>
5:13 pm - Sunday April 19, 3271

የአሸባሪው ዐቅም ከአገዛዙ ድጋፍ ውጭ ኢምንት እንደሆነ ታውቋል (ከይኄይስ እውነቱ)

የአሸባሪው ዐቅም ከአገዛዙ ድጋፍ ውጭ ኢምንት እንደሆነ ታውቋል

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ አገራችን የአንድ ቅጥረኛ አሸባሪ እና የወንጀሉ ተባባሪዎች የሆኑ መንደርተኞች መጫወቻ ሆናለች፡፡ ቅጥረኛ አሸባሪው ሙሉ መንግሥታዊ ድጋፍ ያለው ሲሆን፣ ግራና ቀኛቸውን የማያውቁ÷ ወያኔና ኦነግ የዘር የጥላቻ መርዝ ሲግቷቸው ያደጉ ሥራ ፈት ሆነው የተቀመጡ ጋጠ ወጥ ወጣቶችን በመሣሪያነት እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡ እነዚህ በመንጋ የተሰባሰቡ ጋጠ ወጦች ከአሸባሪው በሚሰጣቸው ትእዛዝ በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በጠራራ ፀሐይ የዛቻ÷ የትንኮሳና ከዚህም አልፎ በንጹሐን ዜጎች ላይ የጥቃት ተግባራትን ሲፈጽሙ የቆዩ ሲሆን፣ በአገዛዙ መዋቅርና አንዳንድ ባለሥልጣናት አይዞህ ባይነት በሕገወጥ እና ነውረኛ ድርጊታቸው ቀጥለውበታል፡፡ ከሕዝቡ እና ኃላፊነት ከሚሰማቸው ጥቂት የማኅበራዊው ብዙኃን መገናኛዎቸ ለመንግሥት ማሳሰቢያ ቢቀርብም እንዳልሰማ ሆኖ በተለመደው ዳተኝነቱ ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ዐቢይ በሚመራው አገዛዝ እምነት ከማጣቱም በላይ መንግሥት የለም ከማለት ደርሷል፡፡

ከሰሞኑም በዚህ በሽተኛ ግለሰብና ተባባሪዎቹ አማካይነት ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ በሚመስል ሁናቴ በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች በንጹሐን ዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ አሰቃቂና ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በተለይም አብያተ ክርስቲያናት ዒላማ መደረጋቸው የአሸባሪውን ተልእኮ ምንነት በሚገባ የሚያስረዳ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት የሚባለው አካል መደበኛና ዓይነተኛ የሆነውን ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በመላው አገሪቱ ሥርዓተ አልበኝነት በእጅጉ ነግሦ ይገኛል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ (አገዛዙ የፈለገውን ቢያወራም) የሚመካበትና የራሴ የሚለው ኢትዮጵያዊ የመከላከያ÷ የአገርና የሕዝብ ደኅንነትና የፖሊስ ኃይል የለውም፡፡ ዜጎች አገዛዙ ያሠማራቸውን የፖሊስና የደኅንነት ኃይል ሲሸሹ ነው የሚስተዋለው፡፡ መከላከያ ተብዬውም ጥፋቱ በስፋት ከተፈጸመ በኋላ ነው ሰላም አስከብራለሁ ብሎ የተንቀሳቀሰው፡፡ እንቅስቃሴው ተገቢ ቢሆንም የሚያስመሰግነው ግን አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ አንድ መንግሥታዊ ተቋም መደበኛ ተግባሩን ሲያከናውን የምናመሰግንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ነገሩ የተበላሸው የአገር መከላከያ÷ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት እና የፖሊስ ኃይሎች ዘርን መሠረት አድርገው ሲደራጁ ነው፡፡ ዐቢይም ሆነ ‹የለውጥ ኃይል› የተባሉት ባልደረቦቹ በያንዳንዱ የመንግሥት መዋቅር ስለ ዘር ኮታ ነው እኮ የሚያወሩን፡፡ ይህን ያህል ከዚህ ጐሣ ይህን ያህል ከዚያኛው እያሉ፡፡ ከዚህ በሽታ ካልተላቀቅን ስለ አገር ህልውናና አንድነት ቀጣይነት መነጋገር አንችልም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ መንበር ላይ በጉልበት ገዥ የሆነው ጐሠኛው የዐቢይ ድርጅት ኦሕዴድ ኦነግን አኽሎና መስሎ (አሸባሪውን ግለሰብ ያልተጻፈ መሪው አድርጎ) ከወያኔ ትግሬ በከፋ መልኩ ለጥፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በእንጭጩ መቅጫት ይቻል የነበረውን ጋጠ ወጥነት መጠነ ሰፊ ሆኖ ሕዝብ የለት ተዕለት ሕይወቱ በሥጋት እንዲሞላ አድርጎታል፡፡ በዚህ ሕዝብንና አገርን የማሸበር ድርጊት ውስጥ ሕግን ያስከብራል ተብሎ የሚጠበቅ የፖሊስ ኃይል ባንድ ወገን ወያኔና አሽከር ድርጅቶቹ አገርን ለማወክና ለማፍረስ በሕገ ወጥ መልኩ ያደራጁት ‹ልዩ ኃይል› በሌላ ወገን በእልቂቱና ውድመቱ ተሳታፊ እንደነበሩም የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡

በሰሞኑ ክስተት እንደተስተዋለው በጭፍንና በመንጋነት የሚሠማሩት ጋጠ ወጦች ከጭካኔ በቀር ዓላማና ወኔ÷መነሻና መድረሻም የላቸውም፡፡ ሕዝብ ራሱን ለመከላከል ሲወጣ አይጥ ሆነው ሲቁለጨለጩ አስተውለናል፡፡ ከለበቅ እንደማያልፉም ዓይተናል፡፡ አሠማሪያቸውም ለጥፋት ዓላማው ከተጠቀመባቸው በኋላ እስከ መፈጠራቸውም እንደሚረሳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለእነዚህ ጋጠ ወጥ ልጆችና ለተገኙበት ማኅበረሰብ ከልብ የሚጨነቅ አካል ወይም ባለሥልጣን በማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ በክፍለ ሀገር አገዛዝ ደረጃ ካለ ተከታታይ የዜግነትና የሥነ ምግባር ትምህርት ሰጥቶ እንደ ሁናቴው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወይም ወደ ሥራ እንዲሠማሩ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ወላጆችና ሽማግሎችም ልጆቹ አደብ እንዲገዙ አጥብቃችሁ ምከሩ፡፡ ልቅሶና ኀዘኑ ነገ የሁሉንም ቤት ያንኳኳል፡፡ ቅጥረኛ አሸባሪውንና በዓላማ የሚመስሉትን ተከትለን ኹከት እየፈጠርን እንቀጥላለን ካሉ ለጋጠ ወጦቹም ሆነ ለአሠማሪዎቻቸው አይበጅም፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ካለ የመንግሥትን ጠባይ ያሳየን፡፡ ጉዳዩ ዐቢይ ምን ያስባል ወይም አሰላለፉ ከነማን ጋር ነው የሚለው አይደለም፡፡ በዚህ ጊዜአችንን አናጠፋም፡፡ ይህ በፍሬውና በተግባሩ ሕዝብ መዝኖ ዳኝነት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አብዛኛው ሕዝብ ትዕግሥቱ ተሟጥጦ በአገዛዙ መሪ ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ ወደማለቁ ተቃርቧል፡፡ ቅጥረኛ አሸባሪውንና መረቡን ወደ ፍርድ ያቅርብ፡፡ አገዛዙ ከወያኔ ትግሬ ስህተት ሳይማር ንጹሐንን አሸባሪ ብሎ መክሰስ ከቻለ (ተአማኒነት ካሳጣው አንዱ ነውረኝነት መሆኑን ይታዘቧል) እውነተኛውን አሸባሪ ለፍርድ ለማቅረብ ምንም ምክንያት ሊያቀርብ አይችልም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስወሩት (አገዛዙም ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በቀር) በአሸባሪው መያዝ (ባገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ የተቀመጠውን የአሸሰባሪነት ብያኔ ስለሚያሟላ) የሚፈጠር አንዳች ነገር የለም፡፡ ግፋ ቢል መንጋ ተከታዮቹ ኹከት ከሚፈጥሩ በቀር፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት አስቀድሞ ተዘጋጅቶ የቆመበትን ሕግና ሥርዓት የማስከበር ተግባር ባግባቡ ከተወጣ አደጋ እንዳይኖር ወይም በእጅጉ ለመቀነስ ይቻላል፡፡ ላንድ ቅጥረኛ አሸባሪ ተብሎ አገር ሲታወክ፣ የንጹሐን ዜጎች ደም እየፈሰሰ እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም፡፡

በመጨረሻም ከእስከዛሬው ተሞክሮና ምድር ላይ ከምናየው ጽድቅ አኳያ የጠ/ሚሩ መግለጫም ሆነ እነ ለማ ለቤተክህነቱ የሰጡት ቃል በቅጥረኛ አሸባሪውና ተባባሪዎቹ የሚፈጸመውን ሽብርና ኹከት ለማስቆም ዋስትና ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ቅጥረኛ አሸባሪው ጀዋር መሐመድ የሚባል ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ሰው ነው፤ ለደረሰው እልቂትና የንብረት ውድመት ከነግብርአበሮቹ ባለሥልጣናት ተጠያቂ ነው ብለው ለመናገር ድፍረቱ አላቸው ወይ? ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው (ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው) አሁን ሥራ ላይ ባሉ የአገሪቱ ሕጎች ሽብር መፍጠሩ ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ በፖለቲካ ጉዳይ መሳተፍ፣ የመደበኛ ብዙኃን መገናኛ ባለቤት መሆን ይችላል ወይ? ሰው እንዳይሞት ብለን ነው የሚለው የማይመስል ምክንያት አያዋጣም፡፡ ዐቢይ ሥልጣን ላይ ከመጣ ጀምሮ በአገዛዙ ቸልተኝነት/ዳተኝነት የአገራዊ ሀብት ውድመቱን ትተን የስንት ንጹሐን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል? ስንቶቹ በአካልና በአእምሮ ስንኩላን ሆነዋል? ስንት ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል? ቤት ይቊጠረው፡፡ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ሂደት አጥፊዎች ወደ ፍርድ እንዲመጡ ማድረግ የመጀመሪያው አማራጭ ሲሆን እምቢተኞች ሆነው በኃይል እንገዳደራለን ካሉ ግን ልናስቀረው የማንችል ተመጣጣኝ ርምጃ መውሰድ ለሰላማዊ ዜጎች ሕጋዊ መድኅንና ዋስትና ነው፡፡ እነ ዐቢይና ለማ ቃላቸውን ስለማክበራቸውና ስለማጠፋቸው (በሌሎች አደናጋሪ ወቅታዊ ጉዳዮች ሳይዘናጋ) በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ለመጨረሻው መጀመሪያ ፈተና የሚቀርቡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ በእስካሁኑ እንገዛዋለን ለሚሉት ሕዝብ በቃላቸው ታምነው አልተገኙምና፡፡

ልዑል አምላክ በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ዕረፍተ ነፍስን÷ ለቤተዘመዶቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፡፡ ስለ ምርጦቹ ብሎ ተጨማሪ ጥፋትን ያርቅልን፡፡

Filed in: Amharic