>
5:13 pm - Friday April 19, 9596

‹‹ ኩኩሉ…››ማለት ይቻላል አይደል? (በፍቃዱ ሞረዳ)

‹‹ ኩኩሉ…››ማለት ይቻላል አይደል?
በፍቃዱ ሞረዳ
የዉጭ ሀገር ዜግነት ባላቸዉ ሰዎች የሚተዳደሩ ሚዲያዎችን አስመልክቶ አቢይ አሕመድ ለኢሕአዴግ ፓርላማ ያሰሙትን ንግግር/ዛቻ፣ አንዳንድ ቅን ልቦች ‹‹ ጀዋርን የሚመለከት አይደለም›› እያሉ ሊያረጋጉ እየሞከሩ ነዉ፡፡ ‹‹ እንደአፋችሁ ያድርግልን›› እንላለን፡፡
     ደግሞም እንዲህ እንላለን፡፡
የአብይ አሕመድ ነፍስ በግራም በቀኝም፣ ከፊትም ከኋላም፣ ከዉስጥም ከዉጭም፣ በጠላትም በወዳጅም…ተወጥራ የተያዘች ናት፡፡ባተሌ ምስኪን ነፍስ፡፡
    የሰሜን አጋሮቻቸዉ  የአማራ ክልል ሹምምንትና አንዳንድ ሽፍቶች ጀዋርንም ሆነ ሚዲያዉን አስመልክቶ በይፋ እየተናገሩ ያሉትን ግምት ዉስጥ አለማስገባት ለአብይ ትልቅ ኪሳራ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ቢያንስ አጋሮቹን ማረጋጋት ይኖርበታል፡፡የመደመር ሐሳብ በገነነበት በአሁኑ ሰዓት ርቀዉ ያሉትን እነአብንን ለማቅረብም ማሽኮርመሚያ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
   ‹‹ ስለዚህ ሰዉዬ አንድ ነገር በል እንጂ…›› የሚለዉ የዉስጥ ግፊት ምን ያህል ሊበዛ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ እናም ከፓርላማ ስብሰባ የተወረወረዉ ቀስት በቀጥታ ጀዋር ሲራጅን የሚመለከት መሆኑን ሙትም አይስተዉም፡፡
     ጀዋርን በግል ማስፈራራትም፣ ሚዲያዉን መዝጋትም ይቻላል፡፡ አዲስ የሚቀሰም ልምድ የለም፡፡ ትናንት ሲደረግ የነበረዉን እንደገና መሞከር ነዉ፡፡እንደገና ከሠራ፡፡
 ጀዋር ሁለት ምርጫ አለዉ፡፡ አንድም የአሜሪካ ፓስፖርቱን ለባለቤቶቹ መልሶ ‹‹ ከዛሬ ጀምሮ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ እኔ ኦሮሞ ነኝ›› ብሎ ልበሙሉ ዜጋ ሆኖ ፊት ለፊት መጋተር ፡፡የሚያስፈልገዉንም ዋጋ ለመክፈል  ኅሊናዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ፡፡ ካልሆነም ሀገሩን ጥሎ በመዉጣት ላለፉት ዓመቶች ሲያደርግ እንደነበረዉ ትግሉን ከዉጪ መቀጠል፡፡
      ሁለቱም ምርጫ ለኢሕአዴግ መንግሥት የሚፈልገዉን እፎይታ ሊሰጠዉ አይችልም፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ ዉስጥ የጀዋርን ጎራ በመግፋት ሠላምን ማግኘት መቻል ባይታሰብ ይሻላል፡፡ ይህንን የምንለዉ ደጋፊ ከመሆን ሳይሆን መሬት ላይ ያለዉን ሀቅ ስለምናዉቅ ነዉ፡፡ ጀዋር ቢያንስ ቢያንስ ነፃ የአርሲ መንግሥት መስርቶ ማንም በዋዛ የማይነቀንቀዉን ባንዲራ ጭላሎ ላይ መትከል ይችላል፡፡
እናም… ከኦነግ ጋር ተላትሞ፣ ከእነጀዋር ጋር ተላትሞ፣ ከሕወሓት ጋር ተላትሞ፣ ከኦፌኮ ጋር ተኳርፎ …አንድን ወገን ብቻ አስደስቶ ዚያችን ሀገር ችግር ለመፍታት ማሰብ አዳራሽ ሙሉ ደጋፊን ሰብስቦ የማስጨብጨብን ያህል ቀላል አይደለም፡፡
  በተለይ በሚዲያ ጉዳይ በማንኛዉም ሰበብ የሚደረገዉን ተፅዕኖ መታገስ የማይቻለዉ ትናንት ነፃዉን ሚዲያ ሲያፍኑና ሲያሳፍኑ የነበሩ አንጎበሪያም ካድሬዎች አሁንም አርፈዉ ስላልተቀመጡ ነዉ፡፡ በጋዜጠኛ ጆሮ ላይ ስልክ በመዝጋት የጀግንነት ካባ የሚደረብላቸዉ ፀረ ዲሞክራሲ እንወደድ ባዮች ሞልተዋል፡፡ ሚዲያን ማፈን የዜጎችን ብሶት ማፈን ነዉ፡፡ ‹‹ስለቅማንት፣ ስለአፋር፣ስለሱማሌ፣… ለምን ትዘግባላችሁ ?›› ማለት ሳይሆን ‹‹ያልተመቸኝ ነገር አለ፣ጥያቄ አለኝ…›› የሚለዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተጠግቶ ማነጋገር ነዉ ሥልጡንነት ፡፡ ‹‹ አሸባሪ ነዉ፣ ፅንፈኛ ነዉ፣ክንፈኛ ነዉ›› እያሉ ከመፎከር፡፡ ሚዲያዉን ቀድሞ ቀዳዳዎችን መዝጋት፡፡ በርህን ክፍት አድርገህ፣ ነዉርህን አደባባይ አስጥተህ ‹‹ ሚዲያ እንዲህ አድርጎኝ…›› አትበል፡፡ ወይ ከሚዲያዉ ጋር ተባብሮ ለጋራ ዓላማ መሥራት…አለያም በማለቃቀስ መትጋት፡፡
      ለማንኛዉም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛቻ ማንንም ይመልከት ማንን ድርጅታቸዉንም፣  ደጋፊዎቻቸዉንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ለሁሉም በሚበጅ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ ያለመታከት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በግራ እጅ እየካቡ በቀኝ መናድ ኪሳራ ነዉ፡፡
    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን በጊዜ ብጫ ምልክት አሳዩን፡፡ እኛም ወደሀገራችን ተመልሰን በሚዲያ  ለሀገራችን በጎ አስተዋፅኦ ለማበርከት የጀመርነዉን ሥራ እንደገና እናየዋለን፡፡ ፕሮጀክታችንንም ወደ ዶሮ እርባታ እንቀይረዋለን፡፡የዉጭ ሀገር ፓስፖርት ይዞ ‹‹ኩኩሉ…›› ማለት ይቻላል አይደል?
Filed in: Amharic