>

ሐረርጌ እና ድሬዳዋ የክርስቲያኖች የሞት ቀጠና ሆነዋል!!!  (ዳ/ን ኢንጂነር  አባይነህ ካሴ)

ሐረርጌ እና ድሬዳዋ የክርስቲያኖች የሞት ቀጠና ሆነዋል!!!
 ዳ/ን ኢንጂነር  አባይነህ ካሴ
ኹለት አብያተ ክርስቲያናት በምሥራቅ ሐረርጌ ዛሬ ተቃጥለዋል፡፡ የዋቅጅራ መድኃኔዓለም እና  የገልዲድ ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ተቃጥለዋል፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ ዛሬ  ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.  እየኾነ ያለው አስከፊ ነው፡፡
፩. በጋራ ሙለታ የገልዲድ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል፡፡   
፪. በጋራ ሙለታ የዋቅጅራ መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ተቃጥሏል፡፡ 
፫. በሜታ ወረዳ ወተር ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ለጊዜው ይጠለሉ እንጅ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
፬. በሐረር ዙሪያ ወረዳ በቀርሳ ሕዝቡ በሚደርስበት ዛቻ እና ትንኮሳ ምክንያት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ተጠልሎ ይገኛል፡፡ 
፭. እዚያው በሐረር ዙሪያ ወረዳ ውስጥ የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በጽንፈኛ ሙስሊሞች ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰ ሲኾን ሕዝቡ ለመከላከል ዐቅም እንዳነሰው ታውቋል፡፡ እስሁን ደረሱት ጥቃት አልደረሰንም፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ፳፩ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በ፬ቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ ክርስቲያኖች ግን ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ ቤተ ክርስቲያን መሥራት በጭራሽ አይሞከርም፡፡ መካ ላይ ቤተ ክርስቲያን እንደመሥራት ይቆጠራል ይላሉ ጽንፈኞቹ፡፡
በሌሎቹ ፲፯ቱ ወረዳዎች ቢያንስ ቢያንስ አንድ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ በዚሁ ዞን ውስጥ ኩርፋ ጨሌ የተባለው ወረዳ ዛሬ ኹለት አብያተ ክርስቲናት የተቃጠሉበት ነው፡፡ ጎሮ ጉቱ የሚባለው ወረዳ ጥቅምት ፲፪ ቀን ካራሚሌ እና ቦሮዳ በሚባሉት ስፍራዎች ቤተ ክርስቲያን ያቃጠሉበት ቦታ ነው፡፡ ጎሮ ሙጢ በመባል የሚታወቀው ወረዳ ደግሞ ከዚህ በፊት ከፍተኛ የክርስቲያኖች እልቂት የደረሰበት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት አካባቢም የስጋት ቀጣና እየኾነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ ቀርሳ ዛሬ ጥቃት የደረሰባት ወረዳ ናት፡፡
ከእነዚህ ወረዳዎች በተጨማሪ የሚከተሉት ወረዳዎች ደግሞ ክርስቲያኖች በጭንቅ ስጋት ውስጥ የሚገኙባቸው ናቸው፡፡ ቡርቃ፣ በደኖ (በግፉ የታወቀ ቦታ)፣ መልካ በሎ፣ ደደር እና ሜታ፡፡ አንጻራዊ ሰላም የሚገኝባቸው ወረዳዎች በጣም ጥቂቶች ሲኾኑ እነርሱም ከስጋት ነጻ አይደሉም፡፡ ለጊዜአዊ መጠለያነት ሊረዱ ስለሚችሉ ስማቸውን እንዘረዝራለን፡፡ ባቢሌ፣ ጉርሱም እና ጭናግሰን ናቸው፡፡
ምዕራብ ሐረርጌ
በደረሱን መረጃዎች መሠረት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን መሰላ ወረዳ (ከአዲስ አበባ ሐረር ከሚወስደው አውራ ጎዳና ፳፱ (29)ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ትናንት በደረሰው ጥቃት እርቀ ሰላም ሞገስ የምትባል አራስ (ገና ከወለደች ፫ ወር ያልሞላት) ኦርቶዶክሳዊት በድንጋይ እና በዱላ በደረሰባት ጭፍጨፋ ጨቅላ ልጇን ጥላ ሕይወቷ ተቀጥፏል፡፡ እስከ ናዝሬት ኃይለ ማርያም ሆስፒታል ለማድረስ ቢሞከረም ሕይወቷን መታደግ አልተቻለም፡፡
እስካሁን ድረስ በደረሰን መረጃ መሠረት አጥቂዎቹ የሦስት ክርስቲያኖችን ቤት በማቃጠል ሙሉ በሙሉ አውድመዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ድብደባ እና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፰ (8) ክርስቲያኖች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ወደ ህክምና ቦታ ለማድረስም ጭንቅ ኾኖባቸዋል፡፡ ከከተማው ውጭ ባሉ የገጠር ቦታዎች በቀጪ አዲስ ዓለም ቅዱስ ሚካኤል፣ በወጊቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በሞሌ ቅድስት ማርያም፣ በቆሬ ቅዱስ ገብርኤል፣ በጎያል መድኃኔዓለም (በተለይም አባ ጨፌ በሚባለው ይከፋል) እየደረሰ ያለው አካባቢውን ከክርስቲያኖች ነጻ የማድረግ የጥቃት አደጋ በጣም አደገኛ መኾኑ ታውቋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ ሰሞኑን ሞቅ በረድ ሲል የነበረው ጥቃት እንደገና እንዳገረሸ እየተሰማ ነው፡፡
መንግሥት ይህንን ጉዳይ ማድበስበሱን ያቁም፡፡ ኦርቶዶክሳውያንን ሊታደጋቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ይህ ጦስ ራሱንም ይበላዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ላይ የአየር ኃይል ይባል የምድር ጦር ተከማችቶ ምን ይሠራል? ፈጥኖ ሊደርስ ይገባዋል፡፡ የየ አህጉረ ስብከቱ  ጽ/ቤቶች በአስቸኳይ ኹኔታውን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ተነጋግረው ወደ ተሻለ ርምጃ መሔድ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እጅ እና እግርን አጣጥፎ ክርስቲያኖችን የማስበላት ድንዛዜ ሊለቅቀን ይገባል፡፡ የአሮሚያ ባለሥልጣናት ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጆሮ ዳባ ብለው እያስበሉን ነው፡፡ በቅርቡ ለሰለማዊ ሰልፍ እስተባባሪዎቹ የሰጡት ምላሽ ይህንን ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡ እያለቁ ያሉት ኢትዮጵያውያን ናቸው እንጅ መጤዎች አይደሉም፡፡ መጤዎችም እንኳ ቢኾኑ ይህ እንዲደረግ ሊፈቀድ ባልተገባው ነበር፡፡
ትናንት እና ዛሬ ማለትም ኅዳር ፪ እና ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በምሥራቅ እና በምዕራብ ሐረርጌ ኦርቶዶክሳውያን በጽኑ መከራ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ግድያው እና ጥቃቱ ሁሉ ምድሪቱን ከኦርቶዶክሳውያን የማጽዳት ሥራ እንደኾነ ከግምት በላይ አልፎ ሔዷል፡፡ ይህ የተጠና ሥራ ውጤት ነው፡፡ ጊዜው ተመቸ እንጅ ተቀብሮ የኖረ ፈንጂ መኾኑን ዐውቀን እንነሣ፡፡
Filed in: Amharic