>

አገራችሁ ትፈልጋችኋለች ! (ውብሸት ታዬ)

አገራችሁ ትፈልጋችኋለች !
ውብሸት ታዬ
   ዛሬ አጠር ያለች መልዕክቴን ማስተላለፍ የምፈልገው በአገራችን የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታችሁን በመከታተል ላይ ለምትገኙ ታናናሽ እህቶቼና ወንድሞቼ ነው።
   እንደምታውቁት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ዕውቀት ለመገብየት የወጡ የነገይቱ አገር ተረካቢዎች ሕይወት እንደዋዛ ሲቀጠፍ ቆይቷል።
   ቤተሰብ ነገ ራሳቸውን ይችላሉ፣ ይጦሩኛል፣ ከዚያም አልፎ ትውልዳዊ አደራቸውን ተረክበው አገር ይመራሉ የሚላቸውን ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መላክ ወደጦር ግንባር የመላክን ያህል እያስጨነቀው መጥቷል።
   ለዓመታት መለያየትን፣ የተዛባ ወገንተኝነትንና ጥላቻን ብቻ ሲሰብኩ የነበሩ ወገኖች ዘራቸው ፍሬ አፍርቶ እናንተ ዕዳውን እየከፈላችሁ ትገኛላችሁ። በእናንተ ንጹህ ደም ጎርፍ  ዋኝተው የየግል ፍላጎቶቻቸውንና የስልጣን ጥማቸውን ማሳካት ለሚፈልጉ ሃይሎች በተላላነት በፍጹም መሳርያ አትሁኑ !
   በአገራችሁ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የራሳችሁን ገንቢ አስተዋጽኦ እንዳታበረክቱ ማንም ሊያግዳችሁ አይችልም። ይህ ማለት ግን መነሻውን የለየለት ጥላቻና መተላለቅ፤ መዳረሻውንም አገራዊ ምስቅልቅል በመፍጠር ጎረቤት ሶማሊያ እንደሆነችው ሕዝብን በየመንደሩ ሃይል በተሰማቸው  ጉልበተኞች እንድትተዳደር ለሚፈልጉ ሃይሎች እንደቦይ ውሃ በተቀደደላችሁ መስመር መንጎድ አለባችሁ ማለት አይደለም።
   መጠየቅና መሞገት አለባችሁ። ለምን? እንዴት? እያላችሁ በአመክንዮ ልትሞግቱ ይገባል። ልትሞቱ ግን ፈጽሞ አይገባም !
  ከጥላቻ ይልቅ በፍቅር ተሸናነፉ። ከልዩነት ይልቅ ሕብረታችሁን አጥብቁ። እናንተ በዓመታት የልፋታችሁ ውጤት አሁን ላላችሁበት የደረሳችሁ፤ በነገዋ አገራችሁ ውስጥም ታላቅ ሚና ያላችሁ የትውልድ ፍሬዎች እንጂ ለሌሎች ያልተገራ የስልጣን ጥምና ሽኩቻ ነጋችሁን በዛሬ የምታጣፉ ያላዋቂዎች አይደላችሁም። ቤተሰቦቻችሁ ይፈልጓችኋል! አገራችሁ ትፈልጋችኋለች!
Filed in: Amharic