>

የተዛባ አመለካከት (ከይኄይስ እውነቱ)

የተዛባ አመለካከት

ከይኄይስ እውነቱ

 

የዚህ አስተያየት አቅራቢ በራሱ የግል ምክንያት የ‹ፈስ ቡክ› ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ጠቀሜታውን በመካድ ሳይሆን ለአእምሮ ሰላም በማሰብ፡፡ ‹ጨዋ› ጽሑፎችን የሚያስተናግዱ ሌሎች እንደ ድረ ገጾችና የአንዳንድ ጦማርያን ገጾች ያሉ ማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎችን ግን ይጎበኛል፡፡ መልእክታቸውንም አንጥሮ ጠቃሚውን ለመውሰድ ይሞክራል፡፡ በዚህም ስለ አገራችን ፖለቲካ እና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በቀላሉ የማይገመት ግንዛቤዎችንና ቁም ነገሮችን አግኝቷል፡፡ 

ብዙዎቻችን ልምድ ሆኖብን አንዳንዶቻችንም ሆን ብለን (ተደራጅተውም ሆነ ሳይደራጁ ራሳቸውን ‹ፖለቲካ ዐዋቂ› አድርገው እንደሚያስቡት ወገኖች) ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ብለን የምናካፍለው ሃሳብ ወይም የግል አስተያየት ጅምላ ሕዝብን እንደሚወክል አድርገን የማቅረብ አባዜ የተጠናወተን ይመስለኛል፡፡ 

ሰሞኑን ‹የለውጡ ቡድን› እና መሪዎች በተባሉት ለማና ዐቢይ መካከል ስንጥቃት እንደተፈጠረ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህንን ተከትሎም አንደኛው ትክክለኛውንና ቀናውን መንገድ እንደያዘ ሌላኛው እንደተንሸራተተ የሚሰጡ አስተያየቶች አንብቤአለሁ፡፡ በሌላ በኩል ዐቢይ ‹አዋሐድኩት› በሚለው የወያኔ ግምባር (ኢሕአዴግ) እና ድርጅቱን እንደ ሸክላ ጠፍጥፎ ባበጀው ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) መካከል እሰጥ አገባ ከተጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አሁንም ዐቢይን ብቸኛ ‹እውነትም መንገድም› በማድረግ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አጥብቀው ሲሰብኩ ይደመጣሉ፡፡ አምነውበትም ይሁን የተልእኮ ጉዳይ የሚያውቁት ባለቤቶቹ ናቸው፡፡ አገዛዞች በእንደዚህ ዓይነት የሸፍጥ ሥራ የሚያሰማሯቸው ሎሌዎች እንደማያጡ ግን ይገመታል፡፡ እውነት ፍላጎቱና ቅንነቱ ካለ አማራጭ ጠፍቶ ነው? በማዕከልም ሆነ በ‹የመንደሩ› ጉልበተኞች ሠልጥነው እንጂ፡፡ 

ዐቢይ አዋሕዳለሁ የሚለው እኮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው በነውራቸው የገዘፉ አራት ድርጅቶችንና አጋር ተብዬዎችን መሆኑን እንዘነጋለን ልበል? ኹሉም ለወያኔ በባርነት አድረው በየአካባቢያቸው የማይወክሉትን ሕዝብ ሕይወት፣ አካል፣ ነፃነትና ንብረት ያስገበሩ እኩያን መሆናቸውን (ቢያንስ በንግግራችንና በአቋማችን) እንዴት እንደ ተራ ነገር ለማለፍ እንሞክራለን? የወገኖቻችን ደም ጩኸት አይሰማንም? ዛሬስ (በዚህ ወደ ሁለት ዓመት በሚጠጋ ጊዜ) ኢትዮጵያችን በሰላም ውላ አደራ ታውቃለች? ኧረ አስተውሎታችንን ማን ነጠቀን? ከተፈጸመውና እየተፈጸመ ካለው እልቂት፣ በገፍ መፈናቀል፣ አድሎ፣ ዘረኝነት፣ ካልተገባ እስርና የእስረኞች አያያዝ፣ የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠበት የፍርድ ሂደት፣ ሽብርና ወከባ ወዘተ. ዐቢይና አገዛዙ ከደሙ ንጹሕ ናቸው?

‹ለውጥ› የተባለውን እንቅስቃሴ በጀመሩበት ስድስት ወራት በማይሞላ ጊዜ ያሳዩት አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ› እና ‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ› በማለት አገሬውን ያነሆለሉባቸው ንግግሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በእኔ እምነት በነዚህ ሁለት ግለሰቦች መካከል የጎላ ልዩነት አላይም፡፡ ለማ ‹መንገዱን ስቷል› የሚለው ወሬ እውነት ቢሆን እንኳ ዐቢይ የሚጓዝበትን መንገድ ትክክለኛ አያደርገውም፡፡ እነዚህ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ የሚታዩ የገመድ ጉተታዎች በአገራችን ቀጣይ ዕድል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ቢኖራቸውም በእኔ ትሁት እምነት ከየትኛውም ወገን (ከወያኔ ድርጅቶች፣ ከሁሉም የጐሣ ድርጅቶች እንዲሁም በድርጎ መተዳደር ከለመዱ ሐሳውያን ተቃዋሚዎች በሙሉ) ለኢትዮጵያችን የሚጠቅም ውጤት አልጠብቅም፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን ከኋላ ቀር የመንደርተኝነት አመለካከት የፀዳ፣ የሕግ የባላይነት የሚከበርበት፣ የዜጎች ዕኩልነት የሚረጋገጥበት መንግሥተ ሕዝብ የማስፈን ዓላማ አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ አደረጃጀታቸውም አይፈቅድላቸውም፡፡ ሳይወለዱ የጨነገፉ (stillborn) ናቸውና፡፡ እነዚህ በሽኩቻ የተሞሉ እንቅስቃሴዎች የቆሻሻ ፖለቲካችን ዓይነተኛ መገለጫዎች የሆኑት ሸፍጥና ቅጥፈት፣ ጥላቻና መጠላለፍ፣ ከአገርና ከሕዝብ የሚቀድም ቅጥ ያጣ የሥልጣንና የንቅዘት ስግብግብነት፣ ከሁሉም በላይ የዘረኝነት ስሜት የነገሠባቸው እና እንደ ወትሮው ሕዝብን የበዪ ተመልካች  ያደረጉ መሆናቸው ከበቂ በላይ ምልክቶች አሉ፡፡ የዐቢይ አገዛዝም ሆነ ለማይገባ ሥልጣን አሰፍስፈው ያሉ ኃይሎች በሙሉ አእላፋትን ገብረው ሥልጣን ለማግኘትም ሆነ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ የማይሉ ለመሆኑ ከንግግራቸውም ሆነ ከተግባራቸው እየታየ ነው፡፡ 

በአመክንዮ ሕግ መሠረት ለክርክር መሠረት የሆነና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ዓረፍተ ነገር (“Premise”) ከመነሻው እውነትን ካልያዘ የምንደርስበትም ድምዳሜ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ዛሬ ዓይኔን ግምባር ያድርገው የሚሉ ወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች (የዘር ፖለቲካ አራማጆች) ካልሆኑ በቀር ወያኔ በኢትዮጵያ ምድር ያቆመው የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እንደ አገር ለምንገኝበት ምስቅልቅል ቀዳሚውና መሠረታዊ ችግር መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ይህንን ‹ሰነድ› የአገር መተዳደሪያ ያደረገ አገር ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ‹ደዌ› ለሞት የሚያበቃ እንጂ ተራ ጉንፋን አይደለም፡፡ የአንድን አገር ርእሰ ሕግጋት እንደ “Premise” ብንወስደውና ይህም አገር ለገባችበት ማጥ ዋናው ደዌ ስለመሆኑ ባብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ስምምነት ካለ፣ በተለይም ባስከተለው አገራዊ ጥፋት በተግባር ከተረጋገጠ መነሻችን የተሳሳተ “Wrong Premise” ይሆናል፡፡ በተሳሳተ መነሻ ደግሞ ትክክለኛ፣ አልፎ ተርፎም እውነተኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ለዚህ ‹ደዌ› (የወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት›) ፍቱን መድኃኒት ሳይፈለግ ‹መደመር፣ ውሕደት፣ የጐሣ ነፃ አውጪ ድርጅት፣ የዜግነት ፖለቲካ፣ ፌዴራሊስት፣ ኮንፌዴራሊስት፣ ወዘተ.) እያሉ ትርጕም ለማይኖረው (ምናልባትም የከፋ አገራዊ ቀውስ ለሚያስከትል) ምርጫ መሯሯጥ ከንቱ÷ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ከነውረኛዎቹ የወያኔ ድርጅቶችም (ተዋሐዱም/አልተዋሐዱም) ሆነ ለሥልጣን ፍርፋሪ ከቋመጡ ሐሳውያን ተቃዋሚዎች በጎ ነገር የምንጠብቅ ከሆነ እንደ ኅብረተሰብ በጠና ታመናል ማለት ነው፡፡ የጥፋት መካር እንጂ የሽማግሌ መካር የሌለበት ‹መንግሥት›፣ በዕውቀትና በልምድ ያልለዘቡ ‹ጎረምሶች› የሚገዟት አገር መጨረሻዋ ምን ይሆን?

ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እንደማነሳው (ጆሮውን የሚያውስ ቢገኝም/ባይገኝም) አሁንም ረፍዷል ከሚባል በቀር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የወያኔ/ኢሕአዴግን አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ዘግቶ፣ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ የሚያመጣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የሽግግር ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ በዚህም አገራዊ ጉባኤ በቅድሚያ አገራዊ ሰላምና ፀጥታን ማስከበር፤ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ ዕርቅ (በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ድርጅትን እንደ ቡድን፣ አባላቱን እንደ ግለሰብ ይቅር ማለቱን አላውቅም፡፡ እንኳን ተጠያቂው ዐቢይና ደርጅቱ ቀርቶ ማንም በሟቾችና ተበዳዮች ተገብቶ ለአረመኔዎች ይቅርታ የመስጠት መብት የለውም፡፡ ብሔራዊ ዕርቅ ለሚገባቸው ሲፈጸም የራሱ ሥርዓት አለውና) እንዲሁም ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ፍትሕ እንዲሰፍን በማድረግ ወደ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ብሔራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ መሸጋገር ለአገርና ለወገን የሚበጅ መንገድ መሆኑን ከልብ አምንበታለሁ፡፡

Filed in: Amharic