>

የቄሮ ነገር! የእስክንድር ፍረጃ! እና የቄሮ ጠበቆች!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የቄሮ ነገር! የእስክንድር ፍረጃ! እና የቄሮ ጠበቆች!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ሰሞኑን አቶ እስክንድር ነጋ ቄሮ የተሰኘውን የወጣቶች ስብስብ በሁለት ከፍሎ በማስቀመጥ፤ አንደኛው ቡድን የትግል ተልኮውን ካሳካ በኋላ ወደ ቤቱ ገብቶ ለውጥኑ እያገዘ ነው። የቀሩትንም ጥያቄዎችን በሰለጠነ መልኩ እያቀረበ ነው። ሁለተኛው እና በቁጥር አነስተኛ የሆነው የቄሮ ስብስብ ደግሞ ጃዋር እንደፈለገ የሚነዳው እና በመንጋ ሕዝብን እያሸበረ መሆኑን ገልጾ ይህ ቡድን በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ጥያቄ አቅርቧል።
በተቃራኒው ቄሮ ሲተች ወባ እንደነደፈው ሰው የሚያንዘፈዝፋቸው ሰዎች እስክንድርን አውግዘውታል።
+ የእስክንድርን ፍረጃ በተመለከተ!
እስክንድር ቄሮን በአለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ለማስባል የጀመረው እንቅስቃሴ መሬት ላይ ካለ ስጋት እና ከጭንቀት የመነጨ ቢሆንም የትም እንደማይደርስ ከወዲሁ ልነግረው እወዳለሁ። አለም እነማንን ሽብርተኛ ብሎ እንደሚፈርጅ እና መስፈርቶቻቸውንም በቅጡ ከመረመርን የእስክንድር ድካም የትም ፈቅ አይልም። ነገር ግን በዚህ ስም የሚጠራው ቡድን ምን እያደረገ እንደሆነ አለም እንዲያውቅ ማድረግ ግን ይችላል። ለምዕራቡ አለም አለም ሽብር ስጋት የሆነውን ያህል የፖለቲካም መቆመሪያ ነው። ሽብርተኛን በመፍጠርም፣ በመፈረጅም፣ በመዋጋትም እጃቸው ያለበት ብዙዎቹ የምዕራቡ አለም አገራት በዚህ ጉዳይ የየራሳቸው መስፈርቶች አላቸው። እስክንድር እንደ ምሳሌ ከጠቀሳቸው መካከል ኡጋንዳ የሚገኘው lord resistance army የምዕራቡን አለም፤ በተለይም የአሜሪካንን ቀልብ የሳበው መቼ እና ለምን እንደሆነ ለመረመረ ሰው የምዕራቡን አለም ሸፍጥ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
ለማንኛውም ቄሮን በሽብርተኝነት አለም እንዲፈርጀው መጠየቅ ፋይዳ የሌለው እና ተገቢም አለመሆኑ በሁለት ምክንያት ለመግለጽ እወዳለሁ። አንደኛው አጥፊ የሆነው የቄሮ ቡድን ለአለም ስጋት አይደለም። ለአለም ይቅር እና ለጎረቤት አገር ስጋት አይደለም። ስጋትነቱ ከኦሮሚያ ክልል አይዘለም፤ እሱም ኦሮሞ ባልሆኑ እና በተለይም አማራ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው። ስለዚህ እኛ በሰጋነው ልክ አለም የሚሰጋ መስሎ ከተሰማን ስህተት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህ በሕገ ወጥ ሥራ የተሰማራው የቄሮ ክንፍ ከመንግስት አቅም በላይ ነው ብዮ አላምንም። መንግስት ከፈለገ፤ ከምሩ ከፈለገ ይህን ኃይል ከቀረው ሕዝብ ጋር ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሲር ሊያውለው፤ መረቡንም ሊበጣጥስ እና ቡድኑ ከእኩይ እና ሕገ ወጥ ሥራው እንዲታቀብ ማድረግ ይቻላል። ይህን ቡድን ለመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ቁርጠኛ መንግስት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
+ ለቄሮ ጥብቅና የቆማችሁ ሁሉ
አንድ አስነዋሪ ነገር ሲፈጸም ድርጊቱን ሳያጋንኑ እና ሳይቀንሱ ማውገዝ ይገባል። የቄሮ ቡድኖች ለጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ ለአይን የሚከብድ አስነዋሪ የጭካኔ ተግባር ሲፈጽሙ ድምጻችሁን አጥፍታችሁ ዛሬ ቄሮ ሲከሰስ እንዴት የኦሮሞ ወጣት እንዲህ ይባላል ብላችሁ አደባባይ ለጥብቅና የወጣችሁ ሰዎች ህሊና ካላችሁ ልታፍሩ ይገባል። በቄሮ ቡድን አባላት ሰዎች በማጅራታቸው ሲታረዱ፣ አስከሬናቸው ሲቆራረጥ እና በአደባባይ ሲጎተት፣ ቤታቸው ሲቃጠል፣ ቤተ ኃይማኖቶች ሲወድሙ እያያችሁ እንዳላየ ትሆኑና ይህ ቡድን ሲወቀስ እና ሲወገዝ ገሚሶቻችው ነገሩን የዘር ፍረጃ ለማስመሰል፣ ገሚሶቻችሁ ሚዛናዊ ለመምስለ፣ ገሚሶቻችሁ ለእውነተኛ ለውጥ ለታገለው ጨዋ ቄሮ የወገናችሁ መስላችሁ ለጥብቅና አደባባይ መውጣታችሁ እጅግ ያስተዛዝባል።
ለነገሩ እንዲህ ያሉ የማምታታት እና የራሴ የሚሉትን ወገን ጥፋት እና ወንጀል የመሸፋፈን ነገር እየተለመደ መጥቷል። ትላንት ሕውሃትን አሸባሪ ስንል እና ስናወግዝ የትግራይን ሕዝብ እንደጠላን ተደርጎ ይገለጽ ነበር። ዛሬ ደግሞ እንዱሁ በተመሳሳይ እና አንዳንዴም በከፋ ጥፋት ውስጥ ሰዎች ሲወድቁ ስናወግዚ ይችው የዘር ካርድ እየተመዘዘች የኛ ዘር ፎቢያ አለባችሁ እንባላለን። ኢጄቶን ያወገዘ የሲዳማ ጠላት፣ ቄሮን ያወገዘ የኦሮሞ ጠላት፣ ፋኖን ያወገዘ የአማራ ጠላት እየተደረገ ሰዎችን ለማሸማቀቅ እና ዝም ለማስባል የሚደረገው ጥረት አዳዲስ ተሟጋቾችን ያሸማቅቅ ይሆናል እንጂ በሕውሃት ዘመን የለመድነውን ፍረጃ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ብለን እናልፈዋለን።
አዎ መልካም ሲሰራ ስሙ ተጠቅሶ የሚወደስ፤ ክፉም ሲሰራ እንዲሁ ስሙ ተጠርቶ ሊወገዝ ይገባል። የአብይ አስተዳደር “አንዳንድ ወገኖች” እያለ ያስለመዳችሁን የሾርኒ አነጋገር ከእኛ ከመብት ተሟጋቾች እና ከጋዜጠኞች ባትጠብቁ ጥሩ ነው።
እጄ ላይ በቄሮ ቡድን አባላት የተፈጸሙት በርካታ የፎቶ እና የቪዲዮ ስብስቦች አሉ። እነዚህን ምስሎች በማህበራዊ ድህረ ገጾች ማካፈል ተገቢ ነው ብዮ ስለማላምን ለራሴ ይዤ አቆይቻቸዋለሁ። ዛሬ ላይ አንዳንድ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኖች እና የመብት ተሟጋቾች ሳትቀሩ ቄሮ ለምን ተነቀፈ ስትሉ ስለሰማሁ ብቻ አንዱን ተንቀሳቃሽ ምስል ሳልወድ ለማካፈል ተገድጃለሁ። እስኪ ይህን ቪዲዮ ያየ ሰው አፉን ሞልቶ ስለቄሮ ቡድን አባላት ይሞግተኝ። ይህን ቪዲዮ ያየ ሰው ቄሮን የፈለገውን ስም ሰጥቶ ቢሰይመው እና ቢፈርጀው ምን ይፈረድበታል?
አዎ የተወሰኑ የቄሮ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ የአሸባሪነት ተግባር እየፈጸምሙ ነው። ይህን አውግዙ በመጀመሪያ።
Filed in: Amharic