>

አባቶቻችን «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ ምን ማለታቸው ነበር? (አቻምየለህ ታምሩ)

አባቶቻችን «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ ምን ማለታቸው ነበር?
አቻምየለህ ታምሩ
የኦነግ ፕሮፓጋንዲስቱ አሕመዲን ጀበል በሃይማኖት ስም የሚደርታቸውን የኦነግ የፈጠራ ትርክቶች እያሰራጨ  የሚያሳስታቸውና በአገራቸው ላይ እንዲነሱ ያደረጋቸው ተከታዮቹ  አባቶቻችን “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” በማለት ሲገልጹ የኖሩትን አባባል ኢትዮጵያ ሌላ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የማይኖርባት ወይም የኢትዮጵያ መንግሥት የክርስቲያኖች ብቻ እንጂ የሙስሊሞች ድርሻ እንዳልነበረበት አድርገው ሲያስተጋቡ ይሰማሉ።
“ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” የሚለው የአባቶቻችን አባባል እውነት  በኢትዮጵያ ሌላ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የማይኖሩባት ወይም የኢትዮጵያን መንግሥት የክርስቲያኖች ብቻ ማለት ቢሆን ኖሮ  ኢትዮጵያ በየዘመኑ በመጡት መንግሥቶቿ እየተዳደረች ስትኖር እስልምና ገብቶ ተከታዮቹን አያበዛም ነበር። የአሕመዲን ጀበል ተማሪዎች ኢትዮጵያ በየዘመኑ በመጡት መንግሥቶቿ በምትተዳደርበት ወቅት እስልምና ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ተከታዮቹን እንዴት እንዳበዛ ሲናገሩ እየዋሉ  “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት”  የሚለውን  አባባል  በኢትዮጵያ ሌላ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የማይኖሩባትና  የኢትዮጵያን መንግሥትም  የክርስቲያኖች  መንግሥት ብቻ ማለት እንደሆነ አብዝተው ሲያስተጋቢ ሲውሉ ኢትዮጵያ የእስልምና ጸር ናት በተባለበት ዘመን እስልምና በመንግሥትነት በተሰየመባቸው አገራት  ውስጡ  ይገዙ የነበሩ የሙስሊም መንግሥታት በስራቸው ይኖሩ በነበሩ ክርስቲያን ዜጎቻቸው ላይ ያካሄዱትን ጥቃትና  ፈቅደውላቸው ስለነበረው  መብት ግን አንዳች የሚነግሩን ነበር የለም።
በእውነቱ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” ማለት ኢትዮጵያ የክርስቲያን ብቻ ናት፣ ለክርስቲያኖች ብቻ የተከለለች (reserve) ደሴት ናት ማለት አይደለም። አባቶቻችን «ኢትዮጵያ በእስልምና ባሕር የተከበበች የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ
ከኢትዮጵያ ተነስተው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ድረስ በየአገሩ የነበሩት የሚያውቋቸው ገዳማት፣ የሚያርፉባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ የሚስተናገዱባቸው ደብሮችና የክርስቲያን ቤቶች በእስልምና ጎርፍ በየጊዜው እየተመናመኑ ሲሄዱና ሲጠፉ፣ ፍርስራሻቸውን እያዩ ሲያልፉ የተሰማቸውን መከበብና የተፈጠረባቸውን ስጋት ለመግለጽና    በኢትዮጵያ ዙሪያ ካሉት ሀገሮች አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ክርስቲያኖች እንደቀሩ፣ በተቀረው አካባቢ የነበሩ ክርስቲያኖች ግን እንደጠፉና እንደተወገዱ እንጂ ኢትዮጵያ የክርስቲያኖች ብቻ መኖሪያ ናት ማለት አይደለም። ባጭሩ «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» የሚለው አባባል የሚገልጸው አካባቢያዊ አውድን ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ አካባቢ ይገኙ የነበሩ የክርስቲያን ይዞታዎች [Presences] በሙሉ ጠፍተዋል። ክርስቲያኖች   በሶማሊያ ምድር በስፋት ይኖሩ ነበር፤ ይህ የታሪክ እውነት ከሶማሊያ ተቆፍሮ በወጣው የክርስቲያኖች ጥንታዊ ፍርስራሾችና ቅርሶጭ ተረጋግጧል። ሪቻርድ በርተን የተባለው አውሮጳዊ እ.ኤ.አ. በ1854 ዓ.ም. የዛሬውን ሶማሊያ አካባቢ ከጎበኘ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1856 ዓ.ም. ባሳተመው «First Footsteps in East Africa, or an Exploration of Harar» መጽሐፉ ከገጽ 127-129 እንደገለጸው Warsangeli የሚባለው የሶማሌ ጎሳ አባላት በሞቱ ጊዜ በመቃብራቸው ግርጌና አናት ላይ ከድንጋይ ወይም ከእንጨት የተጠረበ መስቀል የማድረግ ባህል እንዳላቸው ከነመስቀሉ ሥዕል በመጽሐፉ አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪ Sanaag በሚባለው የሶማሌ ክልል ውስጥ ያገኛቸው የሶማሌ ጎሳዎች ጥንት ክርስቲያን በነበሩ ጊዜ ያመልኩበት የነበረን የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ እንዳሳዩት ሪቻርድ በርተን በመጽሐፉ ጨምሮ ነግሮናል። ሶማሊያ ውስጥ ስለነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎችን ማንበብ የሚሻ ቢኖር Ben I. Aram እ.ኤ.አ. በ2003 ዓ.ም. Africa Journal of Evangelical Theology ላይ “Somalia’s Judeo-Christian Heritage: A Preliminary Survey” በሚል ያሳተመውን ጥናት ይመልከት።
ዶክተር ዐሊ አብዲራህማን ኸርሲ እ.ኤ.አ. በ1977 ዓ.ም. በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ “The Arab Factor in Somali History: The Origins and Development of Arab Enterprise and Cultural Influences in the Somali Peninsula” በሚል ባቀረበው የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱ፣ የ10ኛ እና የ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዐረብ ተጓዦች የመዘገቧቸውን የታሪክ ማስረጃዎች በመጥቀስ ገጽ 117 ላይ፡- “Tenth and eleventh century Arab sources all describe Zaila as an Abyssinian Christian city which traded peacefully with the Yamani (sic) ports across the Red Sea.” በሚል ካቀረበው የዛሬው ምዕራብ ሶማሊያ የክርስቲያን ምድር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ የሶማሌ ክርስቲያኖች ዛሬ ጠፍተዋል።
የሐዋርያት ስራ ምዕራፍ  አንድና ሁለትን ያነበበ ሁሉ  በኢትዮጵያ ዙሪያ በነበሩ አገሮች  ይኖሩ የነበሩት በእስልምና ጎርፍ የጠፉ ክርስቲያኖችን ናውቃል። በየመን የነበረው ክርስትና እና ክርስቲያኖች ጠፍተዋል። በሕንድ ውቅያኖስ እንደነ ሰኮራ ደሴቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ጠፍተዋል። ዛሬ ኢሚሬት በሚባለው ምድር ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ጠፍተዋል። በኩዌት የነበረ ክርስትና ጠፍቷል። በሱዳን የነበረው ክርስትና ጠፍቷል፣ የእምነቱ ተከታይ ኢምንት ሆኗል። በነቅዱስ አውግስቲን ሀገር አልጀሪያ፣ በነ አትናቲዎስ ሀገር ግብፅ ውስጥ የነበረው የክርስትና መንግሥት ጠፍቷል። ሱዳን የክርስቲያኖች ሀገር ነበር። በኑቢያ ክርስትና የቀረው የነገሥታቶቹ ወራሾች ከሙስሊም ጋር ተጋብተው ሃይማኖት በመቀየራቸው የተነሳ ነው። የጥንቶቹ ክርስቲያን አባቶቻችን  እየሩሳሌም ለመሳለምና ለመምጣት በሱዳንና ግብጽ  በገዳም፣ በቤተክርስቲያንና በምዕመናን ቤት  እያደሩ ነበር የሚመላለሱት። በመርከብም ቀይ ባሕርን የሚሻገሩት፣  በአረቢያና በየመን  ምድርም እንደዚያው ነበር የሚያደርጉት። አሁን ግን በመሀከሉና በዙሪያው ባለው ቦታ ሁሉ ክርስቲያን የሚባል ሕዝብ የሌለው የሙስሊም ባሕር ኾኗል።
«ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ማለት አንድ አካባቢ በውኃ ቢጥለቀለቅ በመሀል ያለው በውኃው ያልተጥለቀለቀው ቦታ ማለት ነው። የክርስቲን አካባቢ የነበረውን የዓለም ክፍል ያጥለቀለቀው ባሕር ደግሞ እስልምና ነው። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ክርስትና በእስልምና መስፋፋት ምክንያት በእስልምና ባሕር መሀከል የሚገኝ ደሴት ኾኗል ማለት ነው። አባቶቻችን «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲሉ ይህንን ማለታቸው ነው እንጂ ኢትዮጵያ ለሌላው ቦታ የሌላት፣ ለሌላው መኖሪያና መተዳደሪያ የምትነፍግ፣ ለክርስቲያኖች ብቻ የተከለለች (reserve) ደሴት ናት ማለታቸው አይደለም።
ባጭሩ «ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» የሚባለው ነገር ሲነሳ ታሪካዊና አካባቢያዊ አውዱ (Context) ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። አባባሉ በኢትዮጵያ ዙሪያ ባሉ አገሮች ማለትም በግብፅ፣  በኑብያ/ሱዳን፣  ዘይላና ሱማሌ በኤርትራ፣ በየመን ሁሉ ከእስልምና መምጣት በፊት ክርስትና የነበረባቸው ቦታወች የነበሩ በመሆናቸው  ደሴትነቱን ያመጣው የእስልምና እስከ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታወች ግርጌ ድረስ መስፋፋቱ ነው።
«ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት» ሲባል በእስልምና ጎርፍ ምክንያት መላው የባሕረ ሰላጤ ሀገራት፣ መላው ምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢው ይኖር የነበረው ክርስቲያን በሙሉ ጠፍቶ ብቻዋን ሳትጥለቀለቅ የተረፈች የክርስቲያኖች መገኛ ናት ማለት ነው። ደሴት የሚለው ቃል ትርጉሙ ካልጠፋብን በስተቀር የጥንት ክርስቲያኖች መገኛ የነበረው ከካይሮ እስከ ዛንዚባር፣ ከኑቢያ አንስቶ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ያለው አካባቢ በእስልምና ባሕር ተጥለቅልቆ በመሀል ላይ ሳትጥለቀለቅ የቀረችው ብቸኛዋ የክርስቲያኖች መገኛ ሀገር ኢትዮጵያ፣ «የክርስቲያን ደሴት» መባሏ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ?
እንደ አሕመዲን ጀበል ዓይነት ኦነጋውያን በኢትዮጵያ ዙሪያ የነበሩ የጥንት ክርስቲያን ሕዝቦች በእስልምና ባሕር ሙሉ በሙሉ ሲጥለቀለቁ በመሀል ሙሉ በሙሉ ሳትጥለቀለቅ የቀረችውን የክርስቲያኖች መገኛ ኢትዮጵያን «የክርስቲያን ደሴት ናት» ይሏታል በማለት በደረታቸው የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎቹ አባባሉን የኢትዮጵያ እስላሞች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲቆጠሩ ስለመኖራቸው እንደማስረጃ ያቀርበዋል። ኾኖም ግን እስላሞች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው የመምረጥና የመመረጥ መብት የተከለከሉበትን፣ የካቢኔ ሚኒስቴር እንዳልነበሩ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሕገ መንግሥትም ኾነ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ሕግ አንድ ሰው ሙስሊም ስለኾነ ይህንን ማድረግ አይችልም የሚል የተጻፈ አንድም ክልከላ ማቅረብ አይችልም። እነአሕመዲን የኢትዮጵያ እስላሞች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው ይታዩ የነበሩት ብለው ሲደርቱ «ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛ ዜጋ ከነበሩ ለምንድን ነው ሌሎች የኢትዮጵያ ዜጎች ያገኙት የነበረው ጥቅም (right) የነበራቸው? ምን የተቀነሰ የዜጋ ጥቅም (privilege) አላቸው?» ብሎ የጠየቃቸው ሰው የለም!
Filed in: Amharic