>

ከባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ - ለኢትዬጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ቦርድ ፣

ከባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ!!!
 
ለኢትዬጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ቦርድ  ፣
 
ጉዳዩ :- የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት
 ( ባልደራስ) ሰብሳቢ በሆነው የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ አገዛዙ ለሚወስደው እርምጃ ኢሳት ሐላፊነቱን እንደሚወስድ ስለማሳወቅ!
 
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት (ባልደራስ) ሰብሳቢ የሆነው ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ ከሚኖሩ ኢትዬጵያውያን እና ትውልደ ኢትዬጲያውያን ጋር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በኖቬንበር 24/2019 ዓ•ም• ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው። በውይይቱም ከአገራችን ወቅታዊና አሳሳቢ ሁኔታ እና የቀጣይ የባላደራ ምክርቤቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ጋዜጠኛ እስክንድር ከህዝቡ ጋር ምክክር አድርጓል። የጋራ ውሳኔዎችንም አሳልፏል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ በቨርጂኒያ ሂልተን አሌክሳንድሪያ ያደረገውን ውይይት መሰረት በማድረግ የኢሳት ሳተላይት ቴሌቪዥን “የዲያስፓራ ተቃውሞና ስብሰባ” በሚል ርእስ ሰኞ ቀን “እለታዊ” ፕሮግራም ሰርቷል። በፕሮግራሙም ላይ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ወንድማገኝ ጋሹ የተሳተፉበት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ በእለቱ የተሰራው ዝግጅት የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት የውጭ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴውን እጅግ ያሳዘነ ሆኖ አግኝተነዋል።
የባልደራሱ ምክርቤት ከሰጠን ተልእኮ መካከል ተቋሙን ስም የሚያጐድፉ ተግባራት ተፈጽመው ሲገኙ መከላከል እና ህጋዊ ምላሽ የመስጠት ሃላፊነት ነው። በመሆኑም ኢሳት ከላይ በተጠቀሰው ቀን ያቀረበው ዘገባ እጅግ በጣም አደገኛ እና የሰብሳቢያችንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ባደረግነው ስብሰባ መግባባት ላይ ደርሰናል።
በመሆኑም እነዚህ አደገኛ ሁኔታዎች እና የኢሳት አመራር ቦርድ እንዲወስድልን የሚገቡ እርምጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
፩: ኢሳት የህዝብ ውሳኔን ክዷል፣
በኖቬንበር 24/2019 ዓ•ም•  በሂልተን አሌክሳንድሪያ በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ህዝቡ ከመድረክ የቀረበለትን የመነሻ ሃሳብ ላይ በመወያየት ” በጃዋር መሃመድ የሚመራውንና ራሱን ቄሮ ብሎ የሚጠራው ቡድንና በመንግስት ውስጥ ያሉ ተባባሪዎቹ በኢትዬጵያ ጄኖሳይድ አደጋ ስለጋረጡ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በሽብርተኝነት እንዲፈርጅ እንጠይቃለን” የሚል ውሳኔ በአንድ ድምጽ አስተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ ውሳኔውን ለአለም አቀፍ ተቋማት እና አገሮች እንዲያሳውቅ እና እንዲያስፈጽም በፕሮፌሰር አቻሜለህ ደበላ የሚመራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተሰብሳቢው ህዝብ በጋራ ወስኗል።
ኢሳት ይህ ውሳኔ በተሰጠበት ሰአት በቦታው በመገኘት ዘገባውን ከቀረጹት የሚዲያ ተቋማት አንዱ ነበር። ሳተላይቱን ጨምሮ በሁሉም የሚዲያ አውታሮቹ ማስተላለፉን እርግጠኛ ባንሆንም። ይህም ሆኖ በሰኞው “እለታዊ” ፕሮግራም ላይ ውሳኔው የህዝብ መሆኑ እየታወቀ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እና ወንድማገኝ ጋሹ ውሳኔውን የእስክንድር ነጋ ብቻ አድርገው አቅርበዋል። ይህ የጋዜጠኞቹ አዘጋገብ ቅጥፈት የተሞላበት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ ሂደቱ ላይ አፍራሽ ሚና የሚጫወት ሆኖ አግኝተነዋል።
በመሆኑም ኢሳት የህዝብ ውሳኔን አክብሮ በአስቸኳይ በሳተላይት ጨምሮ በሁሉም የማስተላለፊያ ዘዴዎቹ የኢትዩጵያን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ እና በእለቱ የቀረበውን እለታዊ የተሳሳተ መረጃ የቀረበበት መሆኑን ገልጾ በፍጥንት እንዲያነሳው በማክበር እንጠይቃለን።
፪: ኢሳት በባለአደራ ምክርቤት ሰብሳቢ የቀረበውን ሪፓርት አዛብቶ አቅርቧል።
ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የኢሳት ጋዜጠኞች ‘ የዲያስፓራው ተቃውሞና ስብሰባ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የእለታዊ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ባልአደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ያልተናገረውን ” ተናገረ” በማለት የጅምላ ፍረጃ እንደሰጠ ተደርጐ እንዲቀርብ ተደርጓል። በተለይም ጋዜጠኛ እስክንድር ” ህውሃትን የመጣል ተልእኮውን ከተወጣ በኃላ አብዛኛው ቄሮ(ወጣት) ወደ ቤቱ ገብቶ የቀረው ሽብር እየፈፀመ ያለው በጃዋር መሃመድ የሚመራ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ቄሮ(ወጣት) ነው” ማለቱ እየታወቀ የኢሳት ጋዜጠኞች በተቃራኒው አቅርበዋል። ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን ህዝብን በጅምላ እንደፈረጀ አድርገው አቅርበዋል። ተልእኮው በማይመጥን ጋር በማነፃፀር በጽንፈኝነት ለመፈረጅ ሞክረዋል።
እንደዚህ አይነት የተሳሳተ ዘገባ ማቅረብ ለምን አላማ ታስቦ እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም ውጤቱ ግን ባልደራሱንም ሆነ ሰብሳቢውን ከህዝብ የሚያጣላ ሆኖ አግኝተነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞቹ ያቀረቡት የተሳሳተ መረጃ ለመንግስት እና ፅንፈኛው ሃይል ቅቤ የጠገበ ዱላ የማቀበል ያህል ተሰምቶናል።
በመሆኑም ኢሳት የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤቱንም ሆነ ሰብሳቢ የሆነውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በይፉ ይቅርታ በመጠየቅ ፕሮግራሙን በአስቸኳይ እንዲያነሳ በድጋሚ እንጠይቃለን።
፫: ኢሳት ጉዳዩን የግለሰብ ብቻ ለማስመሰልና የግለሰቦች ፉክክር አድርጐ ለማሳየት ሞክሯል።
ባለፈው እሁድ በቨርጂኒያ የተካሄደውም ሆነ በቀጣይ ሳምንታት በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ባለቤቱም ሆነ ሃላፊነቱ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክርቤት( ባልደራስ) ነው። አዘጋጆቹ ደግሞ የባልደራሱ የውጭ ድጋፍ ኮሚቴ እና የከተማ ቻፕተሮች ናቸው። ይህንንም በተደጋጋሚ በማስታወቂያዎችና ሚዲያዎች ለማሳወቅ ተሞክሯል።
ይህ መሆኑ እየታወቀ ኢሳት በዘገባውም ሆነ በሚያካሂደው ውይይት የግለሰብ ብቻ ለማስመሰልና የግለሰቦች ፉክክር እያደረገ ለማቅረብ ሲሞክር ተመልክተናል። ይሄ አካሄድ በመሰረቱ ትክክል ያልሆነ እና መታረም እንዳለበት የባልደራሱ ድጋፍ ኮሚቴ ለማሳወቅ ይፈልጋል።
በመጨረሻም አዲሱ የኢሳት ቦርድ ያቀረብነውን ቅሬታ በአጭር ጊዜ ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጠን እያሳሰብን ይህ የተሳሳተ ዘገባ የማይታረም ከሆነ በሂልተን አሌክሳንደሪያ ተሰብስቦ ውሳኔ ያሳረፈውን ህዝብ በኢሳት ቨርጂኒያ ቢሮ ተቃውሞ የምንጠራ እና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ሌሎች ተከታታይ ጥሪዎችን እንደምናስተላልፍ ከወዲሁ እንድታውቁት እንፈልጋለን።
     ድል ለዲሞክራሲ!
የአዲስ አበባ ባላደራ ምክርቤት የውጭ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ
ግልባጭ፣
•ለአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት
• በሂልተን አሌክሳንድሪያ ለተሰበሰባችሁ በሙሉ
•ለሁሉም የሚዲያ ተቋማት
Filed in: Amharic