>
5:13 pm - Monday April 19, 1773

እነዚህ ኦሮሞዎች፣ እነዚህ አማሮች፣ እነዚህ ትግሬዎች…..! (ደረጄ ደስታ)

እነዚህ ኦሮሞዎች፣ እነዚህ አማሮች፣ እነዚህ ትግሬዎች…..!
ደረጄ ደስታ
እኔ ተሸንፌያለሁ እናንተስ? እንደኔው የተሸነፋችሁ፣ እንደኔው የፈራችሁ፣ እንደኔው የዘገነናችሁ፣ የየቀኑ ፍጅት ያመማችሁ፣ ታደርጉት ጠፍቷችሁ፣ እንደኔው ያፈራችሁ 24 ሰዓቱን የተዋረዳችሁ ኑ አብረን አንገት እንድፋ። ድል ነሺዎች ይፎክሩ ያቅራሩ። ይወቁ ይራቀቁበት። እኛ ቦቅቧቃ ፈሪና በኋቃ፣ እኛ ደናቁርቱ ዝም እንበል። ይስደቡን ያዋርዱን በእኛ ቅለት እነሱ ይክበዱ። ባይገባን የወላወልን፣ እንቆምበት ግራ ቢገባን አቋም ያጣን ወላዋዮች፣ ንቀትን ከትህትና የደባለቅን ዐያኖቻችንን ከፈጣጦች ደብቀን አቅርቅረን የቀበርን፣ ዘረኞች ላይ ዘረኝነት ያልቀስርን፣ በደም ፍላት ደም ያልታጠብን ብዙ ነን።
እዚህም እዚያም በእውቀት ብዛት፣ በሀሳብ ጥራት፣ በርግጠኝነት አብጦ፣ ደረቱን ገልብጦ አይኑን አፍጦ፣ አገር አስጎንብሶ ቀና ብሎ የሚሄደውን ልቅ ጥራዝ ነጠቅ፣ በቀቀን ባለቀን፣ ዋልጌ ባለጌውን ሁሉ መፍራታችን እውነት ነው።  ላገር ስንል ፈርተን፣ የተቀጨውን ለጋ ነፍስ አይተን ላልተቀጨው ትውልድ ስንል ወኔያችንን የቀጨን፣ ንግግራችንም ዝምታችንም እሚቆጨን፣ የባባን ግራ የተጋባን ድንጉጦች ሞልተናል። ጥሩ ነው አሁንም የበለጠውን እንፍራ። ስለ መቃጠላችን ግን እንጽናና! የገዳይነት ውድድር የጭካኔ ፉክክር ይቅርብን። አንድፈር። ይሉኝታ ቢሶች ይሉኝታችንን አይግደሉት። ህሊና ቢሶች አይርቱን። ትንሾች አያቅልሉን። የጠላ ገፈቱን የወተት ስልባቦቱን ገፈን እንደምንጠጣው የተስፋ አገር ጽዋችንን ፍቅር ሞልተነው እንጠጣ ዘንድ ገፈቱን እየገፈፈን ስልባቦቱን እየቀፈፍን ወዲያ እንጣለው። ስልባቦት አለው ተብሎ አገር አይደፋም። “በቃ እንዲህ ከሆነ አገር ራሷ ለምን ገደል አትገባም?” አንበል።
ለሚያልፍ ፖለቲካ እማታልፍ አገር አትርገመን። ለአገር መጮህ ግዴታ እንደሆነ ሁሉ አገር ላይ ከመጮህም ዝምታን መምረጡም ውለታ ነው። መፍትሔው እስኪገለጥ ዝምታም እርዳታ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የሚያውቅ ሰው እንዲናገር እድል መስጠትም ሊሆን ይችላል። ዝምታ ሁሉ እኮ ግደየለሽነት አይደለም። ቁጣህ ሊያፈነዳህ ስሜትህ ሊነዳህ ያልክ ወዳጄ ሆይ ትለው ዘንድ ካልተገለጠልህ መናገር የለብህም። አንዳንዴም አገርህን ትረዳ ዘንድ ለአፍታ እንኳ ዝም በል። ከዝምታህ ጥበብ ይመነጭ ይሆናል። አገር እሚያድን ጥበብ!
Filed in: Amharic