>

ስለ ‹‹ታላቁ ጥቁር›› ያልተነገረው የታላቅነት ገጽ!!! (በኄኖክ ገለታው)

ስለ ‹‹ታላቁ ጥቁር›› ያልተነገረው የታላቅነት ገጽ!!!
በኄኖክ ገለታው 
   ማርከስ ጋርቬይ ሰዎች ያለትናንት ታሪካቸው ቅርንጫፍ አልባ ዛፎች ናቸው ይላል፡፡ ይህን ያልተወሳሰበ የጋርቬይ ዕሳቦት (perception) ገንዘብ ለማድረግ ግን በትናንት ውስጥ በቅጡ ያልተፈተሹ ጎዶሎ የታሪክ ምዕራፎችን መሙላት ሳያሻ አይቀርም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ትንሹም ትልቁም በጥራዝ ነጠቅ የታሪክ ቅንጣት ላይ ጉንጩን ሲያለፋ ለሚውል ወገን ግን ጽንሰ ሃሳቡ እምብዛም ጭንቀት ሲሆን አይታይም፡፡ … ደራሲ ንጉሤ አየለ ይህ የትውልድ ፍካሬ በወጉ የተገለጸላቸው ሰው ናቸው፡፡ ጸሐፊው የዛሬ ማንነታችን ያለ ትናንት ምሉዕ ታሪካችን ጋርቬይ እንዳስቀመጠው ቅርንጫፍ አልባ ዛፍ እንዳያደርገን ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ ለማዘጋጀት  ተፍ ተፍ ከማለታቸው በፊት ‹‹ሙሽራው›› በተሰኘ የአጭር ልቦለድ ስብስብ (ከአብዱ ራሕማት ጋር) ፤ ‹‹ፍካት›› በተባለ የቀልድና የወግ ጥንቅር ፤ የገራዶ ዋሽንትና ጣዝማ ተብለው በተሰየሙ የልጆች መጽሐፍትና የደራሲያን የህይወት ታሪክ ሥራዎቻቸው ከአንባቢን ጋር ተዋውቀዋል፡፡ ዛሬ በስሱ ጥቁምታ ልንሰጥበት የወደድነውን ‹‹ታላቁ ጥቁር›› የተሰኘው መጽሓፋቸውን ለመጨረስ ደራሲ ንጉሤ ከአስር ዓመታት በላይ ወስዶባቸዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች እየተዘዋወሩ ቤተ መዛግብታትን ለማሰስ እና ከጋዜጣ አንስቶ እስከ ተለያዩ መጻሕፍት ድረስ ጥልቅ ፍተሻና ምርምር ለማድረግ ግን አንዳችም ከመንግሥታዊም ሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ አልተደረገላቸውም፡፡ ከኑሯቸውና ከልጆቻቸው ጉርሻ ቀንሰው ‹‹የሚበልጥብኝ የለም›› ባሉት ሥራ ላይ በማዋል ከዚህ ቀደም ማንም ያልዳሰሰውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ የወዳጅነት ታሪክ የተመለከተ ድንቅ መጽሐፍ ‹‹ታላቁ ጥቁር›› በሚል ርዕስ አቅርበውልናል፡፡ መጽሐፉ በ473 ገጾች ተቀንብቦ ፣ በሓያ ምዕራፎችና በአያሌ ማጣቀሻ ዋቢዎች ተሰናስሎ ቀርቧል፡፡
የደራሲው ተነሳስዖቶች 
        ደራሲው ንጉሤ አየለ በመጽሀፋቸው የመጀመርያ ክፍል በኒውዮርክ እና በተመድ የነበራቸው የጉብኝት አጋጣሚ የኋላ ኋላ ይህን መጽሀፍ ለማዘጋጀት መነሻ እንደሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ በነዚህ የጉብኝት አጋጣሚዎች መሃል ወደ አዕምሯቸው የመጡ ሁለት ጉዳዮች ደግሞ ተከታዮቹ ነበሩ፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ከ1892 እስከ 1924 ዓ.ም ድረስ ከመላው ዓለም የመጡ ስደተኞች መቀበያ ስፍራ ሆኖ ያገለገለው የአሜሪካው ኤሊስ ደሴት ነው፡፡ በዚህ ደሴት አልፈው ወደ አሜሪካ ገብተው ከነበሩ የዓለም ዜጎች መካከል ከኢትዮጵያ የመጡ የቦረና ሰዎች መኖራቸው በፎቶ መረጋገጡና ከዚያ በኋላ የደረሱበት አለመታወቁ “ዕጣ ፈንታቸው ምን ሆነ?” የሚል ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል ፤ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ዶ/ር ግርማ የተባሉ ወዳጃቸው የአጼ ኃይለሥላሴ የአሜሪካ ታሪካዊ ጉብኝትን  አስመልክቶ የተሰማቸው ቅሬታ ነው፡፡ ቅሬታው በመጽሐፉ በሚከተለው መልኩ ተቀምጧል፤ ‹‹ንጉሡ…በአሜሪካ ውስጥ ብዙ ቦታ ጎብኝተዋል፡፡ ታላላቅ ሰዎችንና የኢትዮጵያ ወዳጆችንም እያፈላለጉ አግኝተዋል፡፡ ጉብኝታቸው ሁሌም በቁምነገር የተሞላ ሆኖ አንድም ጊዜ ግን የኢትዮጵያ ታላቅ ወዳጅ የሆነውን ሮበርት ስኪነርን ለማግኘት የሞከሩ አይመስለኝም ፤ ይሄ እጅግ ያሳዝነኛል›› ይህ ቅሬታ የደራሲ ንጉሴ አየለ አዕምሮንም በጥያቄ ወጥሮ ‹‹ሮበርት ስኪነር ማነው?›› ወደሚል የተሟላ መልስ ወደሚያሻው ምርምር እንዲገቡ ገፊ ምክንያት ሆኗል፡፡ የኢትዮ-አሜሪካን ታሪካዊ የግንኙነት ምዕራፎች ስር ሰዶ ለመመርመር የቁርጠኝነት ልኩ ላይ ሲደርሱም ዕጣ ፈንታቸው ካልታወቀው የቦረና ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ጉዳይ ይልቅ ሮበርት ስኪነር የተባለ መልዕክተኛ አሜሪካንና ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅ ለማድረግ የሄደበት ርቀት መጽሐፉን ለማዘጋጀት ዋነኛ ዓላማ ሆኖ አረፈ፡፡ ደራሲ ንጉሤ በዚሁ የመጽሐፉ መንደርደርያ ክፍል እንደሚያስቀምጡልን ‹‹ታላቁ ጥቁር›› የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ሥያሜውን በታሪኩ ውስጥ ከተመላለሱ የዘመኑ ባለታሪኮች የጋራ አገላለጽ መጠቀምን ስለመምረጣቸው ጽፈዋል፡፡ በዚህም መነሻነት የዋሽንግተኑ ዶ/ር ሲስል ፍሬንች ዳግማዊ ምኒልክን ‹‹ታላቁ ሰው›› ፣ ‹‹ታላቁ ጥቁር›› ወይም ‹‹ታላቁ የጥቁር ንጉሥ(Great/Greatest Black Man) በማለት በተለያየ ቦታ የገለጸበትን አግባብ ለመጽሐፉ መጠርያ አውለውታል፡፡
*** ***
ይህ ብዙ የተለፋለትና በእጅጉ የተደከመለት ድንቅ መጽሐፍ ሰፊ የውይይት መድረክ የሚሻ ቢሆንም ለጊዜው ግን በውስጡ ከተዳሰሱ አያሌ ይዘቶች መካከል በጥቂቶቹ ላይ ትንሽ ነገር እንበል፤
የኢትዮ-አሜሪካ ያልተሳኩ የወዳጅነት ሙከራዎች
       በኢትዮጵያና በዩኤስ አሜሪካ መካከል ይፋዊ የመንግስት ግኑኝነት ታሪክ በዳግማዊ ምኒልክና በቴዎድሮ ሩዝቬልት የሥልጣን ዘመን በተሳካ ሁኔታ የተጀመረ ይሁን እንጂ ለንግድና ለወዳጅነት የቀረቡ ቀደምት ጥሪዎች ስለመኖራቸውም መጽሐፉ የሚነግረን አያጣም፡፡ ከ1800ዎቹ አጋማሽ የሚጀምረው ይህ የቀደመ የወዳጅነት ሙከራ ታሪክ ከአሜሪካ ታሪክና ዕድሜ አንጻር ይህን መሳይ ኦፊሴላዊ ግኑኝነት ከአፍሪካዊት ሀገር ጋር ለመፍጠር መታሰቡ አስገራሚነት አያጣውም፡፡ ለማንኛውም ግን በ1846 ፣ በ1872 እና በ1900 በተለያዩ ሦስት ዘመናት ተሞክረው ያልተሳኩትን የንግድና ወዳጅነት ጥያቄዎች በተመለከተ መጽሐፉ ብዙ የሚለን ነገር አለው፡፡ በ1846 ዓ.ም ፓልመር የተባለ አሜሪካዊ ለመጀመርያ ጊዜ በዩ ኤስ አሜሪካና በኢትዮጵያ መንግሥታት መሃል ኦፊሴላዊ ግንኙነት እንዲመሰረት ሀሳቡን በዝርዝር ለአሜሪካ መንግሥት በማቅረብ የመጀመርያ ሰው ነው፡፡ ፓልመር ለአሜሪካ መንግሥት ሃሳቡን ያቀረበው 700 ገጽ በፈጀ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ ይህ ጥናት የኢትዮጵያንና የሌሎች አንዳንድ ምስራቃዊ ሀገሮችን የምርትና የንግድ አቅም ፣ እንዲሁም የንግድ ደንባቸውንና ፖሊሲያቸውን የመዘነ ከመሆኑም በላይ የሀገሮቹን ምርት ፣ ባህል ፣ ጂኦግራፊ ፣ ኃይማኖትና ቋንቋዎች ጭምር አብራርቶ የያዘ ነበር፡፡ ይህ የፓልመር ሀሳብ ግን በ1850 ዓ.ም ኢማኑኤል ዊስ በተባለ ሰው አሉታዊ ሪፖርት ሳቢያ መክኖ ሊቀር ችሏል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚቀጥሉት ሃያ ያህል ዓመታት ከሁለቱም ሀገራት በኩል ምንም ወሬ ሳይሰማ ቆይቷል፡፡ ከ22 ዓመታት በኋላ ግን ሃሳቡን አቅራቢ ሆነው የመጡት አጼ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ሀሳቡን ያነሱት ሠራዊታቸውን በመምራት ያገለግላቸው በነበረውና ኋላም መልዕክተኛቸው ባደረጉት እንግሊዛዊ በጄኔራል ኪርክሃም አማካኝነት ለዩናይትድ ስቴት ደብዳቤ እንዲጻፍ በማድረግ ነው፡፡ ኪርክሃም የአጼ ዮሐንስ ወኪል ሆኖ ጥያቄያቸውን ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሴክሬተሪ ቢያደርስም ጥያቄው ባልታወቀ ምክንያት ከዋሽንግተን ምላሽ ሳያገኝ አሁንም ቀርቷል፡፡ ከ28 ዓመታት በኋላ  ሮበርት ስኪነር የተባለ ዲፕሎማት ጉዳዩን እስከሚያነሳው ድረስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዳግም አንዳችም ነገር ሳይነሳ ቆይቷል፡፡ ስኪነር ከጃንዋሪ 1898 ዓ.ም ጀምሮ በማርሴይ ፈረንሳይ የዩኤስ አሜሪካ ቆንሲል ሆኖ የተሸመ ግለሰብ ሲሆን በሜዲትራኒያን ባህር የሚተላለፉ የአሜሪካ ሸቀጦችን ዝውውርና መድረሻ ማርሴይ ላይ ሲያጠና በምስራቅ አፍሪቃ ብቸኛ ነጻ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ከቀልቡ ገባች፡፡ ከኢትዮጵያ የሚመጡ የግብርና ውጤቶች በ3ኛ ወገን አቅራቢዎች ከፍ ባለ ዋጋ ወደ አሜሪካ ሲገቡ ፣ የአሜሪካ የኢንዱስትሪ ውጤቶችም በሌላ ሀገር ነጋዴዎች ዋጋቸው ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ማስተዋሉ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለሦስተኛ ወገን ቀጥተኛ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ የወዳጅነት ጥያቄውን ለማንሳት ምክንያት እንደሆነው ተገልጹዋል፡፡ ስኪነር ከ1900 ጀምሮ በተከታታይ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጋር መጀመር ስላለበት ወዳጅነት ሰፋፊ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ለውጪ ጉዳይ መ/ቤቱ ቢልክም የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ማኪንሊ በጥይት ተመትተው ሩዝቬልት በሥልጣን ላይ እስኪቀመጡ ድረስ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር፡፡
ምኒልክ እና አፍሪካ
         በዚህ ‹‹ታላቁ ጥቁር›› መጽሐፍ ሰፊና አዳዲስ ግንዛቤዎችን የምንጨብጥበት ሌላኛው ጉዳይ የሚያጠነጥነው በወቅቱ በዳግማዊ ምኒልክ እና ጥቁር አፍሪካዊነት ዙርያ በታዋቂ ግለሰቦች ፣ መጽሀፍትና ጋዜጦች ሰፍረው የነበሩት ዘገባዎች ናቸው፡፡ ምኒልክ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ምልክት ተደርገው ይታሰቡ የነበሩ ሰው መሆናቸው ፤ እርሳቸውንም ለማየትና ባለበት ሆኖም መልዕክቱን ለማድረስ የማይጓጓ እንዳልነበር ከተቀመጡት በርካታ አስረጂዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት በኣንዳንድ ወገኖች ምኒልክ ‹‹እኔ ኔግሮ አይደለሁም ፤ኮኬሽያን ነኝ››(I am not a Negro, I am Caucasian) አሉ መባላቸውን ተከትሎ በጥቁርነታቸው ያምናሉ/አያምኑም ወደሚል የሙግት ጥግ ተደርሶ ነበር፡፡ በርግጥ ምኒልክ በ1878 ለንጉሥ ሊዎፖልድ በጻፉት ደብዳቤም ሆነ ከሱዳኑ መሃዲስት መሪ ጋር ለትብብር ሲደራደሩ ጥቁርነታቸውን ማዕከል አድርገው እንደነበር በማሳያዎች ማመሳከር ይቻላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ግን ምኒልክ በዓለም ዙርያ የሚገኙ የጥቁር ሰው ልጆች ሁሉ መብታቸው ተከብሮና እንደሰው የሚገባቸውን ክብር አግኝተው ይኖሩ ዘንድ ትኩረት ሰጥተው ይታገሉ እንደነበር በአስደናቂ ማስረጃዎች በልጽጎ እናገኛለን፡፡ የመጀመርያው አስረጂ የሚወስደን ዊሊያም ኤሊስና ቤኔቶ ሲልቬይን ወደ ተባሉ ሰዎች ነው፡፡ ኤሊስ ከኩባና ሜክሲኳዊያን የተወለደ ጥቁር የኒውዮርክ ሰው ነው፡፡ ስለጥቁሮችና አፍሪካውያን በእጅጉ የሚቆረቆር በመሆኑ ስለኢትዮጵያ ማሰብ የጀመረው ከአድዋ ድል ማግስት ነበር፡፡ ኤሊስ ስለ ኢትዮጵያ ያለው ግንዛቤ እያደገ ሲመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያ በማቋቋም ጥቁሮችንና ራሱንም ለመርዳት ስለሚችልበት ሁኔታ በማሰብ ከምኒልክ ለመገናኘት ይወስናል፡፡ ሌላኛው የሄይቲ ተወላጅ ሲልቬይ ደግሞ ከሀገሩ መንግስት ለዳግማዊ ምኒልክ መልዕክት በመያዝ ያቀና ሰው ነበር፡፡ ሲልቬይ ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዘና ምኒሊክንም ከተገናኘ በኋላ ንጉሡ ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል ያላቸውን ቁርጠኝነትና ጥረት በመረዳቱ ለንደን ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው ‹‹የአፍሪካዊያን ማኅበር›› ፕሬዘደንት እንዲሆኑና የመክፈቻ ንግግርም በቦታው እንዲያደርጉ ጋብዟቸው ንጉሡ ለግብዣው አመስግነው ሲልቬይን ወኪል በማድረግ ሀሳባቸውን በማህበሩ ጉባዔ ላይ ስለመግለጻቸው ተጽፏል፡፡ ይህም ሁነት በወቅቱ የአውሮፓና የአሜሪካ ጋዜጦች ሽፋን ያገኘ ስለመሆኑ ከተቀመጡልን አባሪዎች ለመረዳት እንችላለን፡፡ … ኤሊስ ደግሞ ከምኒልክ ጋር በነበረው ቆይታ ‹‹አወጉኝ›› ያላቸውን ሀሳቦች ሁሉ ለበርካታ ጋዜጦች የገለጸና ሰፊ ሽፋን ያገኘም ሲሆን ንጉሡ ለነጻነትና ለጥቁር ህዝብ ያላቸውን አመለካከትም አጋርቷል፡፡ ከነዚሀም መሀል አንዱ ‹‹እኔ ጎበዞችን አደንቃለሁ ፣ ነገሥታት ሁሉ እንደ ሩዝቬልት ጎበዞች ሊሆኑ ይገባል፡፡… አንድሪው ካርኒጊ ጥቁሮች ትምህርት እንዲያገኙ ስላበረከቱት መልካም ሥራ የሰሙ መሆናቸውን ነገሩኝ ‹እግዚአብሔር እንዲህ ያሉ ጎበዞችን እንዲባርካቸውና እንዲጠብቃቸው እለምነዋለሁ›… ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ ትኖራለች፡፡ በተለይም የነጻነትን ምንነት የምታውቁ እንደናንተ እንደ አሜሪካኖች ያላችሁትን እንቀበላለን›› የሚለው ንግግራቸው በአስደናቂ ሁኔታ ተዘግቧል፡፡
        አጼ ምኒልክ በዚህ ንግግራቸው አንድሪው ካርኒጊ የሚባል ሰው ስም ጠቅሰዋል፡፡ ካርኒጊ በአሜሪካ ምድር የኢንዱስትሪዎች ባለቤት የነበረ ታዋቂ ነጭ ነው፡፡ ግለሰቡ ሰዎች ሁሉ በአሜሪካ ምድር ያለምንም የዘርና የቀለም መድሎ በእኩል እንደ ዜጋ የሚታዩበትን አሰራር ለመዘርጋት በግሉ ብዙ የደከመና በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ነው፡፡ ምኒልክ ስለዚህ ግለሰብ በጎ ተግባራት ከኤሊስ ሲሰሙ አድንቀው ብቻ አላቆሙም፡፡ ዊሊያም ኤሊስ ወደ ሀገሩ ሲመለስ መልዕክታቸውን እንዲያደርስ ደብዳቤ ጽፈውለታል፡፡ ይህም ደብዳቤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተቀምጦ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ደብዳቤቸው ምኒልክ‹‹ሚስተር ኤሊስ ለመላው ህዝብ የሚደርጉትን ለጋስነትና ቸርነትና በቀና መንፈስ አጫወተኝ፡፡ በዩናይትድ ስቴት ለሚኖሩ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን ያደረጉት ስጦታ ፣ከፍ ያለ ስልጣኔን ፣ እውቀትን ፣ የመልካም ምግባር ጸጋንና ግብረገብነትን እንዲያገኙ ፣ ከፍ ባለ ደረጃም እንዲማሩ የሚረዳቸው መሆኑን ስለነገረኝ እኔም በዚሁ በጣም ተደስቼ ላመሰግኖ ወደድሁ፡፡…›› በማለት ለጥቁሮች ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ሮበርት ስኪነር ከልዑካን ቡድኑ ጋር የአሜሪካ መንግስትን ወክሎ አዲስ አበባ ላይ የመጀመርያውን የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ የወዳጅነት አሻራ ሲጥል ምኒልክ ለሩዝቬልት የላኩላቸው ደብዳቤና መልዕክትም አሜሪካና አውሮፓውያን በአፍሪካ ምድር ላይ ስላላቸው የተለያየ አተያይ ያስቀመጠ ነበር፡፡ ‹‹ሌሎች አገሮች ወደ አፍሪካ የሚመጡት ልክ ልጆች ወደ አባታቸው መጥተው ‹አባባ ኑዛዜ ፈጽመህ አንዳች ነገር ትተህልናል?› እንደሚሉት ዓይነት ነው፡፡ … አሜሪካ ብቻ ናት በአፍሪካ መሬት የሌላትና መያዝም የማትፈልግ፡፡ የአሜሪካ ፍላጎቷ መነገድ ፈቃድ ብቻ ነው›› የሚለው ሀሳባቸው ቴዎድሮ ሩዝቬልት ቀደም ብለው ‹‹ለትንሽም ሆነ ለትልቅ አገር ያለን አመለካከት እኩል አክብሮት የተሞላውና በእውነተኛ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፡፡ የሌሎችን መብትና ፍላጎት አክብረን ሀቀኛ ወዳጅነት መመስረት ፍትሓዊና ተገቢ ነው …›› ካሉት ሐሳባቸው ጋር ስምም የሆነና የአጼ ምኒልክ የአስተሳሰብ ልህቀት ማሳያ ተደርጎ የተወሰደ ነው፡፡
ጋዜጦች ስለ አፍሪካዊው ምኒልክ
         ‹‹ታላቁ ጥቁር›› ዳግማዊ ምኒልክን እንደ አዲስ ምናውቃቸው ያህል ስለሀገራቸው ዕድገትና ብልጽግና ፤ ስለሰው ልጆች ሁሉ እኩልነት የነበራቸው የጠራና የማወላዳ አቋም በምዕራቡ ዓለም በነበሩ መገናኛ ብዙሃን በምን ያህል መጠን ሽፋን እናዳገኘ ዝርዝር መረጃ ይሰጠናል፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት፤ አሜሪካዊያን በ1905 ዓ.ም የሚያዘጋጁትን 100ኛውን የሉዙዋና ግዥ መታሰቢያ ትርዒት ላይ የክብር እንግዳ ሆነው እንዲታደሙ ጥቁሩን አፍሪካዊ ንጉሥ በእጅጉ ፈልገው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ገና ሮበርት ስኪነር ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናቱ በፊት አንስቶ ደርሶ እስከተመለሰበት ጊዜ ድረስ በርካታ ጋዜጦች ‹ምኒልክ አሜሪካን ይጎበኛሉ/አይጎበኙም› በሚለው የዜና ቅርቃር ውስጥ ሆነው መላምቶቻቸውን በገላጭ አንቀጽ(Feature Article) ሲያስነብቡ ቆይተዋል፡፡ የግሎብ ዴሞክራት ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ብንመለከት እንዲህ ብሎ እናገኘዋለን ‹‹የስኪነር የኢትዮጵያ ተልዕኮ በከፍተኛ ደረጃ ተሳካ – ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ትርዒቱ ይመጣሉ … ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ በሴንት ሉዊስ ትርዒት ላይ እንዲካፈሉ የቀረበላቸውን ግብዣ ደንቡን በጠበቀ መንገድ ተቀብለውታል፡፡›› ብሩክሊን ኤግል የተባለ ሌላ ጋዜጣ ደግሞ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ውል መሳካቱን መነሻ በማድረግ ‹‹አቢሲኒያ ወደ ላይ (ተስፋ) እያየች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አገራቸው የምታድግበትን ዕቅድ እየገፉበትና በራቸውን ለውጪ ድጋፍ ክፍት እያደረጉ ነው›› በማለት ጽፏል፡፡
          ምኒልክን አስመልክቶ ለቁጥር የሚታክቱ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጦች አያሌ ጉዳዮችን ጽፈዋል፡፡ እዚህ ጋር ቀደም ሲል የጠቀስነው ብሩክሊን የተባለው ጋዜጣ ስኪነርን ዋቢ አድርጎ ስለንጉሠ ነገሥቱ አጠቃላይ ባህሪ የዘገበውን ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ‹‹ንጉሰ ነገሥቱ አጭር ናቸው፡፡ … ፊታቸው ከሞላ ጎደል ሁልጊዜ በፈገግታ ያበራል፡፡ አንዳንዴ ግን ሰዎቻቸውን ሲቆጡ ፣ የሚያስፈራ ገጽታ መፍጠር ይችላሉ፡፡ … ተወዳጅና ብልህ አገላለጽ የተላበሱ ሆነው ከወግ አጥባቂነት እጅግ ለዘብተኛ አዕምሮ ያላቸውና(Most Liberal Minded) ተራማጅ (Progressive) ሰው ናቸው፡፡ ራሳቸውን ለቅንጦት የሰጡ ሰው አይደሉም ፤ ሆኖም የአውሮፓውያን የአኗኗር ዘዴ ይመርጣሉ …›› በማለት ነው፡፡ ምኒልክ ለአሜሪካው ፕሬዘዳንት ከላኩት ደብዳቤ ባሻገር ለሄይቲው ፕሬዘደንት የላኩት ‹‹ባህርና መሬት ሰውን ከሰው ቢያራርቅ ፤ መልካም ሀሳብ ያቀራርባል›› የሚለው መልዕክታቸው ትልቅ ዋጋ ተሰጥቶት የጋዜጦች ማሻሻጫ ሆኖ ነበር፡፡
 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኤልዶራዶ?
         በዚህ መጽሐፍ ሌላኛው ቀልብን የሚስበው ጉዳይ ደግሞ በዘመኑ ኢትዮጵያ ምድራችን ላይ ካልተነኩ ድንግል መሬቶች አንዷ የመሆኗን ጉዳይ በርካታ ጸሀፍትና መገናኛ ብዙኃን ያወሩለት ሆኖ መመዝገቡ ነው፡፡ እንደ ሎንግ ብራንች ኒውስ ያሉ ጋዜጦች የስኪነርን ከኢትዮጵያ መመለስ ተከትሎ ‹‹ንጉሥ ምኒልክ ሰፋ ያለ አዕምሮ ያላቸው መሪ ፣ በፈጣን የዘመናዊ ለውጦቹ አቢሲኒያን የአፍሪካ ጃፓን ሊያደርጋት ነው›› የሚሉና መሰል ዘገባዎች ‹‹ኤልዶራዶ›› ተብላ በወርቅ ተሸፍና ጠፍታለች ተብላ የምትታመነውን ቦታ ከጥንታዊው የሳባ ታሪክና የከበሩ ዕንቁዎቿ መነሻነት ‹‹በርግጥም ኢትዮጵያ ኤልዶራዶ ትሆን?›› በሚል ስሌት በርካቶች ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ለቁፋሮ ይመጡ እንደነበር ሰፍሯል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የመጡትን ልዩ ልዩ የወርቅ ቁፋሮ ኩባንያዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ፍቃዳቸውን ሰጥተው በማሰማራት ለህልማቸው/ሀሳባቸው ስሙርነት ወይም ክሽፈት የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ እዚህ ጋር በመጽሐፉ ሰፍሮ የምናገኘውና እጅግ አትኩሮታችንን የሚስበው ጉዳይ ግን ምኒልክ ከኩባንያ ባለቤቶቹ ጋር ያደርጉ የነበረው ውልና ዝርዝር ስምምነት ነው፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ ለጥናት ካያቸው ሐያ ያህል የፍለጋ ፍቃድ ደብዳቤዎች በሁሉም ዘንድ የማይቀሩ አምስት ነጥቦች መኖራቸውን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህን ነጥቦች በጥቅሉ ለማየት ያህል ፤ የመጀመርው የፍለጋው ጊዜ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ የፍለጋው ቦታ በምልክቶች የተከለለና ከተሰጠው ቦታ ውጭ መውጣት የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው ነጥብ ፈቃዱ የተሰጠው ለአንድ ኩባንያ እንደመሆኑ መጠኑ ዕድሉን ለሌላ በገዛ ፍቃዱ የመስጠት መብት በፍጹም እንደሌለው የሚደነግግ ነው፡፡ በአራተኝነት የምናገኘው ፈቃድ የተሰጠው ወገን ማንኛውም ዓይነት ማዕድን ማውጣቱ ከተሳካለት ከመንግሥት ጋር አዲስ ውል ሳይዋዋል ማዕድኑን ማውጣትም ሆነ መውሰድ አለመቻሉን ነው፡፡ የመጨረሻው ነጥብ በበኩሉ ማዕድን ፈላጊው ቡድን ከአካባቢው ሹም/ተወካይ ተመድቦለት ፍለጋ ሚያከናውን ስለመሆኑ  የሚገልጽ ነው፡፡ በነዚህ የወል ስምምነቶች መሰረት ስምንት ያህል ኩባንያዎች ፍቃድ ተሰጥቷቸው እንደነበር መጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡
መውጫ
‹‹ታላቁ ጥቁር›› የተሰኘው መጽሐፍን በአጭር መዳሰስም ሆነ በቀላሉ አውርቶ መጨረስ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለበርካታ ተጨማሪ ጥናቶችና ምርምሮች ግን በር ከፋች የሆኑ ምንጮችና አባሪዎች በበቂ ሁኔታ ተቀምጠውለታል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ማንበብ ታሪክን እንደ አዲስ ምልዓትነቱን በጠበቀ መልኩ መማር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትናንት የነበራትን ቦታ(ግምት) እና አጼ ምኒልክ የተሰጣቸውን ሰፊ ዋጋ የዘመኑን ማስረጃዎች ብቻ ዋቢ ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡ ደራሲ ንጉሤ በበጎ ፍላጎትና ቅንነት ስሜት ተነሳስተው ለህዝባቸው ያበረከቱት ይህ ዳጎስ ያለ ሥራ ከማይነጥፉት የሀገር ባለውለታዎች ተርታ ያሰልፋቸዋል ባይ ነን፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያን ያለ ሁሉ ገዝቶ ያነበው ዘንድ ምክረ ሐሳባችንን በመለገስ እንቋጫለን፡፡ ሰላም ያቆየን!!!
Filed in: Amharic