>

‹‹የመደመርና የውሕደት የፖለቲካ ሤራ››? (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹የመደመርና የውሕደት የፖለቲካ ሤራ››?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

የኢትዮጵያ ቆሻሻ ፖለቲካ ለሤራ፣ ለአሻጥር፣ ለሸፍጥ፣ ለተንኮል ያነሰበት ጊዜ የለም፡፡ አገዛዞች በየትኛውም ጊዜ ሕዝብን የሚያደናግሩባቸውና የሚያጃጅሉባቸው ፍሬ የሌላቸው የቃላት ኳኳታዎች አያጡም፡፡ ‹መደመርና ውሕደት› ከዚህ የሚደመሩ ይመስለኛል፡፡ አገር በጭንቀት በጥበት ባላችበት በዚህ ቀውጢ ወቅት እነዚህን ‹ባዶ ቃላት› የሚሰማ ጆሮ፣ የሚናገር አንደበት፣ የሚያሰላስል ኅሊና የለንም፡፡ አገዛዞች ግን የፖለቲካ ትርፍ እንደሚያገኙበት አልጠራጠርም፡፡

አንዳንዶች (የውስጥ ዐዋቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው) የወያኔን የሰሞኑን ‹ውሕደት› የሚል ማደናገሪያ በመተንተን ሲደክሙ ይስተዋላል፡፡ ሥራቸው ነውና (መረጃና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ረገድ) ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ይሁን እንጂ ቁም ነገሩ ያለው ነባሩም ሆነ አዲሱ ወያኔ በርእዮተ ዓለም/ በፍልስፍና (ከነበራቸው/ካላቸው)፣ በፖሊሲ ደረጃ በተግባር ምድር ላይ ላለፉት 28 ዓመታት ለሥልጣንና ለዝርፊያ ሲሉ ያዋሉት የአገዛዝ ዘይቤ ላይ እንጂ ስያሜው ላይ ትኩረት ሰጥተን ባንነታረክ መልካም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ ያለው ጽድቅና እነዚህ በተውሶ የመጡ ስያሜዎች አንዳች ኅብረት እንደሌላቸው አስተዋይ ኅሊናና አእምሮ ያለው ሁሉ ገና ከማለዳው የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡ እውን ወያኔ ትግሬ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› ‹ልማታዊ መንግሥት› ወዘተ ለሚባሉ አሳቦች ገብቶትና ተጨንቆ ይመስላችኋል? በነዚህ ማደናገሪያዎች ሽፋን ኢትዮጵያን በእጁ ጨብጦ በግሩ ረግጦ ለመግዛት፣ ሥልጣኑን ለማደላደልና ያለማንም ሀይ ባይ ለማይጠረቃ ዝርፊያው ከለላ ስላደረገው እንጂ፡፡ ቁም ነገሩ ያለው የጐሣ ፖለቲካው፣ የጐሣ ፌዴራላዊነቱ፣ ‹‹ክልል›› በሚል ያደራጀው መዋቅር፣ እነዚህንም ሕጋዊ ቅርፅ ለመስጠት ድርጅታዊ ዓላማውንና ፕሮግራሙን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› አድርጎ ሥራ ላይ ማዋሉ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በታሪኳ አገዛዝ እንጂ ሥርዓት ያለው መንግሥት ኖሯት ስለማያውቅ፣ ፖለቲካ ዕውቀትን (ሳይንስንና ፍልስፍናን) መሠረት አድርጎ የምንመራበት አገር ውስጥ ባለመሆናችን፣ ሕዝብን ለማታለል ወይም በጥራዝ ነጠቅነት የአገዛዝ ቁንጮ የሆኑ ካድሬዎች የሚያመቻቸውን ስያሜ በጽሑፍ ስለተጠቀሙ ብቻ የአገዛዛቸው ይዘት መገለጫ ማድረግ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ለማወናበጃ የሚጠቀሙበትን ሁሉ በቁም ነገር ወስደን ጊዜአችንን ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም አገዛዞች ለማጭበርበር ካልሆነ በቀር ልማታዊ መንግሥት (የወያኔ አገዛዝ ሆኖም አያውቅ) አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም ባጠቃላይ የትኛውም ‹ኢዝም› ገብቷቸው አይደለም የቃሉን ኳኳታ የሚያሰሙት፡፡ በርጕም ወያኔ ዘመን (የአሁኑን ጨምሮ) የነገሠውን አገዛዝ ርእዮተ ዓለምም ሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መለያ ጠባዩን/ገፅታውን ማስቀመጥ (characterize ማድረግ) ካስፈለገ ለባለሙያዎቹ ብንተውላቸው ይሻላል፡፡ ተግባራዊ ጉዳይ ከመሆኑ ይልቅ አካዳሚያዊነቱ ያመዝናል፡፡ 

በመሆኑም ትኩረታችንን አገርና ወገንን የማዳን ተግባር ላይ ብናደርግ ይሻላል፡፡ ለዚህም ሁላችንን የሚመለከቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ማንሳትና በጋራ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

  • ዐቢይ አዋሐድኩት ያለው መምዕላይ (ወንጀለኛ÷ ሽፍታ÷ወያኔ÷አረመኔ÷ክፉ÷ጨካኝ) ድርጅት የሤራው/የዱለቱ መቋጫ ቢሆንስ?
  • ስለ ውሕደቱ የሚነገረው አጥፊው የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› (ወያኔ ‹ክልሎች› ላላቸው ያዘጋጀላቸውን የይስሙላ ‹ሕግጋተ መንግሥት› ይጨምራል) እና በዚሁ የጥፋት ሰነድ ምክንያት የተተከለው የ‹ክልል› አጥር፣ በቆመው የዘር ፌዴራላዊ መዋቅር እና የጐሣ ፖለቲካ ሳይነካ፤ ተዋሐድኩ በሚለው (ወያኔ ትግሬን ጨምሮ) የዕኩያን ድርጅት የተፈጸሙ የሽብር ተግባራትና ግዙፍ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ተጣርተው ለፍርድ ሳይቀርቡ መሆኑን አስተውለናል?    
  • የዐቢይ አገዛዝ ላለፉት 18 ወራት የማዕካላዊውን መንግሥት መከላከያ፣ የፀጥታ ክፍል፣ ፖሊስ ኃይል፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ወዘተ በተረኞች በተለይም ኢትዮጵያ ህልው ሆና እንዳትቀጥል በሚፈልጉ እጅ እንዲያዝ ማድረጉን ታዝበናል?
  • በተለይም በአዲስ አበባ የሥራ ዕድል፣ የመኖሪያ ቤትና ቦታ ድልድል ነዋሪውን ባይተዋር በማድረግ በጐሣዊ አድሎ እንደተፈጸመ እና እንደሚፈጸም አስተውለናል?
  • ጐሣንና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ/እልቂት፣ የአካል ጉድለትና የንብረት ውድመት፣ የአብያተክርስቲያናት ቃጠሎና የቅርስ ውድመት፣ የባንኮች ዘረፋ፣ አጠቃላይ አገራዊ ጥፋት ዐቢይ ቡራኬ ሰጥቶ ባስቀመጣቸው ባለሥልጣናት፣ በሚመራው የጐሣ ድርጅት፣ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ታግዞና በዝምታም በሚታይ ትብብር መሆኑን ተገንዝበናል? 
  • ዘርን መሠረት ካደረገው ከቡራዩው ጭፍጨፋ እስከ ቅርቡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በዘርና በሃይማኖት ሰበብ የሚፈጸመው ግድያና ማፈናቀል ተጠያቂ አካል ሳይኖር ምንም እንዳልተፈጠረ ተቆጥሮ ሕዝብን በእጅጉ በመናቅ በሚሰጡ አሳፋሪ መግለጫዎችና እንቶ ፈንቶ ንግግሮች መታለፉንስ ተመልክተናል?

እነዚህ ሁሉ ተደምረው ባለአእምሮ ለሆነ ሰው የሚሰጡት አገራዊ ሥዕል ምንድን ነው? የአገር መፈታት ሁነኛ ምልክት አይደለም? ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚደረግ ትዕግሥትና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ይመስላችኋል? በጭራሽ!!! ስለሆነም፣

 

  • ኢትዮጵያን የምትሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ምሁራን አይሆንምን ይዛችሁ ትዘልቃላችሁ ወይስ ኢትዮጵያንና ይህን መከረኛ ሕዝቧን ለማዳን በኅብረት ትነሳላችሁ? 
  • አልረፈደም ወይ? አገራችን ባለቤት አልባ ሆና ነገሮች ሁሉ መረን የለቀቁ መሆኑን እያያችሁ ዝምታን ለምን መረጣችሁ? ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንት በምን ዕዳቸው ነው በጭካኔ የሚጨፈጨፉት? ወጣቶች ተስፋ ጨልሞባቸው ገሚሱ ሟች ጥቂት የማይባሉ ደግሞ የአሸባሪዎች መሣሪያ ሆነው የገዛ ወገኖቻቸውን ሲፈጁ ታዛቢ የምንሆነው እስከ መቼ ይሆን?
  • የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ባንድ ‹ጎረምሳ› እምነት ላይ ታኖራላችሁ? አንዳንዶች በሱ ላይ ያኖራችሁት እምነትና ቃላችሁ ከአገር ህልውና ሚዛን ይደፋል? ያገርና የወገን ጉዳይ በይሉኝታ የሚታለፍ ነው?
  • እውነተኛ የተዋሕዶ አባቶች በውስጣችሁ በተሰገሰጉና ለዐላውያን ባደሩ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎችና በመንፈሳዊ ድርቀት በተመቱ አገልጋዮች፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ በማለት በተጠመዱ ግብዞች እንዲሁም ወያኔ ትግሬ በጉልበት ባስቀመጣቸው ካድሬዎች ምክንያት ቤተክርስቲያን የገጠማትን መሪር ፈተና አስተውሉ፤ እንደ ጎንደሩ ኹሉ መላው የአዲስ አበባን ምእመናን (የሠራተኛውን ኃይል ሁሉ አካትቶ) የሚያስተባብር ምሕላ (ወቅቱም ዘመነ ምሕላ ነውና) እንደ ሁኔታው በመስቀል አደባባይ ወይም በየአድባራቱና ገዳማቱ ቢያንስ ለአንድ ሱባኤ ከተቻለ ለሁለት ሱባኤ በአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ምሕላ በተመሳሳይ ሰዓት (የቅዳሴ ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ) ማድረግ የሚከለክለን ምን ኃይል ነው? ለዚህም ፈቃድ እንጠይቅ ይሆን?
  • በተመሳሳይ መልኩ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ (የሃይማኖቱ ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት) ለአገር ለወገን በኅብረት ዱአ ማድረጊያው ጊዜ አሁን አይደለም ወይ? በየመስጂዱና አመቺ በሆነ መሰብሰቢያ ቦታ ኹሉ በተመሳሳይ ሰዓት ይህንን መንፈሳዊ ሥርዓት መፈጸም የማይቻልበት ምክንያት አለ ወይ?
  • እንደ ሠራተኛ፣ መምህራን፣ ጥብቅና፣ ሌሎችም የሙያ ማኅበራት፣ ባጠቃላይ የማኅበረሰብ (ሲቪክ) ድርጅቶች ኢትዮጵያን ለማዳን በኅብረት የምትነሱት መቼ ይሆን? አገዛዞች በተለጣፊነት የሚያቋቁሙትን ወደ ጎን ትታችሁ ተመሳሳይ አገራዊ ዓላማ ያላቸውን አባላት ማደራጀት አይቻልም ወይ?
  • ማኅበረ ግዩራን (ዳያስጶራ) – በዓለም ሁሉ በስደት ተበትናችሁ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን/ያት – ዞሮ መግቢያ ቤታችሁ ቋያ በቅሎባትና ተፋታ፣ የአውሬዎች መፈንጫ ስትሆን ምን ይሰማችሁ ይሆን? ጅምር እንቅስቃሴ እንዳለ ባውቅም በእጅጉ ተጠናክራችሁ ኃይላችሁን አስተባብራችሁ፣ ጭፍጫፊ ጉዳዮችን ወደ ጎን ትታችሁ አገርና ወገን በማዳን ተግባር ላይ የምትጠመዱበት ጊዜ ዛሬ አሁን ካልሆነ መቼ ነው? 

በጭራሽ ወደማይቀለበስ ሁኔታ ውስጥ ከመግባታችን በፊት በጋራ የጋራ መኖሪያችንን የምናተርፈው መቼ ይሆን? 

የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያንገበግባችሁ እውነተኛ ምሁራንና ሌሎች በተለያየ የሕይወት መስክ ዕውቀትና ልምድ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን፤ ያልተደራጀ የሕዝብ ዓመፃ እንዴት ለመሠሪዎችና ጮሌዎች ሲሳይ እንደሆነና ያስከተለውንም ውጤት በዚህ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ በቅጡ የታዘባችሁ ይመስለኛል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ዝንባሌ ያላችሁ የፖለቲካ ማኅበር በማቋቋም፣ ሌሎቻችንም ሲቪክ በሆነ ማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ ሕዝብን አደራጅተን በቅድሚያ ኢትዮጵያን በማዳን፣ ቀጥሎም አገዛዝን በማስወገድ ለልጅ ልጆቻችን የሚሸጋገር ሥልጡንና የተሻለ መንግሥተ ሕዝብና ሥርዓት የምናቆምበት ጊዜ አሁን አይደለም ወይ?

አምላከ ኢትዮጵያ ሁላችን የየድርሻችንን በቅንነት እንድንወጣ ኃይሉን፣ ጽንዑን፣ ብርታቱን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ የመሠሪዎችን ወጥመድ ይበጣጥስልን፡፡ አሜን፡፡

Filed in: Amharic