>

ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤውን አቋረጠ!!! (ሀራ ዘ ተዋህዶ)

ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤውን አቋረጠ!!!
ሀራ ዘ ተዋህዶ
 
“እየተቃጠለንና እየተገደልን አንሰበሰብም፤ ልጆቻችን ያሉበት ሔደን እዚያው አብረን እንቃጠላለን፤ እንሞታለን”
ብፁዓን አባቶች
ሐረር ካራሚሌ እና በሮዳ ላይ ኹለት ክርስቲያን ወንድማማቾች ዐይናቸውን በማውጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል!!
— 
• በኦሮሚያ ልዩ ልዩ ከተሞች በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ በሚገኘው አስከፊ ጥቃት እና ግድያ ሳቢያ ቅዱስ ሲኖዶስ የምልአተ ጉባኤውን ስብሰባውን አቋርጠ
• የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለብዙኀን መገናኛዎች እና ለዓለም ኅብረተሰብ ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚያሰማውን መግለጫ እያረቀቁ ነው፤
• ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለመከላከያ ሚኒስትሩ እና ለሰላም ሚኒስትሯ ለመጨረሻ ጊዜ የሚደርስ ደብዳቤም እያዘጋጁ ነው፤
• በባሌ፣ በአርሲ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በድሬዳዋ እና በአዳማ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን፣ የአክራሪዎች እና ነውጠኞች ሰለባ እየኾኑ ነው፤ ቤታቸው እና ንብረታቸው እየተጠቃ ነው፤ አስከፊ እልቂት ማንዣበቡ ተገልጿል፡፡
አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ እና እየፈረሱ፣ ካህናት እና ምእመናን እየተገደሉ እና እየተደበደቡ፤ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ችግር ላይ ኾና እኛ እንዴት አስችሎን ቁጭ ብለን ጉባኤ ላይ እንቀመጣለን? በየአካባቢው ወርደን ችግሩን እንመልከት፣ መከራም ካለ አብረን እንቀበል፣ ማጽናናት ያለብንንም እናጽናና በማለት ለወትሮው ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ የነበረውን ጉባኤውን ለማቋረጥ ተገድዷል፡፡ በጉዳዩም ላይ ነገ ጧት መግለጫ ለመስጠት ወሥኗል፡፡
ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና በድሬዳዋ መጠነ ሰፊ ጥቃት በቤተ ክርስቲያን ላይ ተከፍቶ ውሏል፡፡
ጅማ ላይ የክርስቲያኖች የንግድ ተቋማት እየተለዩ እየተጠቁ ነው፡፡ እስካሁን ወደ ፲፩ የሚደርሱ ተቋማት ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡
ዶዶላ ላይ በዐራት አቅጣጫ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት አጥፊ ኃይል እየተመመ ነው፡፡ የክርስቲያኖች ቤቶች እየተለዩ እየተቃጠሉ ነው፡፡ ዶዶላ ከሻሸመኔ ፸፭ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የሚተኩሱት ወደ ሕዝቡ ሲኾን ለጽንፈኞቹ ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ እንደኾነ ታውቋል፡፡ ጥቅምት ፲፫ ላይም ረብሻው እንደከፋ ይገኛል፡፡
አርሲ ነገሌ የጥምቀተ ባሕር ቦታውን በመውረር በቦታው ላይ ተተክሎ የሚኖረውን መስቀል በመንቀል ወንዝ ውስጥ ወስደው ጥለውታል፡፡ ይሁን እንጅ የከተማው ኦርቶዶክሳዊ ሕዝብ ተጠራርቶ በመውጣት ሆ ብሎ የመጣውን መክቶ ወደየመጣበት በመመለስ ተነቅሎ የነበረውን መስቀል መልሶ በቦታው ላይ በመትከል መብቱን አስከብሮ አድሯል፡፡
ሐረር ካራሚሌ እና በሮዳ ላይ ኹለት ክርስቲያን ወንድማማቾች ዐይን እስከማውጣት በደረሰ ግፍ ተገድለዋል፡፡
በናዝሬት እና በደብረ ዘይት ውጥረቱ የረገበ ቢመስልም የስጋቱ ደመና እንዳንዥበበ መኾኑ ታውቋል፡፡
በባሌ ሮቤ ጻድቁ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ብቻ ስድስት ምእመናን መገደላቸውን ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተናግረዋል፤ አባት እና ልጅ በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ቦምብ ተወርውሯል፡፡
በድሬዳዋ ከበዓለ መስቀል በፊትም ኾነ በኋላ እንደነበረው ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን እየለዩ የማጥቃት እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ፍትሕ ለቤተ ክርስቲያን!!!
Filed in: Amharic