>

ኦዴፓ፤ ህውሃት የሄደበትን ቁልቁለት ባይጀምረው መልካም ነው! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኦዴፓ፤ ህውሃት የሄደበትን ቁልቁለት ባይጀምረው መልካም ነው!
ያሬድ ሀይለማርያም
በኦዴፓ የሚመራው የለውጥ ኃይል ህውሃት ያሰመረለትን የቁልቁለት መንገድ መመለሻው እሩቅ ስለሆነ ባይጀምረው መልካም ነው። ህውሃት ያሽመደመዳት ኢትዮጵያ ሌላ አሽመድማጅ ወይም አፋኝ ወይም የመድሎ ሥርዓት የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም። በተወሰነ ደረጃ በተግባር፤ በብዛት ደግሞ በንግግር የታጀበው የዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን የመታደግ ህልም እና ምኞት በድርጅታዊ ቅዠት እና በፓርቲዎች መካከል በሚታየው ፉክክር እየተደነቃቀፈ መንገዱን ሊስት የሚችልበት እድል እሩቅ አይደለም።
የለውጥ ኃይሉ በአንድ አመት ውስጥ ያከናወናቸው ብዙ መልካም ነገሮች በየቀኑ በሚፈጠሩና ልብ በሚሰብሩ አሳዛኝ ክስተቶች እና በመንግስት አካላት በሚፈጸሙ ጉልህ ስህተቶች ከወዲሁ ጥቁር ጥላ እያጠላበት ይመስላል። እርግጥ ነው ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ባሉባት እና ብሔረተኝነት ከፖለቲካ መድረክ መነታረኪያነት አልፎ የእርስ በርስ ግጭቶችን፣ የሚሊዮኖች መፈናቀልን እና ወከባን እያስከተለ ባለበት አገር ሁሉንም ሰው ሊያስደስት የሚችል ሥራ መስራት እጅግ ከባድ ነው።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ የመንግስት ስኬት እና ውድቀት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ እርምጃ የሚለካው በብሔር ሚዛን ስለሆነ ሁሉም ለእኔ ምን ተደረገ እንጂ ከእኔ ምን ይጠበቃል አይልም። ሌላው ሲያገኝ ለእኔም ይበጃል ብሎ የማሰብ ነገር የለም። ሹመትም ሆነ ሽረት፣ እስርም ሆነ ፍቺ፣ ልማትም ሆነ ጥፋት የሚለኩት በአገራዊ ሚዛን ሳይሆን በብሄር ሚዛን ሆኗል።
ከዚህ እውነታ ባሻገር ግን ለውጡን በሚመራው በኦዴፓ በኩል ከወዲሁ እየታዩ ያሉት ችግሮች ህውሃት አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጣበትን መንገድ እንድናስታውስ እያደረገን ነው። በሽግግር ወቅት የነበው ህውሃት/ወያኔ በተወሰነ ደረጃ ከሽግግሩ በኋላ ከነበረው ወያኔ ይሻል ነበር። ከምርጫ 1997 በፊት የነበረው ወያኔ በብዙ መልኩ ከምርጫው በኋላ ከነበረው የወያኔ አስተዳደር ይሻል ነበር። ሌላው ቀርቶ ከምርጫ 2007 በፊት የነበረው የኃይለማርም አስተዳደር ከምርጫው በኋላ የለየለት ጨፍጫፊ ሆኖ ለብዙ ወጣቶች ህልፈት እና ስቃይም ምክንያት ከሆነው የወያኔ መንግስት ይሻል ነበር።
ህውሃት/ወያኔ ከለውጥ ኃይል ወደ ከፊል አንባገነን፣ ከከፊል አንባገኔን ወደ ለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት፣ ከዚያም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፍኖ ወደሚገዛ ጨፍላቂ ኃይል የተቀየረው በሂደት ነው። ከመሰረቱም የዲሞክራሲ ባህል የሌለው ቡድን ስለነበር በሃሳብ ልዩነት በተገፋ ቁጥር የአፈና ማነቆውን እያጠበቀ ሄዶ ነው በስተመጨረሻ የለየለት 100% ጠርናፊ የሆነው። ኦዴፓ መራሹም የለውጥ ኃይል ይህን የቁልቁለት የአፈና መንገድ እንዳይጀምረው ማሳሰብም ሆነ ስጋታችንን መገለጽ ካለብን ጊዜው አሁን ይመስለኛል። የቁልቁለቱ መንገድ ከተጀመረ መመለሻ የለውም።
ድርጅቱን ወይም የለውጥ ኃይሉን ወደዚህ አቅጣጫ ሊገፉት የሚችሉ በርካታ ኃይሎች ዙሪያውን ያሉ ይመስላል። አንዳንድ ምልክቶችም ከወዲሁ እየታዩ መሆኑ የአደባባይ መወያያ ሆኗል። በጥቂቱ፤
+ የድርጅቱ እና አንዳንድ ባለሥልጣናቱ በተደጋጋሚ ወሳኝ በሁኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው እብሪት የተቀላቀለባቸው መግለጫዎች፤
+ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል እና ወከባ ማስቆም አለመቻላቸው፤
+  ቁልፍ በሆኑ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ምደባ ላይ ግልጽነት የጎደለው አካሄድ ከወዲሁ መታየቱ እና መድልዎ እየታየ መሆኑ አጋር ድርጅቶች ሳይቀሩ በገደምዳሜ መናገር መጀመራቸው፤
+ አንገብጋቢ የሆኑ እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አገራዊ ጉዳዮችን ችላ ማለት ወይም አቃሎ የማየት ዝንባሌ ተደጋግሞ መስተዋሉ፤
+ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጽሟቸውን የወንጀል ተግባራት በይፋ ከማጋለጥና አጥፊዎቹንም ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ የመሸፋፈን እና ተጠያቂ እንዳይሆኑ ከለላ የመስጠት፤
+ በተቃራኒው በሰላማዊ መንገድ የድርጅቱን አካሄድ የሚቃወሙ አካላት ላይ ዛቻ መሰንዘር፣ ሃሳባቸውን የመገልጽ እና የመሰብሰብ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት መፍጠር እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ችግር ሲፈጥሩ ችላ ብሎ ማየት፣
+ ፍትሕን ለፖለቲካ በቀል ከማዋል ባለፈ የመብት ጥሰት የፈጸሙ እና ተባባሪ በነበሩ ሰዎች ላይ ግልጽ የሆነ አቋም አለመወሰዱ። ከዚያም አልፎ ባለፉት አንድ አመት ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ችላ በማለት አገሪቱ በመብት ጥበቃ ወደር ያልተገኘላት አስመስሎ ማቅረብ። ለዚህም በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ በመብት ጥሰት ስሟ አልተነሳም ብሎ በቡራዩ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን መሸፋፈን፤
+ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በደህንነት ስጋት እና መኖሪያቸው ፈርሶ በየጫካው እና በየሜዳው ፈሰው ለእርሃብ እና እንግልት በተዳረጉበት፣ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በአገሪቱ በርካታ ክፍሎች ተከስተው ዜጎች የመንግስት ያለህ እያሉ በሚማጸኑበት ወቅት ከመንግስት በኩል ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ አለማግኝት እና መንግስት በሌሎች ግዙፍ የአገር ሃብት በሚጠይቁ የገጽታ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮሩ፤
እና ሌሎች በርካታና ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ችግሮችን ለመጥቀስ ይቻላል።
ኦዴፓም ሆነ ሌሎቹ አጋር የለውጥ ኃይሎች የአንድ አመት ቆይታቸውን በመሞጋገስ እና በየአዳራሹ ከመጨፈር ባለፈ የመጡበት መስመር ህውሃት ካሰመረው እና ከመጣበት የቁልቁለት ጉዞ የራቀ መሆኑን አጽንተው ቀጣዩ ጉዟቸውን ከወዲሁ ቢያቀኑም መልካም ነው። እንደ እኔ እምነት አሁንም ይችን አገር ለመታደግ ኦዴፓ እንደ መሪ ድርጅት እና ሌሎቹም እንደ አጋር ድርጅት እድሉ በጃቸው ነው። የአገሪቱን ፖለቲካ በጥንቃቄ ከያዙት እና የህውሃትን ስህተት ላለመድገም ከተጠነቀቁ ያሻግሩናል፤ ህውሃት ያራባውን የስግብግብነት እና የጥበት ልክፍት ተሸክመው ወደፊት ለመቀጠል ካለሙ ግን አዘቀት ውስጥ ተሰንቅረን እንቀራለን።
መልካሙን ሁሉ ለኦዲፓ እና ለለውጥ ኃይሉ እመኛለሁ!
Filed in: Amharic