>

የምልመላው መመዘኛ (ከይኄይስ እውነቱ)

የምልመላው መመዘኛ

ከይኄይስ እውነቱ

ሰሞኑን የወያኔ (ኢሕአዴግ) መከላከያ ተቋም ወታደሮችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ተመለከትኹ፡፡ ከመመዘኛ መሥፈርቶቹ አንዱ ‹‹የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት የሚቀበሉ›› ይላል፡፡ ወዲያው ወደ አእምሮዬ የመጣው ሃሳብ ኢትዮጵያ ‹ሕገ መንግሥት› አላት ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ መሥፈርቱ እንግዳ ሆኖ አይደለም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የዚህን መዘዘኛ ሰነድ ምንነት መናገር ተገቢ መሆኑን ስለማምን እንጂ በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት እንደሌላት በጽኑ የማምን መሆኔን ከዚህ ቀደም ባቀረብኳቸው አስተያየቶች ገልጬአለሁ፡፡ 

የጋራ ታሪክ÷ እሤቶች÷ባህልና ትውፊትን መሠረት አድርጎ በተዘጋጀ፣ የዛሬውን ፍላጎቱን፣ የወደፊት ምኞቱን የያዘ፣ ሕዝብ ባፀደቀው፣ ተግባራዊነቱ በተረጋገጠ እና እንደ አስፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚሻሻል ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የሚመሩ አገሮች ዜጎች ሕገመንግሥታቸውን መቀበል ብቻ ሳይሆን ታማኝነታቸውንም ጭምር ይገልጹለታል፡፡ ይሁን እንጂ የዜጎችን ሉዐላዊነት ወይም የአገር ባለቤትነት ያልተቀበለ፣ ዘረኝነትን፣ ጥላቻንና መለያየትን ተቋማዊ ያደረገ የወያኔ ሰነድ በየትኛውም መመዘኛ ርእሰ ሕግጋት (ሕገ መንግሥት) የሚለው ስያሜ ሊሰጠው አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ በጉልበት የተቀመጡ የወያኔ ባለሥልጣናት ይህን ሰነድ አንዱ ለሌላው ሲያስረክብ ታዝባችኋል? በዚህ ረገድ የመጨረሻውን ድራማ የተወኑት ኃይለማርያምና ዐቢይ ናቸው፡፡ ያሳፍራል÷ ያሸማቅቃል፡፡ በእውነት የመጨረሻው ያድርግልን፡፡

ወያኔ ትግሬና የእጁ ፍጥረቶች የሆኑት ሦስቱ ሎሌዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከሥተው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከማዋረዳቸው በፊት በዘመናት ሂደት በጋራ ታሪክ፣ በጋራ ባህል፣ በጋራ ትውፊት፣ በአብዛኛው የአብርሃማዊ እምነቶች (ይሁዲነት፣ ክርስትና እና እስልምና) ተከታዮች በጋራ የሚኖሩባት፣ በታወቀ የጋራ መልክዐ ምድር የኖሩና የሚኖሩባት፣ በሰላሙ ጊዜ በጋብቻ÷ በንግድ ወዘተ. በችግር ጊዜ በጦርነት÷ በረሃብ/በችጋር÷በፍልሰት ወዘተ. መስተጋብር ፈጥረውና አንድ ብሔራዊ ሥነ ልቦና አዳብረው፣ አኩሪና ከሌለች ኅብረተሰብ የሚለያቸው ሰፊ ማኅበራዊ ጥሪት አካብተው የኖሩባት/የሚኖሩባት ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ኢትዮጵያዊ የሚባል ሕዝብ እንደሌለ ቈጥሮ፤ ክልል የሚባል የመለያየት አጥር አበጅቶና  ‹ዘጠኝ አገሮችን› በጐሣና ቋንቋ ከፋፍሎ የፈጠረ ሰነድ፣ ማነስና መኮሰስ የፈለጉ የጐሠኞች ፈቃድ መፈጸሚያ ተራ የመንደር ውል እንጂ በጥንት ሥልጣኔ ተካፋይ የነበረ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ በተለይም በጥቁር ሕዝብ ዘንድ እንደ ፈርጥ የሚያበሩ ሁለት ታላላቅ ድሎች – ፀረ ቅኝ ገዥነት በዓድዋ፣ ፀረ ፋሺስትነት በማይጨው – ያስመዘገበ እና አሁንም በአፍሪቃም ሆነ በተቀረው ዓለም ተገቢውን ሥፍራ እንዲኖረው የሚፈልግ ታላቅ ሕዝብ ሕገ መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡ በጭራሽ!!!

ላለፉት 27 ዓመታት በወያኔ ትግሬ፣ ከዛም ወዲህ ባለው ዓመት ተመንፈቅ የቀረበ ጊዜ በአዲሶቹ ተረኛ ወያኔዎች (ኦሕዴድ/ኦነግ) በሁለንተናዊ መልኩ አገራችን ለተደቀነባት የህልውና ፈተና ከመሠረታዊው ምክንያቶቹ አንዱና ዋናው ወያኔና ኦነግ የተከሉት የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ከመግቢያው አንቀጽ እስከ መዝጊያው በዘረኝነት/በጐሣ አስተሳሰብ የተበከለው ይህ ሰነድ ሦስቱን የመንግሥት ዘርፎች (ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ) ጨምሮ የአገራችን የአስተዳደር ግዛቶች እስከ ታችኛው የቀበሌ አስተዳደር፣ የአገር መከላከያ÷የአገርና የሕዝብ ደኅንነት÷የፖሊስ ተቋማት፣ የ‹ፖለቲካ ማኅበራት›፣ የሲቪል ሰርቪስ (በብቃትና በችሎታ /merit based/ የተመሠረት ሳይሆን ለቅጥር ዋናው መሥፈርት የጐሣ ማንነት ሆኗል)፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ፣ የሙያና የሕዝብ ማኅበራት (ለአብነት ያህል የሠራተኞች÷የመምህራን፤ የሴቶች÷የወጣቶች) የንግድ ተቋማት (ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት)፣ ሌሎች አደረጃጀቶች በሙሉ በዘረኝነት አመለካከት እንዲቃኙና እንዲሠሩ ያደረገ ነው፡፡ ዛሬ ባገራችን አጥንት/ጕልጥምት ወይም ደም የማይቈጠርበት የኑሮ መስክ ያለ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ በውይይትና ክርክር ሽፋን መድረክ ያገኙ ባለጊዜዎች ሺህ ዓመት ወደኋላ እየጎተቱን የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይው ወይም ገንዘቡ ይመስል በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ለጐሣ/ነገድ ማንነት ካልሰገዳችሁ በማለት አንሰው ሊያሳንሱን÷ ቀልለው ሊያቀልሉን ይጥራሉ፡፡ የሰውን ልጅ ኅሊናና አእምሮ ሰልበው በስስ ስሜቱ እየተጫወቱ ለሥልጣንና ንዋይ ፍትወታቸው በመንጋነት መሣሪያ ለማድረግ እንጂ የጐሣ/ነገድ ከረጢት ውስጥ ካልገባህ ብሎ ማስገደዱን ምን አመጣው?  በራሱ ማሰብ ያቆመ ዘረኛ መንጋ ኹላ!!! ሰውነታቸውን የጣሉ ድውያን ከኛ ጋር አብራችሁ ዕበዱ ሲሉን ማበድ አለብን እንዴ? ናይጄርያዊ፣ ጋናዊ፣ አሜሪካዊ፣ ፈረንሳዊ፣ ጃፓናዊ፣ ቻይናዊ፣ ኢራናዊ፣ ኦማናዊ ማንነት እንዳለ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ማንነት ትናንትም ዛሬም አለ፡፡ ለወደፊቱም ይኖራል፡፡ ብሔራዊ ማንነት ካገር ህልውና ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማለት ነው፡፡ ዜግነት ደግሞ ባጭሩ አገላለጽ የአገር ባለቤትነት ማለት ነው፡፡ መቼም ልማድ ክፉ ነውና ዛሬ ሳር ቅጠሉ መደበኛም ሆኑ ኢመደበኛ ብዙኃን መገናኛዎችን ጨምሮ ‹ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች› የሚል እንቶ ፈንቶ ከአፉ የማይለይ ሆኗል፡፡ ወያኔ የረጨው መርዝ ውጤት፡፡ ምሁራን ነን የሚሉትም የዚህ ልማድ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በስታሊን ከተለከፉትና ያለ ዓውዱ ኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ካሰቡት የ‹ያ ትውልድ› ዐወቅን ባዮች ጀምሮ ሆን ብሎ ለፖለቲካ ዓላማው ማስፈጸሚያ መሣሪያ ካደረገው ወያኔ (የአሁኑን አገዛዝ ጨምሮ) እና በመንጋነት እስከሚከተለው የአሁኑ ትውልድ ድረስ በዚህ የድንቁርና አስተሳሰብ አገር እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያዊ ‹ብሔርተኝነት› አለ ወይ የሚል የሰነፎች ጥያቄም ባልሰማን ነበር፡፡ ብሔርተኝነት ምንድነው? ለነዚህ ዓይነት ግለሰቦች ‹ብሔር› ማለት ጐሣ/ነገድ ስለሆነ፣ ብሔራዊ ማንነት የሆነውን ኢትዮጵያዊነት በዘረኛ አስተሳሰብ ከጐሣ/ነገድ ጋር ሊያዛምዱት ይፈልጋሉ፡፡ ተጣሞ ያደገን ዛፍ ማቃናት አስቸጋሪ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ፅንሰ ሃሳቡ ሳይኖር ስያሜው ከየት ይመጣል? ባዕድ ነገር ያለቦታው መደንቀር ካልሆነ፡፡ ዘረኞች የሠለጠኑበት ዘመን ስለሆነ ለነሱ እንደ አዲስ ግኝት ነው የሚያዩት፡፡ ምስኪኖች!?

በየትኛውም የመንግሥት ተግባር ለመሠማራት ይህንን የወያኔ ሰነድ መቀበል እንደ መሥፈርት ማስቀመጥ ማለት ዘረኝነትን/ጐሠኝነትን መቀበል በመሆኑ፣ ይህ አጥፊ ሰነድ በኢትዮጵያ ምድር እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ የግዛት ሉዐላዊነቷንና ዳር ድንበሯን፣ የዜጎቿን ደኅንነትና ሰላማዊ ሕይወት ባጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብር የአገር መከላከያ፣ የአገርና የሕዝብን ደኅንነት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ የፖሊስ ኃይል ሊኖራት አይችልም፡፡

በተለያዩ አስተያየቶቼ ደጋግሜ እንደገለጽኩት ይህንን የወያኔ ሰነድ የመቀበል የሞራል ግዴታ የለብኝም፡፡ ሰነዱ ባብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት (legitimacy) አለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን  የዘረኝነት/የመንደርተኝነትን አስተሳሰብ ሕጋዊ ቅርፅ የሰጠ ነው፡፡ ሆኖም ኃይል ለጊዜው ከአገዛዙ ጋር ስለሆነ መሥፈርቱን በጉልበት ሊያስፈጽመው ይችላል፡፡ የኢትዮጵያውያን ትግል መሆን ያለበት ግን ተደራጅቶ የወያኔን ሰነድ በአዲስ ርእሰ ሕግጋት መቀየርና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚታይበትን ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ የዚያን ጊዜ በሥጋት የምናየው ሳይሆን አለኝታ የሚሆነን፣ የምናፍርበት ሳይሆን የምናከብረው ኢትዮጵያዊ ቁመና ያለው የአገር መከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል ይኖረናል፡፡

Filed in: Amharic