>

የመንግሥት ልዑካን ቤተ ክርስቲያን ወደተቃውሞ እንዳታመራ ተማጸኑ!!!

የመንግሥት ልዑካን ቤተ ክርስቲያን ወደተቃውሞ እንዳታመራ ተማጸኑ!!!
ቀሲስ በላይ አስራት
“አንዳንድ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን ሲላቸው በፊውዳል ስም፣ ሲላቸው በነፍጠኛ ስም እየፈረጁ እያስፈጁን ነውና ችግሩን ለመቆጣጠር አቅም አላችሁን? አቅም ከሌላችሁ አሁኑኑ ንገሩን፤ እየሞተ የሚቀጥል አይኖርም…”   ብፁዓን አባቶች
….አቅም አለን፣ እየተነሣ ለውን አቧራ በአንድ ጀምበር ጸጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ግን መግደልን ይጨምራል፡፡ የመግደልን መንገድ ደግሞ የመጣንበት ስለኾነ አልፈለግነውም….” የመንግስት ልኡካን
 
ዛሬ ዐርብ ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት ለማነጋገር ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመጡት የመንግሥት ባለሥልጣናት ቤተ ክርስቲያን ትራዳቸው ዘንድ ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡
ወደ ጉባኤው የመጡት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ፣ የሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የፌድራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ናቸው፡፡
ለእነዚህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አባቶች ኹለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል፡፡
አንደኛ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ ነገ ይሻላል በማይባል ጥቃት ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህ ያላባራ ጥቃት ይቆም ዘንድ መንግሥት የሚሰጠው ዋስትና አለን?
ኹለተኛ፡- ጥቃት አድራሾችን ለይቶ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት እስከምን ድረስ ነው?  የሚሉ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ ብፁዓን አበው “አንዳንድ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን ሲላቸው በፊውዳል ስም፣ ሲላቸው በነፍጠኛ ስም፣ ሲላቸው በአንድ ጎሳ ስም እየፈረጁ ስሟን ሲያጠለሹ ታግሰናል፡፡ ግን ይህ አልበቃቸውም፡፡ ወደ አካላዊ ጥቃት ዘምተዋል፡፡ አሁን የምንጠይቃችሁ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ እርሱም ችግሩን ለመቆጣጠር አቅም አላችሁን? የሚል ነው፡፡ አቅም ከሌላችሁ አሁኑኑ ንገሩን፤ እየሞተ የሚቀጥል አይኖርም፡፡” በማለት ፍርጥም ያለ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በአንጻሩ ከፍተኛ የምንግሥት ባለ ሥልጣናት አበውን በማመስገን ለጥያቄው መልስ ሰጥተዋል፡፡ በጥቅሉ አቅም አለን፣ እየተነሣ ለውን አቧራ በአንድ ጀምበር ጸጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ግን መግደልን ይጨምራል፡፡ የመግደልን መንገድ ደግሞ የመጣንበት ስለኾነ አልፈለግነውም ነበር፡፡ ከእንግዲህ ግን ትዕግስታችን ተሟጥጧል፡፡
የጎሰኝነት እና የሃይማኖት ጽንፈኝነት ከፍተኛ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ነገራችን ሁሉ ሳቅ እና ሐዘን ኾኗል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ብዙ ሥራ አጥ ወጣት አለን፡፡ ይህንን ወጣት ጽንፈኞቹ በቀላሉ እየዘወሩት ይገኛል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ተረዱን እርዱንም፡፡ እናንተ ወደ ተቃውሞ ከሔዳችሁ ማን ነው ከጎናችን የሚቆመው? እርዱን እርዱን ነው የምንለው፡፡ ለልጅ ኹለትም ሦስትም ዕድል ይሰጣል፤ አሁንም ዕድል ስጡን፡፡
የተጠየቁትን ጥያቄዎች መሠረት አድርገን ርምጃ መውሰድ እንጀምራለን፡፡ ለጠቅላይ ሚንስትሩም ነገሩን እናደርሳለን በማለት ተሰናብተዋል፡፡
Filed in: Amharic