>

መግለጫው ዝም አለ!!! (ደረጄ ደስታ)

መግለጫው ዝም አለ!!!

ደረጄ ደስታ
 
 
“ይህ ሁሉ ለምን እንደመጣብን እናውቃለን” ጠ/ር አብይ
ጠ/ር አብይ ስለሰሞኑ ሁኔታ ዛሬ የሰጡትን መግለጫ አነበብኩት።  አደጋውንና በደረሰውም ጉዳት ማዘናቸውን ገልጠው “የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎች በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢው ሁሉ እንዲያገኙ ያለማወላወል እንሠራለን፡፡” ብለዋል። ባይሠሩ ነበር እሚገርመን እንጂ እንደሚሠሩማ እናውቃለን። አሁን የፈለግነው በዚህ ጉዳይ ምን እንደሠሩ? ምን እንደተደረገ? ምን ማድረግ እንዳሰቡ ነው። ከመግለጫው ሁሉ ትኩረቴን የሳበው ““ይህ ሁሉ ለምን እንደመጣብን እናውቃለን” ያሉት ነገር ነው። ምንድነው ያወቁት? አገራዊ ምስጢርነቱን አስቀርተው ከሚያውቁት ጥቂቱን እንኳ ቢያካፍሉን ጥሩ ነበር። ያን ማድረግ የማይመቻቸው ከሆነ ደግሞ የሚያደርጉትን አደራርገው ሪፖርቱን ቢያቀርቡልን ይህን ሠርተናል በዚህ የተነሳ ይህን ፈጽመናል ቢሉን በተገባ ነበር። እሳቸው የሚያውቁትንም ያህል ባይሆን እኛም እሳቸው ራሳቸው በነገሩን መሠረት መርምረው የጨረሱትና ገና ቀድመው አውቀው ያስጠነቀቁን ነገር መሆኑን እናውቃለን። ሁለተኛ የተደረገውና የሆነውም ነገር በግልጽ በአደባባይ የተፈጸመ ነገር ነው። ወደፊት እንደሚደገምም በማናለብኝነት እየተነገረና እየተዛተብን ነው። እኛም ይህን ሁሉ እናውቃለን። እባክዎ ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር እኛ እምናውቀውንና እርስዎ እሚያውቁትን አንድ ላይ አስማምተው አንድ ነገር ያድርጉ። ሚሊዮን ተከታይ ያለው ስጋት እንኳ ቢመጣብዎ በበብዙ ሚሊዮኖች እሚቆጠር ተከታይ እንዳልዎት ያስታውሱ።  ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳይሉ ይህን ነገር ያስታግሱ። እስከዚያ ድረስ ዝም ይበሉ። መናገርዎ የግድ ከሆነ አንጀት የሚያርስ ወይ ከልብ የሚደርስ ወይም አገር የሚያጸና ነገር ይናገሩ። ለአቲዎ ባቲዎው ንግግሩና እሪታው እኛ አቅመቢሶች እንበቃለን። ግልጽነትዎን ብንወደውም ሙያ በልብንነትም አይርሱብን። ከኢትዮጵያ ጋር እስከሆኑ ድረስ ኢትዮጵያ ከርስዎ ጋር ናት- አይዞን። አያያዝዎን አይቶ ጭብጦዎን ሊቀማ ካሰፈሰፈ ጭልፊት እግዚአብሔር ይጠብቅዎ! እኛስ ብንሆን…የሌለው ደግሞ ያቺው ያለችውም ብትሆን ትወሰድበታለች… ብንባል ትርፋችን ምን ይሆናል?
Filed in: Amharic