>

"እኛ በህይወት ያለን ሁላችን "የፍትህ ያለህ" የማለት ሞራላዊ ግዴታ አለብን!!!" (ዶ/ር ኤርሴዶ ሌዲቦ)

“እኛ በህይወት ያለን ሁላችን “የፍትህ ያለህ” የማለት ሞራላዊ ግዴታ አለብን!!!”
ዶ/ር ኤርሴዶ ሌዲቦ
~~
የአብይ መንግስት ወገኑን በግፈኞች በተነጠቀው ህዝብ ለቀረበለት የፍትህ ጥያቄ መልሱ የሞቱትን ሰዎች ብሄር መቁጠር ሆኗል። እጅግ አሳፋሪ ነው። መልዕክቱ “እንኳን እናንተ 20 የሞተባችሁ፣ 8 የሞተባችሁ… ወዘተ ይቅርና 50 ሰው የሞተበት ኦሮሞም ምንም አላለም” እንደማለት ነው።
~~
ሲጀመር “ነፍጠኛና ዶርዜ” እየተባለ ቤቱ ውስጥ የተቃጠለው፣ በድንጋይ የተቀጠቀጠውና በገጀራ የተቆራረጠው ኦሮሞ ሊሆን የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። ሲቀጥል በኦሮሞ ክልል ውስጥ “ጃዋር ተከበበ” ብሎ ኦሮሞን የሚያጠቃ ሌላ ሃይል የለም። ኦሮሞን የሚያጠቃ የጃዋር አፍቃሪ ከየት መጥቶ ነው? ለሰሚም ግራ የሆነ ነጭ ውሸት ነው ጠ/ሚሩ የተናገረው።
~~
“50 ኦሮሞ ሞተ” የተባለውን ቀልድ እንተወውና በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ብሄሮች ማን ማን እንደሆኑ ግን ተለይተዋል (ናዝሬት ላይ ተቀጥቅጦ የተገደለውን #ትግሬ ሳይጨምር)። እስካሁን ሞተ ያልተባለው አፋርና ሶማሌ ነው። የአፋሩን ባናውቅም የሞቱ የሶማሌ ክልል ልጆች እንዳሉ ግን እናውቃለን። ዞሮ ዞሮ የጠ/ሚሩ አሃዝ ሌላ ዳፋን የሚያስከትል ነው። “ኦሮሞ በክልሉ እንዴት በመጤ ይገደላል?” የሚል አጀንዳ ይዞ የሚያራግብ ሌላ የውሸት ተቀጥላ ሃይል ይነሳል። ከዚያም በግጭቱ ሳቢያ ሞቱ ተብለው ብሄራቸው የተጠቀሱ ወገኖች ታርጌት ተደርገው ለሌላ እልቂት ይዳረጋሉ። ሌላ ጭፍጨፋ፤ ደግሞ ሌላ ውሸት!!!
~~
እኛ ጥያቄያችን የብሄር ሥብጥር አይደለም። ለአንድ ግለሰብ (ጃዋር መሃመድ) ዝናና ክብር ተብሎ 86 ንፁሃን የተጨፈጨፉበት አሻጥር ወደ ህግ እንዲቀርብ ነው። የንፁሃንን ጡት ቆርጦ፣ አንገት በሜንጫ ቀልቶና ቤት ዘግቶ አቃጥሎ 86 ነፍስ ያጠፋው ድርጊት ትክክለኛውን ቅጣት እንዲያገኝና ይህ ድርጊት ካሁን በኋላ እንዳይደገም አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ነው። መንግስት ነኝ የሚል አካል ይህን የማረጋገጥ ሃላፊነት ነበረበት። ነገር ብሽሽቅ ውስጥ እንዳለ አንድ ተራ ግለሰብና መንግስታዊ ሃላፊነት እንደማይሰማው ሰው የፍትህን ጥያቄ በብሄር ስብጥር አዳፍኖ ለማለፍ መሞከር ፍትህን አለማወቅን፣ የአንድ ብሄር ወገንተኝነትን ወይም ለሰው ህይወት ክብር ማጣትን ያመለክታል። ይህን የመሰለ አካል መንግስቴ ነው ብላ የሾመች ሃገር ብዙ ጣጣ አለባት።
~~
ስለሆነም እኛ በህይወት ያለን ሰዎች በሙሉ ብሄር ስብጥር ውስጥ ሳንገባ አንድ ላይ “የፍትህ ያለህ” ማለት አለብን። መንግስት በብሄር ስብጥር አስታኮ ሊያልፈው የፈለገውን የፍትህ እጦት ዝም ብንል ዞሮ ዞሮ የምንሰቃየው እኛው ራሳችን ነን።
ስለዚህ አንድ ላይ ስለ ፍትህ እንነሳ!!!
Filed in: Amharic