>

መንግስት የለም አትበሉ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግስት የለም አትበሉ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ዜጎች እርስ በርስ ሲጋጩ፣ ዜጎች የመንጋ ሰለባ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ንብረት ሲወድም፣ ተማሪዎች የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ፣ ከተሞች በሕገ ወጦች ሲወረሩ፣ የድረሱልን ጥሪ እየተሰማ ሰሚ ሲጠፋ መንግስት አለ ወይ ያስብላል። መንግስት ግን አለ። ፖሊስ፣ መከላከያ፣ የደህንነት ቢሮ፣ አቃቤ ሕግ እና የመንግስት ኃላፊዎች ለእርስ በርስ ግጭቶች ወይም ለዜጎች መጠቃት አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠታቸው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆኑ ያሳያል።
መንግስት ሙሉ አቅሙን ይዞ ማድፈጡን የምትረዳው በተቃራኒው ዜጎች ከመንግስት ጋር ሲጋጩ ወይም ለመንግስት ስጋት ሲሆኑ ነው። ያኔ መንግስት ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ያልተመጣጠነ እርምጃ ጭምር በአንድ ግለሰብ ላይ ሳይቀር ሲወስድ ታያለህ። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ከመንግስት ጋር የተጣላህ እለት ብቻ ነው መንግስት መኖሩን የምታውቀው። ያኔ ግለሰብ ሆንክ የተደራጀኽ ቡድን መንግስት ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ከአፈር ይደባልቅሃል። ያኔ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ደህንነት፣ አቃቤ ሕግ እና ሹማንቱ ጭምር ይረባረቡብሃል። ሕግ ከማስከበርም አልፈው ሕግ ይጥሱብሃል። ያኔ ወይ በጥይት ትመታለህ፣ እድለኛ ከሆን እስር ቤት ትወረወራለኽ። ከመንግስት ጋር ተጣልተኽ ማንም የማይነካህ ልክ እንደ ጃዋር በወጀብ ከተከበብህ ወይም እንደ ጌታቸው አሰፋ የሚደብቅህ ክልል ካለህ ብቻ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እና አንዳንድ አካባቢም ነዋሪዎች በመንጋ ተከበናል፤ ድረስሉን እያሉ ለቀናት ሲጮኹ የሚሰማ የለም። አንድ ጃዋር ተከብቤያለሁ ቢል ከደጋፊዎቹ በተጨማሪ የመንግስት ሹማምንቱ ጭምር በየቴሌቪሽን ጣቢያው እየወጡ ማረን፣ ይቅር በለን ሲሉ ታያለኽ።  ለዚሁም እንደማሳያ ኮማንድ ፖስት ለድሬዳዋ እና ለሐረር ሊታዘዝ ሲገባው አርባምንጭ ላይ እንዲዘምት ተደርጓል።
በመንጋ እና በተደራጁ ሕገ ወጥ ቡድኖች ሌት ተቀን የሚታመሱት ድሬዳዋ እና ሐረር የመንግስት ያለህ እያሉ፤ መንግስት አርባምንጭን በኮማንድ ፖስት ስር ማድረጉ ምን ይሉታል? ንጹሃን ዜጎችን በጠራራ ጸሐይ የሚገድሉ እና የሕዝብ ንብረት የሚዘርፉ፣ መንገድ የሚዘጉ እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በድንጋይ ናዳ የሚሰባብሩ መንጋዎች የወረሯቸውን ከተሞች መንግስት ችላ ብሎ አርባምንጭ ላይ ከሰዓት እላፊ በኋላ ሞተር ነድተሃል ያለውን አንድ ሰው እግሩን በጥይት መቶታል። ከቀናቶች በፊትም እንዲሁ አንድ ወጣት በታጣቂዎች እዛው አርባ ምንጭ አናቱ ላይ ትልቅ ጉዳት ደርሶበታል።
ይህን ጉዳይ እየተከታተለ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርገውን Dawit Wasihun Kassa ደግሞ ዛሬ ጠዋት #አርባምንጭ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በኮማንድ ፖስቱ ታግቶ መወሰዱን ሰምተናል።  መንግስት ኃይሉን በቦታው እና በአግባቡ ቢጠቀምበት መልካም ነው። ፍትሕ ለአርባምንጭ!  መንግስት ዳዊትን በአፋጣኝ ሊለቀው ይገባል!
ይህ አይነቱ መንግስታዊ አቅምን ለሕዝብ ደህንነት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ከማዋል ይልቅ ለሥልጣን ማስጠበቂያ ብቻ ማዋል አደገኛ አዝማሚያ ነው። ሕግ የሚያስከብር ኮማንድ ፖስት ለድሬዳዋ እና ሐረር!
Filed in: Amharic