>

ደውሉ ያስገመገመ  ቀን ….  (አሌክስ አብርሀም)

ደውሉ ያስገመገመ  ቀን …. 
አሌክስ አብርሀም
   ገና ባልፀኑ የልጅ ጣቶቸ ሰበዝ አስይዞ ሃሁ ያስቆጠረኝ …እናገርበት ልሳን እጠበብበት ፊደል የሰጠኝ የትኛውም ዩኒቨርስቲ አይደለም !  ይሄው እራሴን የምገልፅበት አንደበት የሆነችኝ  ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነች ! ያቃጠላት የእኔንም አንደበት  አብሮ አቃጠለ !
     አገሬን እንድወድ ያስተማረኝ የትኛውም ፖለቲከኛ  ወይም የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ አይደለም … ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ናት ….ያቃጠላት በአገሬ ያለኝን እምነተን አብሮ አቃጠለ !!
     ሰው ሁሉ በፈጣሪ ፊት  እኩል መሆኑን ያስተማረችኝ ገና በህፃንነቴ  ፈሪሃ እግዚአብሔርን ያለማመደችኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ናት …..ያቃጠላት ለሰው ያለኝን የዘመናት እምነት አብሮ አቃጠለ !!
    ማነህ ስባል ከስሜ ቀድሞ ፊቴ ላይ የሚነበበው ማንነት እኮራበት ቅርስ እተርከው ታሪክ ያስተማረችኝ  ….ማስተማር ብቻ አይደለም  በቢሊየን የማይተመኑ ውድ ቅርሳቅርስ  ሽንብራ ቆርጥወመው የጠበቁ ልጆችን ያፈራች ….. ታሪኬ ተረት አለመሆኑን አሳይበት ዘንድ ለኔ ዘመን ህያው መረጃ ያሳለፈች ኦርቶዶክስ ናት ….ያቃጠላት ማንነቴን አቃጠለ !!
ሚሊየን ድሆች  ይልሱ ይቀምሱ አጥተው በእርሃብ አለንጋ ሲገረፉ  ከየትኛውም አለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት በፊት መቀነቷን ፈታ ያጎረሰቻቸው በደብሯ ስር ተጠልለው ታደጊን ሲሏት በፍፁም እናትነት የታደገች…ደዊያቸውን ሳትፀየፍ ክፋታቸውን ሳትሰለች ያቀፈች  የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ናት …ያቃጠላት በጎነትን አቃጠለ !!
     ሁላችንም የተጠለልንባት አገር  …ከየትም በቀዳነው ቅራሪ አይዲዮሎጅ … በነተበ ቲዮሪ አይደለም የቆመችው …ይች አገር  አገር ሁና እንድትኖር ደግፈው ከያዟት  ታላላቅ ምሰሰዎች  አንዱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አስተምሮዎች ናቸው …..እዚች ቤተክርስቲያን ላይ እሳት ስትለኩስ ከብልግናህ በላይ …ከትእቢትህ በላይ አገርን ደግፎ የያዘ ምሰሶ እያፈረስክና ተሸክማ የኖረችው መከራ ተደርምሶ ምድርህ የራስህ ቀብር እንዲሆን እየቸኮልክ ነው !
    የእምነቱ ተከታይ ብንሆን ባንሆን … በቅርብ ብንሆን በሩቅ …ይችን ቤተ ክርስቲያን ስትነካ  ማንም ሁን ማን ሁላችንም ውስጥ ያለ ማንነት ይፀየፈሃል ! ሁላችንም ውስጥ ያለ ማንነት  ይንቅሃል …ይሄ መፀየፍና ንቄት ደግሞ አልፎ የሚሄድ ተራ ስሜት ሳይሆን  ለዘመናት የልጅ ልጆችህን የሚያሸማቅቅ ምድርህ ላይ የተፃፈ  ታሪክህ ይሆናል !! ነፍሳችን ከአንተ የፖለቲካ እንቶፈንቶ በላይ  ፣ ከአንተ የዘርም ይሁን የብሔር ጩኸት በላይ …ከአንተ የትእቢት ድንፋታ በላይ  ከደብሮቿ ለሚያስገመግመው የድረሱልኝ ደወል ታማኝ ነው !
    ደማችን ውስጥ ያለምንም ልዩነት  ታላቅ ክብሯ ታላቅ ታሪኳ ታላቅ እናትነቷ  አለ …ትእግስቷ አልቆ ልጆቿን መጥሪያ ደውል  ከነዛ ደብሮች  ያስገመገመ ቀን  …. እመነኝ የቱንም ያህል ሃይል ቢኖርህ የፈለገ ገንዘብና  ስልጣን  ቢኖርህ ከዛ በኋላ ቁመህ አትሄድም !!እሳትህን ችላ ለሰላም ስትጮህ ስማ ….እብሪትህን ችላ ለፍቅር ስትጣራ ስማ …ካልሰማህ ሰው ለሆነ ሁሉ ደውሏን ማሰማቷ አይቀሬ ነው !! ከደውሉ  በኋላ እንኳን የቆመ እብሪተኛ ሰው የቆመ ሰራዊት ኑሮ አያውቅም !!  ብታጣምመውም ታሪክ የሚነግርህ እውነት ይሄው ነው !! ታሪኩን ባታምን እንኳን ግራ ቀኝህን ተመልከት ሳር ቅጠሉ አፍ አውጥቶ የሚነግርህ ይሄንኑ ነው !!
Filed in: Amharic