>

የላቀ ምስጋና እና ክብር ለወልዲያ አበው ወእመውና ለአጠቃላይ ነዋሪው!!! (ታዬ ቦጋለ) 

የላቀ ምስጋና እና ክብር ለወልዲያ አበው ወእመውና ለአጠቃላይ ነዋሪው!!!
ታዬ ቦጋለ 
የጋሞ አባቶችና ወጣቶች ወገኖቻቸው ሲገደሉ፤  ስለክፉ ፈንታ ብቀላ አላረገዙም። ይልቅዬ አባቶች ጎንበስ ብለው ልጆቻቸውን ተማፀኑ። በስነምግባር ታላቅነት ተኮትኩተው ያደጉት የጋሞ ልጆች – ወላጆቻቸውን አክብረው ታላቅ የፍቅር ጀብድ ፈፀሙ። በዚህም የተነሳ ዛሬ ጋሞ እንደ ማህበረሰብ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ታትሞ –  “ጋሞ ነኝ” ማለት ክብር ፍቅር የልህቀት ማሳያ ሆነ ብል ፈፅሞ እብለት የለበትም።
*
ትላንት በተመሳሳይ ከወልዲያ ከተማ  ታላቅ የወገን ፍፃሜ ተሰማ። ፖሊስ አጣርቶ የሚገልፀው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ – ምናልባት በእኩያን ሴራ፤ ተስፋ ሰንቀው ዩኒቨርሲቲ የገቡ እና ቤተሰብ መከራውን ዐይቶ በውጣ ውረድ አሳድጎ፣ በስስት የሚጠብቃቸው፤ የሁለት ተማሪዎች ህይወት ተቀጠፈ። አሥር ያህል ተማሪዎች ጉዳት ደረሰባቸው።
 *
ይህንን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ ወልዲያዎች አደጋ ደርሶባቸው ሆስፒታል የገቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፦ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ አጥሚት፣ የተለያዩ አይነት ጭማቂዎች ይዘው እየጎበኙ ከመሆኑ ባሻገር ሆስፒታል አድረው በየተራ በማስታመም ተጎጂዎቹ በወገን መሀከል እንዳሉ ያህል እንዲሰማቸው እያደረጉ ነው።
የጋሞዎች ጅማሬ በአማሮች በላቀ ፍቅር ተደግሞ እነሆ ደም ሊያፋስሱ የሚንቀዠቀዡ ሰይጣኖች ያፍሩ ዘንድ = ትላንት “የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የኔ ነው” ብሎ ስለኦሮሞ በስናይፐር የወደቀው አማራ ዛሬም በልጆቹ (የኦሮሞ ልጆች) ጉዳት ልቡ ተሰብሮ = በዕንባ ታጅቦ እዬዬዬዬዬ ሲልና ዕንባው ጉንጮቹን እየገመሰ ሲያልፍ ታይቷል።
*
ለዚህ ነው ለገረፉኝ ለገደሉኝ ለዘረፉኝ ላኮላሹኝ ላመከኑኝ፤  ዛሬም ከእኩያን ተላላኪዎች እየተመሳጠሩ ሚያስገድሉኝ ወያኔ / ትህነጎች፦  በርቱ ግፉ ቀጥሉ ለማለት መቀሌ ከመጓዝ ይልቅ ስጋበዝ ወደ አማራ የምዋበው። እደግመዋለሁ አማራ ቤሳ ቢስቲን ሰጥቶኝ አያውቅም፤ አልፈልግምም። ፍቅር የለገሰኝን፣ በኦሮማራ ያደመቀኝን፣ በክፉ ቀን አብሮኝ ቆሞ አጋርነቱን ለገለፀልኝ አማራ ምላሹ ሜንጫና አንሶ በተገኘበት ገድሎ በኃጢአት ደም ጀግኜ ዐልታይም። ሊሰመርበት የሚገባው ለትግራይ ህዝብ የላቀ ፍቅር አለኝ። ወያኔ ትህነግን ለሚደግፍ (በሰቆቃችን ለሚሳለቅ) ግን ቅንጣት ክብር የለኝም።
*
የአማራ አባቶች ወጣቶቹን እየመከሩ፣ እያፅናኑ፣ እያበረቱ ‘አለን ከጎናችሁ ነን’ ሲሉ ውለዋል። ይህንን በጎ ተግባር የአማራ ወጣቶችም ጀምረዋል። ትላንት የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የእኔም ነው እንዳሉ ሁሉ፤ በኦሮሚያ ውስጥ የተፈፀመውን አሰቃቂ ተግባርና የወልዲያውን አሰቃቂ ፍፃሜ ሊያወግዙ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ሰምቻለሁ።
*
ሁሉም ወጣት የደም ነጋዴ ፖለቲከኞችንና ሃላፊነት የጎደላቸውን ዝቃች “አክቲቭ ቢስቶች” (ስመ አክቲቪስት) ሳይሆን አባትና እናቶቹን ትላንት ስለነበረን የበዛ ፍቅርና ያ  አብሮነት በማን እንደተነጠቀ ይጠይቅ። በቃ አባት እናትና ጎረቤት አረጋውያንን ጠይቅ። የዘመዶችህን ጋብቻ ተመልከት – ባይዋደዱ ተጋብተው እንዲህ ማትለየው ህብር ይፈጠር ነበር። እናንተ ገና ስለሆናችሁ አታፈቅሩም እንጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዐይታችሁ የምትወዷት ልጅ ዘሯ ምንድነው?!
 ዐየህ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፦
“ማታ ማታ አማራ ሚስቶቻቸውን አቅፈው እየተኙ
ቀን ቀን አማራና ኦሮሞን ያጋድላሉ”
ሲሉ መልዕክቱ ሰምና ወርቅ አለው። ወገን አትሸወድ!
*
ቀድሜም ብያለሁ – የተቀጠፉ አለፉ። ገዳዮች አያተርፉም ከእድሜ ልክ ፀፀት ጋር ዘብጥያ ይወርዳሉ። ጓደኞቻቸው ተመርቀው ወደ ሥራና ትዳር ሲሰማሩ እነሱ በእስር ይማቅቃሉ። ለዚህ ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቀጭን መመሪያ ከቁጣ ጋር አውርዶ ፖሊስ ምርመራውን እያጧጧፈ ነው።
 ነገም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በላኪዎች ፍርፋሪ ተጥሎላችሁ፤ የት ጋ ረብሽ የሚያስነሳው አንድ እኩይ እንደሚያሳስታችሁ አታውቁምና ረጂም የነገ ህይወታችሁን አታበላሹ። የምን ሞኝነት ነው። ወጣቱ ነቄ መሆን አለበት – አራዳ!!!
አጋዳዮችህ የሚኖሩበትን ቤት ተመልከት። የሚነዱትን መኪና ዕይ። ባንተ ነፍስ እየቆመሩ ለእነሱ ህይወት እንዴት እንደሚሳሱ ተመልከት። በ’ጋርድ’ እየሄዱ፦ “ተከበብኩ” ይላሉ እነ ከበቡሽ። አይሟሙ – “ሞቴም እናንተ መሀከል ነው” ብለው በተቃራኒው ሞትን እናንተ መሀከል ደገሱ።
*
ትላንት የገደሏችሁ መቀሌ መሽገው ትኩረቱን ከእነርሱ ላይ ለማዟዟር (Diversion) እና ቢችሉ መልሰው የትላንቱን መከራ ሊጭኑብህ ሲሯሯጡ ንቃ እንጂ ወገኔ!!!
ትላንት በስናይፐር ለፍትህ ስትጮህ ወድቀህ፤ ዛሬ በገጀራ ጠገራና ዱላ ወንድምህን መግደል ፍትህ ነውን?!
*
በፀብና መገዳደል ኢንቨስትመንት ቢቆም –  ነገ የምትቀጠረው የት ይሆን?! ሀገር ብትፈርስ እንደ ሶርያውያን ደቡብ ሱዳናውያን ሶማሊዎች… መጠጊያህ የት ይሆን?!
ቄሮ ፋኖ ዘርማ… የሚያምርባችሁ የትላንትናው አብሮነት ነው። ከዛሬው ፀብ በሚሊየኖች የሚያፍሱት እነ እንትና ናቸው። አንተማ ትርፍህ የደም ኃጢአት ወይም ሞት ነው።
*
ወደ ፈጣሪ ተመልከት። እኔ ላጥፋህ ግድየለህም መርምር። እመነኝ ምንም አታተርፍም። 12 ወራት ሙሉ በመስኖ የምትታረስ ተስፋ ያላት ሀገር ይዘህ፤ ትላንት ገበሬውን ላፈናቀለው ወያኔ እኩይ ዓላማ ማሳኪያ ስትሆን የምር ያማል። ያሳዝናል። አንተ እኮ የተፈጠርከው በዚህ 27 ዓመት ነው። ያየኸው ዛሬ እያለ – ካላየኸው ትላንት የሚያጣሉህ- ምን ተልእኮ ይዘው እንደሆነ መርምር።
እመነኝ አባትህ ነኝ። እኔ አንተን ልጎዳህ አልመክርህም። ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሆኜ በእግሬ እየሄድኩ፤ ከሞት ጥላ ጋር ተፋጥጬ የምመክርህን አድምጠኝ። እባክህ ወገኔ እመነኝ እንቅልፍ ማጣው አባቶቼና እናቶቼ ሀገር ያቆዩኝ እንቅልፍና ምቾት አጥተው ስለሆነ ነው። አንተ ተስፋ አለህ – ተስፋህን አታጨልም።
*
ቤተሰብህ ጥቁር ገዋን ለብሰህ እንድትመጣ ሲጠብቁ – እባክህ ጥቁር የሀዘን ልብስ (ማቅ) አታልብሳቸው።
እንደ ጋሞና አማራ አባቶች ተለመነኝ።
NB. አስደንጋጭ ክስተት ያልኩት ጥሩ ለማንበብ ስለማንጓጓ ነውና ዝቅ ብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
Filed in: Amharic