>

ተስፋየ ገብረአብ፡  የወያኔው ኦቶ ዲትሪኽ (መስፍን አረጋ)

ተስፋየ ገብረአብ፡  የወያኔው ኦቶ ዲትሪኽ

 

መስፍን አረጋ

 

መንደርደርያ

 

የዚህ ጦማር አላማ ብአዴን (አዴፓ) በፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ሊከሳቸው ከሚገባቸው አያሌ ግለሰቦች ውስጥ ዋናውና የመጀመርያው የወያኔው ተስፋየ ገብረአብ መሆን እንዳለበት ለማስገንዘብ ነው፡፡  ጃዋር ሙሐመድን በዓለም አቀፍ ፍርድቤት ለመክሰስ አንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡  በኔ እምነት ግን ቢቻል ከጃዋር አስቀድሞ ባይቻል ደግሞ አብሮ መከሰስ ያለበት ቀንደኛው ፀረሰብ ወንጀለኛ ተስፋየ ገብረአብ ነው፡፡

 የተስፋየ ገብረአብ ጀርመናዊ አቻ ኦቶ ዲትሪኽ (Jacob Otto Dietrich) በመጀመርያ ደረጃ የወንጀለኛው ናዚ ድርጅት አባል በመሆኑ ብቻ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በወንጀለኛው ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች (በተለይም ደግሞ በፕሬስ መምርያ ኃላፊነት) ላይ በነበረበት ወቅት በተረከታቸው (narrate) ፀረይሁዳ ትርክቶች (narration) ሳቢያ በኒዩርምቤርግ ችሎት (Nuermberg trials) ቁሞ (tried) በፀረሰብ ወንጀል ተወንጅሎ፣ ሰባት ዓመት ተፈርዶበት ዘብጥያ ከወረደ፣ ከዲትሪኸ ቢብስ እንጅ የማያንስ ፀራማራ ወንጅል የፈጸመው ተስፋየ ገብረአብ ደግሞ ተገቢውን ቅጣት የማያገኝበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡  የጥቅምት 13 እና 14 ጭፍጨፋ ብቻ ግለሰቡን በፀራማራ ወንጀል ለመክሰስ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ክሱን ባማራ ክልል ውስጥ በመክፈት፣ ግለሰቡ በኢንተርፖል ታድኖ ወደ ጦቢያ እንዲመጣ መጠየቅ ብቻ በግለሰቡ፣ በመሰሎቹና ሊመስሉት በሚያስቡ ፀራማሮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡    

 

ወያኔ፡ የጦቢያው  ናዚ

በፀራማራነት ላይ የተመሠረተው ዘረኛው ወያኔ፣ በፀረ ይሁዳነት ላይ ከተመሠረተው ዘረኛው ናዚ ጋር በብዙ ረገዶች ይመሳሰላል፡፡

  • ወያኔ አፍሪቃዊ ናዚ ነው፡፡  ናዚ ፀረይሁዳ፣ ወያኔ ፀራማራ፡፡ 
  • መለስ ዜናዊ አፍሪቃዊ ሂትለር ነው፡፡
  • ስብሐት ነጋ አፍሪቃዊ ዲትሪኽ ኤካርት ነው፡፡  የሂትለርን ዘረኛ (በተለይም ደግሞ ፀረይሁዳ) አስተሳሰብ የቀረጸው፣ የናዚ ርዕዮተ ዓለም የመንፈስ አባት የነበረው፣ የሞርፊን ሱሰኛው፣ ሰካራሙና፣ ሴሰኛው ዮሐንስ ኤካርት (Johann Dietrich Eckart)
  • በረከት ስምዖን አፍሪቃዊ ዮሴፍ ጌቤልስ ነው፡፡  የናዚ ማስታወቂያ ሚንስቴር የነበረው ዮሴፍ ጎቤልስ (Joseph Goebbels)
  • ተስፋየ ገብረአብ ደግሞ አፍሪቃዊ ኦቶ ዲትሪኽ ነው፡፡  የናዚ ፕሬስ መምርያ ኃላፊ የነበረው ያቆብ ዲትሪኽ (Jacob Otto Dietrich)፡፡

መለስ ሙቶ ተቀብሯል፣ ስብሐት ነጋ አንድ እግሩ መቃብር ገብቷል፣ በረከት ታስሯል፣ ተስፋየ ግን አሁንም መርዙን ይነዛል፡፡  የወያኔው ጎቤልስ በረከት ስምዖን፣ ወያኔ በጦቢያውያን ላይ (በተለይም ደግሞ በጠላትነት በፈረጃቸው ባማሮች ላይ) ለፈጸመው ሂትለራዊ ጭፍጨፋ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ተጠያቂ ነው፡፡  ስለዚህም ብአዴን (አዴፓ) በረከትን መከሰስ የነበረበት በኢምንት ወንጀሉ በገንዘብ ማጥፋት ሳይሆን በጃምንት ወንጀሉ በዘር ማጥፋት ነበር፡፡  ለማንኛውም የዚህ ጦማር ርዕስ ወደ ሆነው ወደ ወዲ ገብረአብ እንመለስ፡፡

 

ወዲ ገብረአብ

ልክ እንደ ናዚው የፕሬስ መምርያ ኃላፊ ኦቶ ዲትሪኽ፣ የወያኔው የፕሬስ መምርያ ኃላፊ የወዲ ገብረአብ ዋና ተልዕኮ ወያኔያዊ ሕትመቶችን (ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ መጽሐፎችን፣ ወዘተ.) በበላይነት በመቆጣጠር፣ ጦቢያዊነትን አመንምኖ ጎጠኝነትን በማግነን በካፍለህ ግዛው ዘዴ የወያኔን አገዛዝ በማይናወጽ መሠረት ላይ ማቆም ነበር፡፡  በተለይም ደግሞ የወያኔን ጥንካሬ እጅግ አግንኖ የማይጋፉት ባላጋራ ማስመሰል ይጠበቅበታል፡፡ ወያኔ በተቃዋሚወቹ ውስጥ ለሚያሰማራቸው አፈ ጮሌ ሠርጎ ገቦች ደግሞ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ተቃዋሚወችን የማተራመስ ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ ከፍተኛውን እገዛ ይደርጋል፡፡ በተለይም ደግሞ የጦበያውያንን ጥቃቅን ልዩነቶች አግዝፎ ርስበርስ በማናቆር፣ ሙሉ ትኩረታቸውን ርስበራሳቸው ላይ አድርገው ርስበራሳቸው እንዲጠባበቁ ማድረግ ይጠበቅበታለ፡፡  

ልክ እንደ ዲትሪኽ፣ ወዲ ገብረአብም ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት የበቃው፣ አስቀድመው የተሰጡትን ኃላፊነቶች ሁሉንም በሚገባ ተወጥቶ ከወያኔው መሪ ከመለስ ዜናዊ ከፍተኛ አድናቆት፣ ከበሬታና፣ መታመን በማግኘቱ ነው፡፡  ልክ እንደ ዲትሪኽ፣ ተስፋየም አዲሱን ኃላፊነቱን ከተጠበቀው በላይ አሳክቶ የወያኔውን መሪ ይበልጥ በማስደሰቱ፣ ቅናት ቢጤ የለመጠጣቸው ባልደረባወቹ ከመሪው ጋር ሊያቃቅሩት ጥርሳቸውን ነክሰውበት ነበር፡፡

የወያኔን ጥንካሬ አንሮ ሰማይ እንዲያደርስ በተሰጠው ልዩ ተልዕኮ መሠረት፣ ወያኔ ሰውን ይቅርና ተራሮችን የሚያንቀጠቅጥ የማይጋፉት ባላጋራ ነው ለማለት ‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ›› የተሰኘውን ልብወለድ ጽፏል፣ አስጽፏል፡፡  ላንድ ቀን ቢተባበሩ ወያኔን ባንድ ቀን የሚጥሉትን አማራንና ኦሮሞን ለማፋጀት ደግሞ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› የተሰኘውን አደገኛ መርዝ ከበረከት ስምዖን ጋር በመተጋገዝ ቀምሟል፡፡ 

ዲትሪኽ በመጀመርያ ደረጃ የወንጀለኛው የናዚ ድርጅት አባል በመሆኑ ብቻ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በወንጀለኛው ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ በነበረበት ወቅት በነዛቸው እኩይ ትርክቶች (narration) ሳቢያ በኒዩርምቤርግ ችሎት (Nuermberg trials) ቁሞ (tried) በፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ተወንጅሎ፣ ሰባት ዓመት ተፈርዶበት ዘብጥያ ወርዷል፡፡

ፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ማለት ሰላማዊ ሰወችን ለመፍጀት ወይም ለማፋጀት ሲባል ሥራየ ብሎ የተፈጸመ ማናቸውም ዓይነት እኩይ ድርጊት ማለት ነው፡፡  ፀረሰበ ወንጀል እንደ ጦርነት ወንጀል (war crime) በጦርነት ወቅት ብቻ የሚፈጸም ወንጀል ሳይሆን፣ በጦርነትም፣ በሰላምም፣ በማናቸውም ጊዜ ሊፈጸም ይችላል፡፡  ፀረሰብ ወንጀልን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ወንጀሉ በፈጻሚው ቡድን (ወይም ድርጅት) መመርያ ውስጥ በይፋ ወይም በሕቡዕ የተካከተ በመሆኑ፣ ቡድኑ ወንጀሉን በይፋ ወይም በሕቡዕ የሚደግፈው ወይም ደግሞ የሚቸልለው (condone)  (ማለትም ቸል የሚለው ወይም አይቶ እንዳላየ የሚያልፈው) መሆኑ ነው፡፡

ወያኔ ከጽንሰቱ ጀምሮ አማራን በጠላትነት በይፋ ፈርጇል፡፡  የወያኔው ወዲ ገብረአብ ደግሞ በወያኔ ፖሊሲ መሠረት ጠላት ተብሎ የተፈረጀውን አማራን በኦሮሞ ለማስፈጀት ሥራየ ብሎ እኩይ ትርክት ተርክቷል፡፡  ይህ እኩይ ትርክት ደግሞ ባማራ ጥላቻ የቀወሱትን የኦሮሞ ጽንፈኞች ይበልጥ አቀውሶ አሳብዷቸዋል፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ እንደውም ጤዛ ነሽ፡፡ ስለዚህም በኦሮሞ ጽንፈኞች ለተጨፈጨፉትና ለተፈናቀሉት እልፍ አእላፍ አማሮች አንዱና ዋናው ተጠያቂ ወዲ ገብረአብ ነው ማለት ነው፡፡  በመሆኑም በፀረሰብ ወንጀል ተከሶ፣ በኢንተርፖል ታድኖ፣ ወደ ጦቢያ መጥቶ፣ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት፡፡

ጦቢያን በመሰለች የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochazka) መሠረታዊ ሐሳብ በሚያቀነቅኑ ምዕራባውያን ያላሰለሰ ጥረት ጎጠኝነት እንደ ወረርሽኝ በተስፋፋባት አገር ይቅርና፣ ጎጠኝነት በጽኑ ስለሚያስቀጣ ጎጠኝነትና ጎጠኞች ከሞላ ጎደል በከሰሙባቸው በምዕራባውያን አገሮች እንኳን፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የሚሄደው እስከተወሰነ ደረጃ ብቻ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል ታዳሚ በታደመበት ቲያትር ቤት፣ በውሸት እሳት ተነሳ ብሎ ኡኡ በማለት ግርግር ፈጥሮ ታዳሚውን ለጉዳት ይልቁንም ደግሞ ለሞት መዳረግ፣ በሞት የሚያስቀጣ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡

ወዲ ገብረአብ ደግሞ በወያኔ ፀራማራ ፖሊሲ መሠረት አማራን ጡት የሚሸልት፣ ፣ ማሕፀን የሚዘረክት፣ አጥንት የሚከተክት፣ በደም የሚፈትት ያረመኔወች አረመኔ በሚያስመስል ትርክት የኦሮሞ ጽንፈኞችን በተለይም ደግሞ ቄሮ ተብየ መንጋወችን መርዞ፣ እልፍ እእላፍ አማሮችን ለመፈናቀል፣ ለመጎሳቆልና ለእልቂት ዳርጓል፡፡  ይህን ባማራ ጥላቻ ያበደ እኩይ ግለሰብ በፀረሰብ ወንጀል ለመክሰስ፣ አንገቶች የተመተሩበት፣ ጦቶች የተቆረጡበት፣ ሆድ እቃወች የተዘረገፉበት የቡራዩ ጭፍጨፋ የቡርቃ ዝምታ መስታዋታዊ ነጸብራቅ (mirror image) መሆኑን መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡    

የፀረሰብ ወንጀል ሕግ የሚያገለግለው በነጮች ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣  የናዚ ፕሬስ መምርያ ሃላፊ ኦቶ ዲትሪኽ በእኩይ ሕትመቶቹ ተወንጅሎ ሰባት ዓመት ከተፈረደበት፣ ከዲትሪኽ ወንጀል ሰባት ጊዜ ሰባ በላይ የከፋ ወንጀል የፈጸመው የወያኔው ፕሬስ መምሪያ ሃላፊ ወዲ ገብረአብ ደግሞ የጁን ማግኘት አለበት፡፡  

ባርባጉጉ፣ በበደኖ፣ በጉራፋርዳና በመሳሰሉት የሰቆቃ ቦታወች የተከሰከሰው ያማሮች አጽም፣ በቡራየ የታረዱት የጋሞወች ጣዕረ ነፍስ፣ በቅርቡ ደግሞ በመላው ኦሮሚያ በጥቅምት 13 እና 14 በግፍ በገፍ የፈሰሰው የሁሉም ጦቢያውያን ደም፣  ወዲ ገብረአብን በፀረሰብ ወንጀል ተፋረዱልኝ እያለ በጦቢያውያን ሕጋቶወች (lawyers) ጆሮ ላይ ያለማቋረጥ ይደውላል፡፡  

የዚህ ጦማር ዋና ዓላማ ደግሞ የወዲ ገብረአብ አሰቃቂ ወንጀል አንዱን ጦቢያዊ ሕጋቶ ወይም ሕጋቲት አነሳስቶ በወዲ ገብረአብ ላይ ዶሴ እንዲከፍትበትና፣ ሌሎቻችን ደግሞ ለዶሴ ከፋቹ አቅማችን የሚፈቅደውን አስፈላጊውን እገዛ እንድናደርግ፣ መወርወር የምንችለውን ሁሉ እንድንወረውር ነው፡፡  

የወያኔው ዲትሪኽ የወዲ ገብረአብ ወንጀል ግልጽ ስለሆነ፣ ዶሴው ይከፈት እንጅ ለመዝጋት ጊዜ አይፈጅም፡፡  ወንጀለኛው ደብቁኝ፣ ደብቁኝ ሳይል፣ እዩኝ፣ እዩኝ እያለ ዶሴውን መክፈት ደግሞ የጁን የሚያገኝበትን ጊዜ ይበልጥ ያፋጥነዋል፡፡  የጦቢያ ሕጋቶወች (lawyers) ማሕበር ሆይ፣ አለህ?    

 

    መስፍን አረጋ

                mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic