>

ብሶት የወለደው ኢ ህ አ ዴ ግ ምቾት በወለደው እርጅና ውስጥ ! (አሌክስ አብርሃም)

ብሶት የወለደው ኢ ህ አ ዴ ግ ምቾት በወለደው እርጅና ውስጥ !
አሌክስ አብርሃም
አዎ ኢህአዴግ አርጅቷል !! ያ ተራሮችን የሚያንቀጠቅጥ ትውልድ አርጅቷል ! እነዛ የህዝብን ብሶት አርቀን እናያለን የሚሉ አይኖች በእርጅና ምክንያት እግራቸው ስር የቆመ እንቅፋት መመልከት ተስኗቸዋል ! በሽ ምርኩዝ ተደግፎ በሽ መቀነት የደከመ ወገቡን አስሮ የሚውተረተረው ኢህ አ ዴግ በየመንገዱ በሚገጥሙት እና ተሻግሮ ህዝቡን ማሻገር በሚጠበቅበት በርካታ መሃበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅፋቶች ከህዝቡ ቀድሞ በግንባሩ እየተደፋ ወደፊት መራመድ አቅቶታል !! ህዝቡም የመውደቅ የመነሳቱን አርቲቡርቲ ምክንያቶች ብቻ ማድመጥ ስራው ሁኗል !
በእርግጥ ያረጀ ሰው አልፎ አልፎ ያልወለቁ ጥርሶች ለምልክት ድዱ ላይ እንደሚታዩት ኢሃዴግም አንዳንድ የተሸሉ ግለሰቦች ከማቀፉ ውጭ እንደተቀናጀ ጠንካራ ግንባር ከላይ እስከታች ያለ አካሉን ማሰራት ተስኖት ያረጀ ዙፋኑ ላይ ባረጀ ዲስኩርና አሰራር ተቀምጦ ቀርቷል !ብሶት የወለደው ኢህአዴግ ብሶት እያወራ አርጅቷል ! የእለት ተእለት የብሶት ተረቱን እየሰሙ ያደጉ ህፃናት ብሶተኛ ወጣቶች ሁነዋል …ብሶተኛ ህዝብ ፈጥሯል !
ጆሮወቹ በእርጅና ምክንያት ህዝብን መስማት አቅቷቸዋል ….ክንዶቹ ዝለዋል ቆዳው ተሸብሽቦ የመሃበረሰቡ ሂወት ላይ ፊቱ ጨፍግጓል ! በእርጅናው ምክንያት መከላከል ከማይችለው ኪሱ በአደራ ያስቀመጠውን የህዝብ ገንዘብ እንዳሻቸው እጃቸውን እየላኩ በሚቆነጥሩ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ አላረጀህም እየተባለ ቢጨበጨብለትም ኢህአዴግ አርጅቷል !
የህዝቦችን መሰረታዊ ችግር እንደባለጥለት ኩታ አጣፍቶ በአደባባይ የሽማግሌ ዲሰኩርና ልብ ህዝብ ውስጥ ጠብ የማይል ተስፋ ከመለፈፍ በቀር እርጅና ያደነዘዘው ኢህአዴግ እንኳን የህዝብ ችግር ሊፈታ ቀርቶ እራሱን የወረሩትን ዝንቦች ከራሱ ላይ ማባረሪያ አቅም አጥቶ ጭራውን ለምልክት እንዳንከረፈፈ ቁሟል !! ልክ እቤት የዋለ ሽማግሌ በዶሮም በልጅም ጎረቤት ጋር እንደሚናቆረው እርሱም ከተቀዋሚውም ከተማሪውም ከፀሃፊውም እየተናጨ ነውና ግዴላችሁም አርጅቷል !
አላፊ አግዳሚውን መመረቅና መርገም የሽምግልና ምልክቶች ከሆኑት አንዱ መሆኑ ይታወቃል …ሽማግሌወች ሰላም ስላላችኋቸው ወይም የሚያወሩትን እራሳችሁን እየነቀነቃችሁ ስለሰማችኋቸው ብቻ ይመርቋችኋል …. ትንሽ ብትገለምጧቸው አልያም ሲያልፉ ከመቀመጫችሁ ብዲግ ብላችሁ ካላከበራችኋቸው አልያም የሚያወሩትን ታሪክ ከተቃወማችኋቸው ሊረግሟችሁ ይችላሉ …አዛውንቱ ኢሃዴግም ይህ ምልክት በጉልህ እየታየበት ነው ! ከስር ከስሩ አስር ጊዜ እጅ የሚነሱትን ኢቲቪ በሚባል ልሳኑ ምርቃትና አድናቆት ሲያዥጎደጉድ … በእድሜየ ብቻ አላከበሩኝም ብሎ የሚያስባቸውን በየቀኑ ይረግማል ያጥላላል ውርስ ሁሉ ሊከለክል ይችላል ! ….ግዴላችሁም ብሶት የወለደው ኢህአዴግ ምቾት በጣለበት እድሜው ምክንያት አርጅቷል!!
አዎ እኛ ኢትዮጲያዊያን ተቸግረናል ችግራችን በዚህ ባረጀውና ህዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጦ በጃጀው ኢህአዴግ ሊቀረፍ አልቻለም! በዚህ ዘመን ቢያንስ መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን እንኳን መፍታት ያቃተው ‹ፓርቲ › በእርግጥም ከእርጅና ውጭ ምን ምክንያት ሊኖረው ይችላል ?
በእርጅና ወደደነቆሩት ጆሮወቹ በጣም ተጠግተን እንዲህ እንላለን ‹‹ አዛውንቱ ኢህአዴግ ሆይ ኩርርርርርር ይሰማሃል …. መፍተሄ መፍተሄ መፍተሄ እባክህ የከበቡህን ዝንቦች አባርርና መላውን ኢትዮጲያዊ ያሳተፈ በባለ ምላሶች ሳይሆን በባለሙያወች የተዋቀረ መንግስት መስርተህ ችግራችንን ፍታልን ጨለማ ውሃ ጥም የስልክ ችክር የመንገድ የሰበአዊ መብት ችግሮች ወረውናል ምክንያት ሳይሆን መፍትሄ መፍተሄ መፍተሄ !! ሽማግሌ ልጀ ብር ልኮልኝ እከሌ ካፖርታገዝቶልኝ እንደሚለው ‹‹አገራት ያበደሩህን ብድርና የሰጡህን ስጦታ እንደትልቅ ድል እያወራህ አሰለቸኸን ! ሽማግሌ አትጩሁብኝ እንደሚለው አንተም አትሰለፉ አትጩሁ ልተኛበት እያልክ ነው ! ግዴለህም እርጅናህን እመንና ለለውጥ ከልብህ ተነሳ !!
ይህ ፅሁፍ በድጋሜ የቀረበው ሽማግሌ ነገር ካልተደገመለት ስለማይሰማ ነው !
Filed in: Amharic