>

የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ መተላለቅም ሃገር ማጣትም የተጣመሩበት ሁለት ኪሳራ......!!! (መስከረም አበራ)

የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ መተላለቅም ሃገር ማጣትም የተጣመሩበት ሁለት ኪሳራ……!!!
መስከረም አበራ
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ክስተቶች በሊቃውንት ቀርቶ በእኔ ቢጤው ተራ ሰው ውስን ግንዛቤ እንኳን ብዙ ትርጉም የሚወጣላቸው፣በርካታ ሰበዝ የሚመዘዝባቸው፣ሰፋ ያለ ትንታኔ የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ሆኖም የተረዳሁትን ሁሉ ለመፃፍ አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም አንዳድ እውነቶች የሚነገሩበት ጊዜ አለ፤እውነት ከሚነገር ይልቅ ባይነገር በጎ የሚሆንበት አንዳንድ የጭንቅ ወቅት አለ፡፡
 ዛሬ ሃገሬ የምትገኝበት የጭንቅ ወቅት የተረዱትን ሁሉ በተረዱት መጠን፣ባዘኑበት ልክ የሚነገርበት መስሎ አይሰማኝም፡፡የምናገረው እውነት እንደሆነ ባውቅም፤ያለወቅቱ የተነገረ እውነትም ሃገሬን ሊያጠፋ ይችላል ብየ ስለማምን የጠ/ሚውን ንግግር ከሰማሁ በኋላ አሁን ልቦናየ የሚነግረኝን ነገር ሁሉ ከመናገር እቆጠባሁ፡፡
መግለጫውን ስለማ ግን ተስፋ ማጣት እጅግ ተፈታትኖኛል፣ሃገሬ ሰው አልቆባት ኦና እንደቀረች ተሰምቶኛል፣ማስተዋል ከነገስታት እንደራቀች ገብቶኛል፣መሪዎቻችን የእኛን የተመሪዎቻቸውን የማገናዘብ ደረጃ እንዴት አሳንሰው እንደሚያዩ በደምብ ተረድቻለሁ፡፡ ፖለቲካ እና ፖለቲኝነት ከምገምተው በላይ ረቂቅ ውስብስቦሽ እንዳለው ተገንዝቤያለሁ፡፡ፖለቲከኛ ሲኮን የሆነ የሰውነት መልካም ገፅታ ከሰዎች እንደሚሸሽም ጠርጥሬያለሁ፡፡
የትኛውም የሃገሬ ሰው እንዲሞት አልሻም፡፡ የሟች ብሄረሰብ ማንነት ለሞቱ የተሰማኝን ሃዘን አይጨምርም አይቀንስም፡፡ በደህና ቀን የሰብዓዊ መብቶች ፅንሰሃሳብ የማረከኝ ሰው ነኝ!ከሰብዓዊነት የበለጠ ውብ ነገር አይታየኝም፡፡የሰብዊነት ዋነኛ ጠር ደግሞ ዘረኝነት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡እንደ ዘረኝነት የሰው ልጅን ከከፍታ የሚያወርድ ነገር እንደሌለ በዓለም ላይ የተከሰቱ አሰቃቂ የዘር ማጥፋቶች ምስክር ናቸው፡፡
የዛሬው የጠ/ሚው መግለጫ የሬሳ ዘር መቁጠሩ ሲገርመኝ፣የሟች ዘር የቁጥር ድልድሉ ይብስ ያስተዛዝባል፡፡የሬሳ ዘር መቁጠሩን ካነሱት ዘንዳ በኦሮሚያ ኮሽ ሲል የማን ሬሳ እንደሚታፈስ ማን ይጠፋዋል ተብሎ ነው ይሄ ሁሉ የቁጥር ጨዋታ? የሞተ ቀርቶ የቆመ ሰው ዘር መቁጠር ስራ ፈትነት እንደሆነ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም የዛሬው ሪፖርት የያዘው ሆድ ሲያውቅ የሆነ የቁጥር መረጃ ዘረኝነት ማለቂያ ወደሌለው አዘቅት እያወረደን እንደሆነ ህያው ምስክር ነው፡፡
ፖለቲካችን ከዘር ፖለቲካ ካልተዋጀ ሃገራችን እንደ ሩዋንዳ የሬሳ ክምር የሚያከረፋት፣የሞት መንፈስ የሚያስበረግጋት፣ስሟ ራሱ እልቂትን የሚያሳስብ የጣረሞት አምባ መሆኗ አይቀሬ ነው፡፡ በሩዋንዳ ዘር ማጥፋቱ ካለፈ ብዙ አመት ቢሆንም በበኩሌ አሁንም ሩዋንዳ ሲባል የሚሰቀጥጠኝ ነገር አለ! በፍሪካ ሃገር ባልሄድባት የምመርጠው ሃገር ነች-ሩዋንዳ…..በሩዋንዳ ዛሬም በየመንገዱ የሚጮህ ደም የሚዋጋ አጥንት ያለ ይመስለኛል
አካሄዳችን ግን ሃገሬንም እንዲህ ዘመን የማይሽረው የጣረሞት ምድር እንዳያደርጋት ስጋት አለኝ ፤ያውም እንደ ሩዋንዳ ከእልቂት በኋላም ሃገር መሆን ከተቻለ ነው! ይጎዝላቪያን መሆንም አለ-መተላለቅም ሃገር ማጣትም የተጣመሩበት ሁለት ኪሳራ
Filed in: Amharic