>

"መንግስታዊ አጀንዳ ማስቀየሪያ፣ የራስን ወንጀለኛ መሸፋፈኛ፣ አማራን መከፋፈያ ሴራ ሊቆም ይገባል!!!" (ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ)

“መንግስታዊ አጀንዳ ማስቀየሪያ፣ የራስን ወንጀለኛ መሸፋፈኛ፣ አማራን መከፋፈያ ሴራ ሊቆም ይገባል!!!”
 
ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ
“ለእኔ የዛሬ 10 ሰዓቱ መግለጫ የድራማው ሶስተኛ ክፍል ነው!” –
ኮለኔል አለበል አማረ
ወንጀለኛን ከአፍንጫ ስር አስቀምጦ ሌላ ወንጀለኛ ለመያዝ መሞከር ከንቱ ድካም ነው። ዛሬ የአማራን ደም ያፈሰሰውን ወንጀለኛ ለመሸፋፈን ስለ ሰኔ 15ቱ ግድያ መግለጫ ለመስጠት ቀን ጠብቆ ብቅ ማለትም ነውረኝነትን ያሳያል። መንግስታዊ የአጀንዳ ማስቀየሪያ መሆኑንም እንረዳለን። በዚህም ትናንትም፣ ዛሬም የሞትነው እኛ ሆነን ሳለ – ለነገም አማራን የመከፋፈያ አጀንዳ እየተፈበረከልን መሆኑን አናጣውም።
በመሆኑም መላው አማራ ካልጠፋ ቀን የዛሬው የጠቅላይ አቃቢ ህግ መግለጫ አጀንዳ ማስቀየሪያ፣ የራስን ወንጀለኛ መሸፋፈኛ፣ አማራን መከፋፈያ … መሆኑን መረዳት አለብን። የትኛውም የዚህች ሀገር መንግስታዊና ግለሰባዊ አጀንዳ አማራ የሚጎዳበት፣ የሚሳደድበት፣ የሚገደልበት እንጂ የሚያተርፍበት አይደለም።
ስለዚህ ነገሮችን በጥልቀት ማስተዋሉ ይበጀናል። ዛሬ በማንነታቸው የታረዱት ወገኖቻችን ሀዘን ሳይወጣልን፣ ለሌላ መከፋፈል የሚዳርገን አጀንዳ ላይ ጊዜ አናጥፋ። በአጠቃላይ ትናንት በመከራ የመለስነውን አማራን በጎጥ የመከፋፈል ሴራ፣ ዛሬም ተመልሰን ማኘክ የለብንም። እንብሰል ለማለት ነው!
(ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ – በዛሬው እለት በጠቅላይ አቃቢ ህግ መግለጫ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት)
 
 
“ለእኔ የዛሬ 10 ሰዓቱ መግለጫ የድራማው ሶስተኛ ክፍል ነው!” –
ኮለኔል አለበል አማረ
የመጀመሪያው የድራማ ክፍል ውድ የአማራ ልጆችን በመግደልና በማስገደል “የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ” የሚል ስያሜ መስጠት ነበር። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከሞት የተረፉትን አማራዎች እስር ቤት ማጎርና አማራን በጥ የመከፋፈል ሙከራ ነበር። ዛሬ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ይሰጣል የተባለው መግለጫ ደግሞ የድራማው ሶስተኛ ክፍል ነው። እሱም የጃዋርን ወንጀል ለመሸፋፈንና የአማራን ህዝብ ለመከፋፈል የታቀደ።
ካልጠፋ ቀን ዛሬ በዚህ ዙሪያ መግለጫ መቅረቡ ምንሰ ያሳያል? በኦሮሚያ የፈሰሰው የንፁሐን ደም እንደሆነ በውሸት መግለጫ አይጠፋም። ውድ ልጆቻችንም መረጃ አሰባስበው ለአለም አቀፍ ተቋማት ክስ ጀምረዋል።
አሁን አዴፓ፣ አብን ወይም ሌላ የልዩነት አጀንዳ አይኖረንም። ሁላችንም በህብረት የምንቆምበት ጊዜ ነው። የአብን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የህሌና እስረኞች አጀንዳም መዘንጋት የለበትም። አንድነት ሃይል ነው!
(ኮለኔል አለበል አማረ – ስለዛሬው የአቃቢ ህግ መግለጫ የሰጠው አስተያየት)
Filed in: Amharic