>

ለገዥው መደብ ፅንፈኛ ሊሂቃን ጥሪ (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ለገዥው መደብ ፅንፈኛ ሊሂቃን ጥሪ

 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

በይቅርታ እንሻገር፥ በፍቅር እንደመር ለሚለው ወንድማችሁ ውጋት እየሆናችሁ፥ ዛሬ ላይ ሰው እንደ እንስሳ ሲጨክን እንድናይ ሆነ። አሁንም እየተሰበሰባችሁ “የኦሮሞ አንድነት” እያላችሁ ለይስሙላ አስሬ ከምትፈራረሙና ልባችንን ከምታደርቁ፥ “የኢትዮጵያ አንድነት” ብላችሁ የአኖሌን የጡት መቁረጥ የጠብ አውልት ለፍቅር በማፍረስ ጀምሩና አቃፊ ለመሆን ዳዴ በሉ።  ያኔ ኦሮሞ ይከብራል፥ በመልካም ስምና ፍታዊነት እንደ ማንነቱ ይገዛል። የተጨቆነው ደጉ ኦሮሞ ሕዝብ አሁን በመንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ሲገዛ፥ ተፈውሶ ፈውስን ለመላው ኢትዮጵያ ሊያመጣ አምላኩን የሚፈራ ሆኖ ሳለ፥ እናንተ በአስተሳሰባችሁ ገና ነፃ ስላልወጣችሁ፥ ትላንት በረከት ሆናችሁ፥ ዛሬ ወደ መርገምነት ተቀይራችዋልና፥ አንገታችሁን ማደንደን ትታችሁ ተመለሱ። 

 

ኢትዮጵያን እንበትናለን ብላችሁ፥ ኦሮሞ መግዛት አይችልም እያስባላችሁ ነው። የሚገዛ በመጀመሪያ አቃፊ መሆን አለበት።  እናንተ እንደ ሕፃን ልጅ ሁሉ የእኔ ነው እያላችሁ፥ አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ሆናችሁ። የኦሮሞ ልጅ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ሲሰበስብ ከስር ስሩ ተከትላችሁ ትበትናላችሁ።  ሲተክል ትነቅላላችሁ። ኦሮሞ መንገሱን ሳይሆን የፈለጋችሁት፥ እናንተ ራሳችሁ መንገስ ነውን? በናንተ ቤት ኢትዮጵያን ስትወጉ፥ ትልቁን የኦሮሞን ሕዝብ ስም ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እያደማችሁ ነው። ወገናዊነትን እያቀነቀናችሁ ዛሬን አታላችሁ ትኖሩ ይሆናል፥ ግን ነገ የታሪክ ጥላሸት ሆናችሁ እንዳትታሰቡ እፈራለሁ።

 

አሁንም ጊዜ ሳያልፍ የኦሮሞ መፍትኤ ሁኑ።  እንዴት ብትሉ ሽማግሌ በመሆን ነው። እናንተን ለመመለስ ወደ እናንተ የሚቀርብ ተስፋ የማይቆርጥ እንደ እኔ ያለ ጉደኛ ብቻ ነው።  ምክንያቱም እናንተ እርቅ ሳይሆን ጠብ ትርፋማ ንግድ ሆኖላችዋልና። ግን ይህ ንግድ መጨረሻው በኦሮሞ ሕዝብ መተፋት እንዳያመጣባችሁ ንቁና ሽማግሌ ሁኑ።  ሽማግሌ ስትሆኑ በመጀመሪያ እናንተ ራሳችሁ በአጭር ንግስና ዘመናችሁ በሕይወት እያላችሁ ክፉ ዘር በመዝራታችሁ በምድራችን ስለታየው ሰቆቃ ይቅርታ ጠይቁ። ከዚያ የሞቱት የገዥ መደብ ሥር ተበደልን ስለምትሉት ሁሉ፥ እኛ ሕያዋን የሆንነው ለምድራችህ ፈውስ እንዲመጣ በሞቱት ሰዎች ፈንታ ቆመን ይቅርታ እርስ በርስ እንጠያየቃለን። ትላንት የበደሏችሁንና በሕይወት ያሉትንማ በሚያስገርም ፍጥነት ይቅርታ ሳይጠይቋችሁ፥ ወዳጅነት ፈጥራችዋል አሉ።  

 

ለኢትዮጵያ መዳን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!

 

Email: ethiostudy@gmail.com

Filed in: Amharic