛና የብሄርተኞች ልዩነት!

ሙክታሮቪች
ኢትዮጵያን የምንል ሰዎች ከኢትዮጵያ የተለየ ጥቅም ስለምናገኝ አይደለም:: ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደታሪኳ ቀና ብላ በአለም ላይ ብትደምቅ ብትበለፅግ ለእኛ የተለየ ድርሻ ይኖረናል ብለን አይደለም። የሁላችንም ጥቅም ጎልቶ ስለሚታየን ነው።
.
ተው አንድ እንሁን፣ ተው ቂም በቀል አንፈልፍል፣ ተዉ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ማንም ኢትዮጵያዊ ያሻው ቦታ ላይ ሠርቶ የማፍራት፣ መርጦ የመኖር ነፃነትና መብቱ ይጠበቅ ማለታችን የእናት የአባት ቦታ፣ ማረፊያ መውደቂያ ስላጣን አይደለም:: አንድ እንሁን አንለያይ ማለት መነሻ የሌለን ወፍዘራሽ ስለሆን አይደለም። የዜግነት ፅንሰሀሳብ የሚመሰረተው በሁሉ እኩልነት ላይ መሆኑ ስለገባን ነው።
.
ኢትዮጵያን ያልን በዚህች ሀገር ከመጎዳት ውጪ ያተረፍነው የለም። ብሔራችንን ያላልን በሀገራችን ተገፍተናል፣ ባይተዋር ሆነናል፣ ተበደልናል፣ ከንቀትና የቀድሞ ስርዓት በደል ተሸካሚ ከመሆን ውጪ ያተረፍነው የለም። ተናቅን እንጂ አልተከበርንም:: አጣን እንጂ አላገኘንም:: መታገሳችን እኛ ጀግንነትና ድፍረቱን አጥተን፣ ብሔሬን ያሉት ስለጀገኑም አይደለም:: ብሄርተኝነት መንገድ የሚመጣውን መዓት መተንበይ ስለቻልን ነው። አለም በብሄርተኝነት የት መቀመቅ እንደገባች፣ ሀገራትን እንዴት እንደፈረሱ ስላጠናን፣ ከአዋቂዎች አንደበት ቁጭ ብለን ስለተማርን፣ በግል ከመጠቀምና ለስልጣንና ክብር ከመስገብገብ የሀገርና የህዝብን ሰላምና ቀጣይነት ስለፈለግን ነው።
.
የሀገር ፍቅር በጥቅም ስለማይመዘን ነው:: ትሥሥራችን እያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ የዘለቀ ስለሆነ ነው:: ሀገር ከመንደር ስለሚሻል ነው:: ሠርተን፣ ለፍተን በላባችን አፍርተን፣ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንኖርባት ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር ነው:: ደስታም ስኬትም፣ ዝናም ክብርም፣ ሀብትም ፍቅርም፣ ትዳርም ጥሪትም፣ ዕምነትም ተስፋም፣ ሰርግም ቀብርም…ሁሉም በሀገር እንደሚያምር ስለገባን ነው:: መስከናችን፣ ዝም ማለታችን ለሀገር የሚበጅ ከሆነ ግዴለም ይሁን ብለን እንጂ እውነት ከኛ ጋ መሆኗን አጥተን አይደለም።
.
የብሄርተኝነት መንገድ ለሰጥቶ መቀበል የማያመች፣ መነጋገር የሌለበት፣ እኛ እና እነሱ በሚል ግጭት ቀስቃሽ ቁርሾ፣ ታሪክን እና የድሮ በደልን እየቆሰቆሱ በቂም ማያያዝን እንደርእዮተአለም የሚጠቀም፣ በፍርሃትና በስጋት ህዝብን እያመሰ ድጋፍ የሚሰበስብ የጥቅመኞች መንገድ ስለሆነ ከጥቅም ሀገርን መርጠን ነው የራቅነው። ደም መፋሰስ ያረጀ ያፈጀ፣ ሗላ ቀር፣ እንስሳዊ ባህሪ ስለሆነ ነው የራቅነው:: መጫረስ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያቀዱልን እና ማዳከም ማልፈስፈስና አቅመቢስ ማድረግ የፕሮጀክታቸው ግብ ስለሆነ ነው ብሄርተኝነትን የምንጠየፈው። የብሄር ፅንፈኝነት አሸናፊ የማይኖርበት ሁላችንንም መቀመቅ ይዞን የሚወርድ የጋራ ውድመት መንገድ ስለሆነ ነው የምንርቀው።
.
ማንም ማንንም ለፍቶ ካቀናው ሀገር፣ ተወልዶ ካደገበት ከተማ፣ ከአባቱ ርስት በዋዛ ሲነቀል ዝም ስለማይል ፣ ማንም በማንም ላይ የበለጠ ጀግና እንዳይደለ፣ ማንም በየትም ቦታ መኖር መክበርና ወልዶ መሳም አለበት ብለን ስለምናምን ነው የብሄር ፖለቲካ የማይጥመን። ይህ ማለት ጨፍላቂነት እንዳልሆነ እናውቃለን። አንድነት የልዩነት ማሰሪያ ብርቱና ወርቃማ ገመድ መሆኑን እናውቃለን። ልዩነት የአንድነት ጌጥ መሆኑን እናውቃለን። ሀገር በአንድነት ላይ ተመስርታ ልዩነታን ማቀፍ እንዳለባት እናምናለን። ከልዩነት መነሳት ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ የባሰ መከፋፈል እንደሚወስደን ስለገባን ነው አንድነትን የምናስቀድመው እንጂ ልዩነት አይኑር ብለን አይደለም።
በሀይማኖትና በጎሳ የሚለያዩን በችግር ጊዜ ከእኛ ጋ እንደማይሆኑ ስለሚገባን ነው የማንፈልጋቸው። የግጭትና ሞት ነጋዴ ስለሆኑ ነው የምንርቃቸው። የሰው ህይወት መጥፋት ስለሚያመን ነወ የማንወዳቸው። በሞት ስለሚያተርፉ ነው የማንከተላቸው።
ኢትዮጵያን እና ህዝቦችዋን የምናስቀድመው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሰው መሆኑ ተከብሮ፣ እኩል ሆኖ፣ በተከበረችና በበለፀገች ሀገር ላይ ብሄሩ፣ ቋንቋውና ታሪኩ እንደሚከበርና እንደሚበለፅግ ስለምንተልም ነው አንድነትን የምንሻው። የስርዓት ችግር ስርዓቱን በማረምና በማዘመን ይታረማል ብለን ስለምናምን ነው ወደ ኋላ ከማየት ወደ ፊት እያየን ነገአችንን በመመካከረ
በእኩልነትና በነፃነት ላይ ሀገር እንገንባ የምንለው። ከትናንት ተምረን ነገን እናሻሽል በማለት ነው የትናንቱን ታሪክ መጥፎ መጥፎውን ብቻ ሳይሆን መልካሙንም እንያዝ የምንለው።
እኛ ይህን ነው የምናስበው። በዚህ እሳቤ ሀገር ያድጋል እንጂ ማንም አይጨፈለቅም። ማንም አይዋረድም። የአለም ሀገራት የሚሄዱበትም መንገድ ይህ ነው።
.
ኢትዮጵያ ከነህዝቦችዋ ከነልዩነቷ ለዘላለም በአንድነቷ ትኑር!!!
Filed in: Amharic