>
5:13 pm - Sunday April 19, 7598

እስክንድርንማ ተውት! (መስከረም አበራ)

እስክንድርንማ ተውት!

መስከረም አበራ
*ተመስገን ደሳለኝ ያለውን እኔም እደግመዋለሁ። ይህ ሰው የዘመኔ አሉላ አባነጋ ነው። የእርሱ ትውልድ አንድ አካል በመሆኔም ኩራቴ ወደር የለውም። ፍትሕ ቀና እስክትል ሄደህ የሞት ነጋዴህን ማንቆለጳጰስ ትችላለህ ፤ አውጋሩን፣ አድባሩንና ዋርካውን ይህን ሰው እንድትነካ ግን የሰው ሳይሆን የተፈጥሮ ሕግም አይፈቅድልህም!
ሰሞኑን ከአንድ ወዳጄ ጋር በስልክ እናወራለን፡፡ እሱ በጠ/ሚ  አብይ አስተዳደር ላይ ተስፋ ቆርጦ ጨርሷል፤እኔ ደሞ ደፍርሶ ሲጠራ የሚመጣ ነገር ካለ እንይ ባይ ነኝ፡፡ በክርክራን መሃል “አንድ ቀላል ጥያቄ  ልጠይቅ” አለኝ፡፡መተባበቅ ጀመርኩ፡፡ ቀጠለ “ሌላ ሌላውን ተይውና በአሁኑ ሰዓት በበእኩልነት የምንጨቆንበት ሁኔታ እንኳን እንደሌለ አይታይሽም? በዚሁ ሁኔታ እንዴት ያለ ተስፋ ነው የሚኖረኝ?!” ሲል ምርር አለ፡፡ ለዚህ አባባሉ ብዙ እውነተኛ መረጃዎችን አቀረበልኝ፡፡ ክርክሩ ልክ ስለሆነ፤እውነትን መቀበል ደግሞ ግድ ነውና ፣አንድነት ልዩነታችን አጠር አድረጎ ባስቀመጠልኝ ግሩም አገላለፅ ተስማምቼ ስልኬን ዘጋሁ፡፡
ልክ ነው! አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ እኩል መጨቆን እንኳን አልቻልንም፡፡አንዱ እንደ ስለት ልጅ ነው-የሃገሪቱን የመንግስት ራስ ሳይቀር እያብረከረከ ማብራሪያ የሚያስጠይቅ፣ ‘የሚያስከፋ ነገር ምን ተናገርኩህ?’ የሚባልለት፣’የሃገርህ እና የሃገሬ ቋንቋ አለመመሳሰሉ እንጂ ምን ቆርጦኝ አንተን ላስከፋ፣ምን ሲደረግ አጀብ ሊጎድልብህ?’ የሚባል ክቡር!
ሌላው ደግሞ ምን ቆርጦህ ታሰላስላለህ፣ምን ሲደረግ መብትህን ትጠይቃለህ፣ እንዴት ብለህ መታፈንህን ትናገራለህ ተብሎ መግቢያ መውጫ ያጣል፡፡ ጨዋ ንግግሩ ከጋጠወጥነት ተቆጥሮ እንደ ተራ በተራ ሰዎች ይዘለፋል፡፡የስለቱ ልጅ ደግሞ አስቦ አለመናገሩ የታጋይነት ቁንጮ ተደርጎ ይወሰድለታል፡፡ አጃቢው ብዙ ነው፤የተናገረው ቀርቶ የማያውቀው ይሰየፍለታል፤ለክብሩ መገለጫ ሰው ይታረድለታል፤ተዘቅዝቆ ይሰቀልለታል፡፡ ይህም እንደምንም ሳይቆጠር ህይወት ይቀጥላል፡፡
እኩል መጨቆን አለመቻላችን እንደ እስክንድር ነጋ ዋጋ እያስከፈለው ያለ ሰው የለም፡፡እስክንድር መዛባትን አይቶ ዝም ማለት የማይችል ሰው ነው፡፡ መዛባትን ባየ ጊዜ ሁሉ ባዶ እጁን ከአረመኔዎች ጋር ለመዋጋት የሚወጣ ልባም፤’እሞት ይሆን?’ ብሎ የማይፈራ ብርቱ፤ነፍሰ በላው ህወሃት ሲኖርም ሳይኖርም ለትግል የሚወጣ ሞት ጤፉ፡፡ እስክንድር መሞት እንደ ሌለ አስረግጦ ሃገር ቤት የገባ ቡከን ፤ማዕከላዊን ለጉብኝት ሄዶ ያየ  ቱሪስት አይደለም፡፡እስከንድር ዶላር የሚያነቃቃው የ”Go fund me” ታጋይ፣የኪቦርድ አርበኛ ከቶ አይደለም! ትግልን የጀመረውም ሳር ቅጠሉ ታጋይ ነኝ ባለበት የጅምላ ዘመን ሳይሆን የሃገር ሰው ሁሉ ባርነትን ሳይወድ በግድ ተሸክሞ በሚያቃስትበት ወቅት ለብቻው አንገቱን ቀና አድረጎ የባርነት ቀንበር አሽቀንጥሮ የግፈኞችን መራራ ፅዋ ለመጎንጨት ወደ ከፍታ የወጣ ንጥር ነው!
እስክንድር ጥፍር ነቃይም፣አላስርም ባይም በሚገዛበት ምድር ለመታገል የተዘጋጀ በራሱ ጨካኝ ታጋይ እንጅ ስጋት እንደ ሌለ ሲያረጋጋጥ ተሳፍሮ መጠቶ “እኔ ልባስ!” የሚል ቱልቱላ አይደለም፡፡ እሱ ከተከታዮቹ በፊት ሊሞት የተዘጋጀ የሞራል መሪ እንጅ ሞቱን ለሌላ ዝናውን ለራሱ አደላድሎ ለትግል የሚወጣ መሰሪ አይደለም፡፡
ስለዚህ እስክንድርን ተውት …….!
Filed in: Amharic