>

እኔ የምፈራዉ!  (ሃራ አብዲ)

እኔ የምፈራዉ! 

 

ሃራ አብዲ

 

ስሙን ካልጠራሁ ስለማን እንደምናገር  አንባቢ ማወቅ ስለ ማይችል እንጂ የዚህን ሰዉዬ ስም መጥራት አልፈልግም ነበር። ከሚገባዉ በላይ ተጠርቶአል። በፍጹም ሳይገባዉ (ይ ጠበቅ ብሎ ይነበብ) የኢትዮጵያን የፖለቲካ አየር ሞልቶታል። በዘረኝነት, በጠባብነት, በስልጣን ጥመኝነት። ጃዋር መሀመድ። ዛሬ በመኖሪያ ቤቱ የተወሰኑ የኦሮምያ ባለስልጣናትን፤ እነ ጄነራል ከማል ገልቹን ፤ሺመልስ አብዲሳንና ገላሳ ዲልቦን (አልተሳሳትኩም አይደል?) ሰብስቦ ዉቃቢ-አምላኩን ሲያስለምናቸዉ መዋሉን በዜና ስሰማ፤ ግራና ቀኙን ሳያዉቀዉ ጃዋርን በጭፍን የሚከተለዉ የወጣት መንጋ ጉዳይ አሳሰበኝ። መቼም የነጄነራል ከማልና የነ ሽመልስ እንዲህ መንጰርጰር አይጣል ከማለት ሌላ ምንም ሊባል አይቻልም። አይጣል መባል ከሌለበት ደግሞ እነርሱ እራሳቸዉ የጃዋር አንድ ሳንቲም ሶስት ገጽታ ሆነዋልና ጠ/ሚ አብይ ፈጥኖ እርምጃ መዉሰድ ግድ ይለዋል። ይህ ሁሉ ልፋቱ፤ አገር እለዉጣለሁ ብሎ ጉዋንት እንኩዋን ሳያደርግ ችግኝ መትከሉ፤ ቤተ-መንግስትን ያህል እንዲህ ባበደ ወቅት ሙዚየም ማድረጉና ደፋ ቀና ማለቱ የመንግስትን ስልጣን ለጃዋር ለማስረከብ ሊሆን አይችልም ብዬ ነዉ።

እኛም ሲጀምረን እንዲህ አርጎን ነበር እንዳለችዉ እብድ አንዳንዶች ሲጀምራቸዉ እንዲህ አድርጎአቸዉ ነበር። የከልት መሪዎች ማለት ነዉ። እነ ጂም ጆንስ (Jim Jones) 1955-1978 በነበረዉ ጊዜ፤ከዘጠኝ መቶ በላይ ተከታዮቹ እራሳቸዉን እንዲያጠፉ (suicide) አሳምኖአቸዉ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸዉን አጥፍተዋል። ጂም አባላቱን የሳበዉ የሰብአዊ መብት አክቲቪስት ነኝ በማለቱ እንዲሁም አረጋዉያንና የአእምሮ ህሙማን የሚኖሩባቸዉን ቤቶች በመምራቱ ነበር፤ ክርስቲያን መሪ ነኝ ከማለቱ ጋር።

ዴቪድ ኮረሽ (David Koresh) የሰባተኛዉ ቀን አድቬንቲስት ፅንፈኛ የነበረ ሲሆን በ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ 1993 ድረስ አባላቱን ብሬን ዋሽ ሲያደርጋቸዉ ቆይቶ ሲነቃበት ለ51 ቀናት ከኤፍ-ቢ-አይ ጋር ተፋጦ በመጨረሻ ቅጥር ግቢዉ እንዲጋይ በመደረጉ ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ተከታዮቹ ህይወታቸዉ አልፎአል። የከልት መጨረሻዉ ተያይዞ መጥፋት ነዉ። በምሳሌነት የቀረቡት ጂም ጆንስና ዴቪድ ኮረሽ አሜሪካዉያን ሲሆኑ፤ሀይማኖትን፤ የሰብአዊ መብት ተሙዋጋችነትን፤በጎ አድራጎትን እንደመነሻ ያደረጉ ሲሆን እየዋለ ሲያድር የተከታዮቻቸዉን አእምሮ ለመቆጣጠር በመቻላቸዉ ፤ህይወታቸዉን ለመሰዋት ምንም የማያቅማሙ ተከታዮችን ማፍራት የቻሉ ናቸዉ። ወደኛ ሀገር ጉድ ስንመለስ ፤ጃዋር( አሜሪካዊ ነዉ) እርሱን መንካት የኦሮሞን ህዝብ መንካት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶበት፤ ህዝቡ በጣም እንደተቆጣ፤ ከዚህም የተነሳ አቅም እንዳለዉና እነ አብይ ከእርሱ ጋር ጸብ ባይሞክሩ እንደሚሻላቸዉ አሳምሮ ገልጾአል። ይህ እንግዲህ እነጀማል ገልቹ፤ «እዉነት ነዉ ትግሉ ተቀልብሶአል— ምናምን እያሉ የጃዋርን አዶከብሬ ሊለማመኑ እቤቱ ታድመዉ ሳሉ ማለት ነዉ። እዉነት ነዉ ፤ትግሉስ ተቀልብሶአል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ በደንብ አለ። ሆኖም እነሱ ወደሚሉት አቅጣጫ ባይሆንም ቅሉ።

በመጀመርያ ደረጃ፤ ለጃዋር ጥበቃ ያዘዘለት የኢትዮጵያ መንግስት ነዉ። እንዲህ ነገር ሲያጣልቅና ህዝብ ሲያበጣብጥ አንዱ ሰርኑን ብሎት ጦሱ ለሀገራችን እንዳይተርፍ በማለት። ወዲሁም እንደ ወያኔ ጊዜ መከራ አትቀበሉም ኑ አብረን እንስራ ተብሎ ጥሪ ለፖለቲከኞች ሲተላለፍ እንደ curtesy ወይም መተማመኛ ነገር ተደርጎ ነዉ የሚመስለኝ። ይህ ማለት የኢትዮጵያ መንግስት አላስፈላጊ ነዉ ብሎ ባመነ ጊዜ ያስቀመጠለትን ጥበቃ የማንሳት ሙሉ መብት አለዉ ማለት ነዉ። የጃዋርን ጠባቂዎች ማንሳት እንዴትም ሆኖ ቢፈተሽ የኦሮሞን ህዝብ መንካት ሊሆን አይችልም። ሆኖም ጃዋር አንደኛ ፈሪ ነዉ፤ ሁለተኛ ስራዉን ያዉቃል፤ ሶስተኛ አላማዉ ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳትና ለዉጡን አደጋ ላይ መጣል ነዉ፤ አራተኛ ከወያኔ ጋር ተባብሮ በሚስጢር ሲወያዩበት የከረሙትን ነገር ምንም ይሁን ምን ለማሳካት መሞከር ነዉ። እንዲህና እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ጃዋር በንግግሩ ዉስጥ የሀይማኖትና የብሄር ግጭት እንዲነሳ የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ ማለቱ ተዘግቦአል። ልብ በሉ።እነ ጂም ጆንስና ዴቪድ ኮረሽ ሲጀምሩ አፋቸዉ ቅቤ ይጠብስ ነበር። ሃይማኖተኞች ፤በጎ አድራጊዎች፤የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ነበሩ። በመጨረሻ ተከታዮቻቸዉን አጥፍተዉ ጠፉ።እኔ የምፈራዉ ጃዋር ይሀን የአካሄድ መስመር እየሄደበት እንዳይሆን ነዉ። የሰብአዊ መብት ተከራካሪ፤ ፖለቲከኛ፤ ለመንግስታችን እስትራቴጂ ቀያሽ፤ የቄሮ የጦር አዛዥ፤የሚዲያ ባለቤት፤ እሱ ሚሊየነር ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ለግሉ ሚዲያ ( የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ዎርክ)የገንዘብ ድጎማ ታድርግልኝ ብሎ የሚጠይቅ፤ለመጣል ታግየዋለሁ ከሚለዉ ህወሀት ጋር የታክቲክም ሆነ የእስትራቴጂ ልዩነት የለንም ማለት የጀመረ ወለወልዳ ነዉ። በዚያ ላይ እልም ያለፈሪ ፤ምንም ሳይሆን ድረሱልኝ የሚል፤ ስንኩል ሰዉ ነዉ። ያለዚያማ፤ የሀይማኖትና የብሄር ግጭት እንዲነሳ የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ ማለትን ምን አመጣዉ? እሱ አይደለም እንዴ ኦሮሞን ከእስልምና ጋር አያይዞ ስንት ቅስቀሳ ሲያደርግ የነበረዉ? የሃይማኖት ጦርነት የሚነሳ ከሆነ የጦር አዝማቹ ሀጂ ጃዋር መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳምሮ ያዉቀዋል።

እንግዲህ የጃዋር ሰራዊት የተወሰነ የቄሮ ክንፍ አብዛኛዉ ፖለቲካዉ በደንብ የሚገባዉ መሆኑ ያጠራጥራል። ለመሆኑ የሚያነቡት ባለ እእምሮ የጻፈዉ ነገር እጃቸዉ ይገባ ይሆን? ከጃዋር ፌስ ቡክ በቀር ሌላ የሚያዉቁት ነገር ይኖራል? አምባገነኖች ፤የከልት መሪዎች አነሳሳቸዉና አወዳደቃቸዉ ምን እንደሚመስል አንብበዉ፤ ሰምተዉ ያዉቁ ይሆን? ለአብዛኛዉ ጥያቄ መልሱ አያዉቁም ከሆነ እንግዲህ የምፈራዉ ይህንን ነዉ። እነዚህ መንገድ ከመዝጋትና ጎማ ከማቃጠል ሌላ ምንም የማይዉቁ ቦዘኔዎች፤ ጃዋር በብሄርም ሆነ በሃይማኖት የተነሳ ግደሉ፤ ሙቱ ቢላቸዉ ያላቸዉን ከማድረግ አይመለሱም። አሁንም ጀምረዋል። ያ ፤በጣም ያስፈራኛል።

 

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይባርክ።

Filed in: Amharic