>

ዝም አንልም! ዝምታ ምርጫችንም አይደለም!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዝም አንልም! ዝምታ ምርጫችንም አይደለም!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
በማህበረሰባችን ውስጥ ዝምታ ትልቅ ስፍራ አለው። ‘ዝምታ ወርቅ ነው’ ብሎም ያስባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዝምታ ይደግፋል፣ በዝምታ ይቃወማል፣ በዝምታ የጠላውን ገለል ያደርጋል፣ በዝምታ ያልወደደውን ያበራያል፣ በዝምታ ፍርሃቱን ይገልጻል፣ በዝምታ ያባልጋል፣ በዝምታ ያጀግናል፣ በዝምታ ያሞስናል፣ በዝምታ አገር ያዘርፋል፣ በዝምታ ሌቦችን ይቀጣል፣ በዝምታ ግፍን ያጸናል፣ በዝምታ ግፏንን ያጽናናል፣ በዝምታ ግፈኞችን ያበረታል፣ በዝምታ ይዋረዳል፣ በዝምታ አገርን ለአዋራጆች አሳልፎ ይሰጣል፣ በዝምታ መልሶ ይነግሳል። እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ በዝምታ መከራን እና ደስታን እያፈራረቀ የሚቀበል ሕዝብ መኖሩን እንጃ።
እኛ ግን ዝም አንልም። ጋዜጠኛ፣ የመብት ተሟጋች እና የሃሳብ አቀንቃኝ የሆነ ሰው ግን ዝም አይልም። ዝምታ የእኛ አማራጫችንም አይደለም። ጋዜጠኛ ዝም ካለ ጋዜጠኛ አይደለም። የመብት ተሟጋች ዝም ካለ እሱ እውነተኛ ተሟጋች አይደለም። የሃሳብ አቀንቃኙም እንዲሁ ዝም ካለ ችግር አለ ማለት ነው። ሁሌም እንጮኻለን። በተለይም አብላጫው የአገሪቱ ነዋሪ በደሉንም፣ ደስታውንም፣ ሃዘኑንም በዝምታ እና በአርምሞ ብቻ በሚገልጽበት አገር ነጋ ጠባ የሚጮኹት ጋዜጠኛው፣ የመብት ተሟጋቹ፣ የሃሳብ አቀንቃኙ እና ፖለቲከኞች ብቻ ስለሆንን ለጥቃት፣ ለነቀፌታ፣ ለትችት፣ ለመሳሳት፣ ለፍረጃ፣ ለእስር፣ ለዱላ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያም የተጋለጥን ነን። ቢሆንም ዝም አንልም። ዝምታ የእኛ አማራጭ አይደለም። ግፍ እየተፈጸመ፣ አገር በመንጋ እየታመሰ፣ አንባገነንነት ዳግም እያቆጠቆጠ ስናይ ዝም አንልም።
ትላንት ህውሃት የሰራችውን ወንጀል እና የመብት ጥሰት ስናጋልጥ ዘጠና በመቶ የሚሆነው የአገሬው ሰው ጸጥ፣ ለጥ ብሎ የግፍ እንቆቆውን ይጋት ነበር። እነ ዕርዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ዮናታን ተስፋዮ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ በቀለ ገርባ፣ ስዩም ተሾመ፣ አንዷለም አራጌ እና ሌሎች ሺዎች ሲታሰሩ እና ሲሰቃዩ ሚሊዮኖች ጎመን በጤና ብለው ተቃውሞ ይሁን ድጋፍ በዝምታ አርምሞ ተውጠው ከክፉው ሥርዓት ጋር ይካሄድ የነበረውን ትንቅንቅ እንደ ተወዳጅና ተከታታይ የቴለቪዥን ድራማ በጉጉት ይከታተሉ ነበር።
ድራማው ቀጥሏል፤ እኛም ጩኸታችንን ቀጥለናል፣ ለድጋፍ ሲሆን አደባባዩን የሚያጨናንቀውም ሕዝብ ንቁሪያው ሲበረታ ወደ አርምሞም እየተመለሰ ይመስላል። ዝም ያላችሁም ዝምታን ስበሩ፤ ለመብት የምትጮኹም ድምጻችሁን ከፍ አድርጉ። የዚች አገር መከራ ገና አላበቃም። ትላንት የአገዛዝ ሥርዓቱ እና ጀሌዎቹ ሊያሸማቅቁን ሞክረው አልተሳካላቸውም። ዜሬ ደግሞ አክራሪ ብሔረተኞች የምናነሳውን የመብት ጥያቄ ሁሉ በዘረኛ እና ወገንተኛ መነጽራቸው እያዩ ጩኸታችንን ሊያጣጥሉ እና እኛንም የዘር ከረጢት ውስጥ ሊዶሉን ይለፋሉ። አይሳካም።
ዝምታ ግን የእኛ የመብት ተሟጋቾች አማራጭ አይደለም፤ ዝም አንልም!
Filed in: Amharic