>
5:13 pm - Saturday April 19, 0730

እውነት እንናገራለን:— የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ቀድሞ ተገንጥሏል!!! (ሱራፌል አየለ)

እውነት እንናገራለን:— የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ቀድሞ ተገንጥሏል!!!
ሱራፌል አየለ
ከአመት በፊት “የህይወቴ አስቀያሚው የስራ ልምድ” ብዬ የምሰይመው ስራ ውስጥ ተሳተፍኩ። ስራው  መማሪያ መፅሃፍትና መምሪያ ማዘጋጀት ነበር— ለኦሮሚያ ክልል ትት ቢሮ። የማስተበባር ስራ ነበር ድርሻዬ። በዚያውም አዘጋጆቸቹ የመጨረሻ የሚሉትን ረቂቅ ለህትመት ወደ ውጪ ከመላኬ በፊት የአርትኦት ስራ እሰራ ነበር። እጅግ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ስራ ነበር።
እኔ ስደርስ (ከሌላ ፕሮጀክት ነበር ቡድኑን የተቀላቀልኩት) የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ድርጅቴ ያቀረባቸውን በአካዳሚክ ዘርፍ ውስጥና በትምህርትና ካሪክለም ዝግጅት “ለጥ ብለን” እጅ የምንነሳቸውን ታዋቂ ባለሞያዎች “ወግዱ ፣አልፈልግም፣ የራሴ ሰው አለኝ” አለ። ይህ በኮንትራት ስራ አለም ውስጥ ምን ያህል ህገወጥ ስራ እንደሆነ የሚገባችሁ ትኖራላችሁ። ቁም ነገሩ እሱ አይደለም፤ ምክኒያታቸው እንጂ። እነዚህ ምሁራን ለዝግጅቱ ያልተመረጡት በቢሮው ሃሳብ  ” በአንድ ወገን የሌላ ብሄር ደም ስላላቸው”  ነበር።
ስለ መፅሃፍ ዝግጅት
አለም አቀፍ በሆነው ስታንዳርድ መፅሃፍ ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ሳይክል ተማሪዎች አካባቢያቸውን እንዲመረምሩና እንዲረዱ ይደረጋል። በቀጣይ ሁለተኛ ሳይክል ጀምሮ ሃገራቸውን እንዲረዱ እንዲመረምሩ እንዲያውቁ ይበረታታሉ። ድንበር ተሻጋሪ ሆነው ከሚኖሩበት አካባቢ ውጪ የሚገኙ የሃገራቸው አካባቢ ሰዎች የአናናር፣ አለባበስ አመጋገብ ዘይቤ፣ ታሪክ ወዘተ መሰል እሴቶችን እንዲያውቁ ይደረጋል። ይህ በስነልቦና ደረጃ ለተማሪዎቹ ዝግጅት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ አህጉርና አለም አቀፍ የሆነውን ስነምድር፣ህዝብ፣ ባህል ወዘተ የሚተዋወቁት።
በኦሮሚያ ት/ት ቢሮ ውስጥ ይህ የማይታሰብ ነው። በየትኛውም የክፍል ደረጃዎች የሚቀርቡ መረጃዎች በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ውጪ ስለለው ወንድም ህዝብ/ማህበረሰብ እንዲያውቁ አይፈቅዱላቸውም።
ከፓለቲካ አመራር እስከ ታዋቂ አካዳሚሺያን ፣ ከደራሲ እስከ ስፓርት ሰዎች፣ ከዳር እስከ ዳር የሚካተቱ ግለታሪኮች፣ መረጃዎች፣ ፅሁፎች በሙሉ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የወጡ ካልሆኑ አዘጋጁ “ነፍጠኛ” የሚል ታርጋ ሳይለጠፍበት በፊት ሃሳቡን መቀየር አለበት።
በዚህ ስርአት ውስጥ ለሚያልፉ ተማሪዎች ” ኢትዮጵያ” የምትባል ሃገር የለችም። ንፁህ አዕምሮአቸው በንፅና የተቀበለው ሰማይና ምድር “ኦሮሚያ” የሚባል “ወንደር ላንድ”ን ነው።
ለነዚህ ህፃናት/ታዳጊዎች “ሌሎች/others” የሚለውን ስነልቡና የሚዘሩባቸው ከልጅነት ነው።  በዚህ የተነሳ ስሌሎች ማወቅም ሆነ መስተጋብርን ስለመስራት ተማሪዎቹ አያልሙም። ይልቁንም “ሌሎች ” ሲያጠቋቸው እንደኖሩ ይነገራቸዋል። በዚህም በበታችነት ስነልቡና ውስጥ ሲያልፉ፣ አጋጣሚና ሁነቶች በተመቻቹ ጊዜ “ሌሎች”ን ማጥቃትና መበቀል በልጅ ልቦናቸው ውስጥ ይፀነሳል።
ለፊልድ ስራ በተጓዝኩበት አንደኛው የክልሉ ገጠር ከተማ ውስጥ ይህን የሚያረጋግጥልኝ ሃቅ አይቻለሁ። የአማርኛ መማሪያ ደብተር ከሌሎቹ ነጥለው በማውጣት ከቤታቸው ደጃፍ የሚያስቀምጡ ታዳጊዎች አይኔ አይቷል። የ13/14  አመት ታዳጊ በዚች የህይወት ልምድ ውስጥ ይሄን ያህል ጥላቻ ሊያዳብር አይችልም። ይህ ትምህርታቸው indoctrinated ከመሆኑ የመነጨ ጭፍን ጥላቻ ነው።  የቋንቋ ደብተሩን እየተፀየፈ ያደገ ተማሪ ከተናጋሪዎቹ ጋር ያለው መስተጋብር harmonize እንዲሆን መጠበቅ ያቆምኩት ያኔ ነው።
የመጨረሻውን  ንባብ እያካሄድኩ “ጎርባጭ ” አረፍተ ነገር አጋጠመኝ። ይሄን በአስራዎቹ እድሜዬ ባነብ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ነገር አሁን እንደምታይዋቸው እንዳንዱ “ዱላ” ይዤ እወጣለሁ፣ የ “ሌሎች” የሆነን ነገር ማውደምም እመኛለሁ።
ቅዳሜ ቀን ላየረ ፀሃፊዎቹ ስራቸውን አጠናቀው ለመሄድ ሲሰናዱ ሃሳቤን የሚረዳኝ የሚመስለኝን (በእድሜ ስታንሱ ያላችሁን ተደማጭነት ምታቁት ነው እኛ ቀዬ ላይ )  ፅሁፉን አሳየሁት። ” ምን ይዘሽ መጣሽ ደሞ?  ይሄን የሰራው እገሌ ነው  የሱን ስራ መቀየር ታቂያለሽ አደል ምን እንደሚያስከትል? “
ለመንኩት!  ” በልጆችህ ይሁንብህ! ይሄን  አንድ አረፍ ነገር በሌላ ተካው” አልኩት። ሃሳብ ሲያመነዥግ ቆዬ። አስተካክለዋለሁ አለኝ። እያየሁት ሰረዘው ፣ በሌላ ተካነው።
ልክ እንደ አባት አቀፈኝ! ምን ተሰምቶት እንደሆነ አላቅም። ( ይሄን እያነበበ እንደሚሆን እገምታለሁ! አመሰግነዋለሁም! ) እንባዬ አንዳይንጠባጠብ እየተጠነቀቅኩ አመሰገንኩት። (ወንድ ብቻውን ነው ሚያለቅስ! )
የሽፋን ስራው ተሰርቶ አለቀ። ቢሮው ደነፋ። ምክኒያት ነበራቸው። የፌደራል ባንዲራ ከፊት ገፅ ላይ እንዳይቀመጥ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ።
ያኔ—  እኔ ተስፋ ቆረጥኩ። አብቅቷል ።
———
አሁን ላይ ስለ ጀዋር መሃመድና ወጣቶች ስትተነትኑ እየተገረምኩ አልፍ ነበር። አትድከሙ ሌላ ነገር ተንትኑ!  ጀዋር መሃመድ የተፈጠረለትን አጋጣሚ የተጠቀመ ብልጣ ብልጥ ነው። ከዛ የዘለለ ምልከታ የለኝም ለሱ። በእውኑ መምራት ችሎም አደለም። ጀዋር ኢትዮጵያዊ መሆን የማይፈልገው የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ባነሳሁትና ባላነሳሁት መልኩ  ያዘጋጀለትን አፍላ ወጣቶች ሜዳ ማስወጣትና ማስገባት ቻለ። ወጣቶቹን እዘኑላቸው!  ሰብአዊ ክብራቸው ሜዳ ተነድቶ ወጥቶ ግባ ሲባል ስለሚገባ አዝንላቸዋለሁ።
አሁን ጭቅጭቁንና ከንፈር መጠጣህን ትተህ ስለ ትምህርት ስርዓቱ ካላወራህና ያገባኛል ካላልክ  እመነኝ the worst is yet to come!
Filed in: Amharic