>

‹ቃሌ!!!›› (ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ - የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር )

‹ቃሌ!!!››

ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ 
(የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር)
ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በ‹ዴሞክራሲ› ሥም ብረት-ነክሶ የወየነበትን ትግል በአሸናፊነት ከተወጣ በኋላ በነበረው ሥርዓት፣ ‹ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ፈቅጃለሁ› የሚል አዋጅ መለፈፉ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች ለህትመት መብቃታቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁንና አዋጁ የ‹ወረቀት ነበር› በመሆኑ፣ ጋዜጠኞች ላይ ከእስር እስከ መግደል የደረሰ ጭካኔ ለመፈፀም ከጥቂት ወራት ፈቀቅ ያለ ትዕግስት አልነበረውም፡፡ (የማስረጃው ዝርዝር በጣም ብዙ ስለሆነ ላለማሰልቸት እዘለዋለሁ)
ያም ሆኖ የነፃው ፕሬስ አባላት የተፈፀመባቸውን የተለያዩ ስቅየት በመቋቋምና መስዋዕትነት በመክፈል የሕዝብ፣ የአገር፣ የእውነት ወገንተኛ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡ እኔም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ይህንኑ አገር ለማዳን የሚተጋውን ፕሬስ ተቀላቅዬ የቻልኩትን ያህል ለማገዝ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም ‹ሐምራዊ መጽሔት›ን አቋቁሜአለሁ፡፡ በ2000 ዓ.ም ደግሞ በዚሁ ጉዳይ ዛሬ ተሰድዶ በሰው አገር እየተሰቃየ ባለው ወንድሜ አለማየሁ ማሕተመወርቅ ጋር ‹ዕንቁ› የተሰኘ መጽሔት መስርተን ለንባብ አብቅተናል፡፡
‹ሐምራዊ› ለአንድ ዐመት ያህል ከመታገዱ በስተቀር፣ ለአራት ዐመት ያህል ሲታተም ቆይቶ፣ በ2003 ዓ.ም የ‹ሐምራዊ›ን ፍቃድ መልሼ፣ ‹ሀበሻ ሪቪው› የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁሜ፣ ሕጋዊ ሂደቶች በሙሉ አልቀው፣ የመጀመሪያው ህትመት ሊወጣ ቀናት ሲቀረው ማንአህሎኝ የተጠናወተው ሕገ-ወጡ የሕወሓት መንግሥት አግዶታል፡፡ ‹ዕንቁ› መጽሔት› ደግሞ በ2006 ዓ.ም ወርሀ ነሐሴ በዘመቻ መልክ በኃይል እንዲዘጉና እንዲከሰሱ ከተደረጉት ስድስት ሚዲያዎች ጋር የተጠላው ሥርዐት ሰለባ ሆናለች፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም የሕወሓት የበላይነት የነገሰበት ሥርዓት ተባርሮ፣ በተለምዶ ‹ቲም ለማ› እየተባለ የሚጠራው የለውጥ ኃይል ሥልጣን ጨብጧል፡፡ ይህንን ተከትሎ፣ የእስር ቤት ደጃፎች ተከፍተው በግፍ የሚሰቃዩ አያሌ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ተፈትተዋል፡፡ ጠመንጃ አንስተው የነበሩ ተቃዋሚዎችም ለከፈሉት መስዋዕትነት፣ ለአደረጉት ተጋድሎ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፤ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲቀጥሉም ተደርጓል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተክተው የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይቅርታና ፍቅርን በተንተራሰው  የመደመር እሳቤ ግድያ የፈፀሙ፣ በመፈንቅለ-መንግሥት የተከሰሱ፣ በሙስና የተወነጀሉ ዜጎች ጭምር በነፃ እንዲለቀቁ በመደረጋቸው በኢትዮጵያችን ታላቅ መነቃቃት ፈጥሯል፤ ሕዝባችንም ተስፋ እንዲሰንቅ ገፊ-ምክንያት ሆኗል፡፡ በሺ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተመሰረተባቸው ክስ ተቋርጧል፤ በግፍ ተፈርዶባቸው ይሰቃዩ ለነበሩት ደግሞ ውሳኔው ተሸሮላቸው ከውዶቻቸው ጋር መቀላቀል በመቻላቸው ሕዝባቸውንና መሪዎቻቸውን አመስግነዋል፤ በአገራቸውም ኮርተዋል፡፡ እኔም ወደ ሁለት አስርታት ባገለገልኩበት ሙያ ዳግም ማገልገል የምችልበት እድል በመፈጠሩ ‹ግዮን› የተባለ መጽሔት መስርቼ አገሬንና ለውጡን በማገዝ ላይ እገኛለሁ፡፡
ይሁንና በ2006 ዓ.ም  መጨረሻ ከተዘጉት ስድስቱ ሚዲያዎች ጋር አብራ በተጨፈለቀችው ‹ዕንቁ መጽሔት› ስም በ2007 ዓ.ም መጀመሪያ የመሰረቱብኝ የፈጠራ ክስ፣ በድኀረ-ለውጡም በፍፁም ሊገባኝ ባልቻለ መንገድ በመቀጠሉ ጉዳዩን ለተለያዩ ባለሥልጣናት በአካልና በጽሑፍ ባስረዳም፣ በጉዳዩ ከመገረምና ከማዘን ያለፈ ሕገ-ወጡን ክስ በማቋረጥ እርምጃ ሊወስዱ አልቻሉም፡፡ መቀሌ የመሸገው ቡድን የመደባቸው እነዛው አቃቤ ሕግያን፣ ያንኑ የሀሰት ማስረጃ ቆጥረው በመክሰስ የቋጠሩብኝን ቂም-በቀል እንዲወጡ ክፍተት አግኝተዋል፡፡ እናም ዛሬ ለውጥ በመጣበት ወቅት፣ የግፈኞቹ ዋና አለቃ የነበረው ጌታቸው አሰፋና ግብረ-አበሮቹ በነፃነት በሚንቀሳቀሱበት አገር፣ በእኔ ላይ ያውም እነ ጌታቸው በሀሰት በመሰረቱት ክስ ፍርድ ቤት ስመላለስ ቆይቻለሁ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቃፊና ደጋፊ አካሄድ አሉታዊ ገፅ እንዳይኖረው በማሰብ፣ እንዲሁም ከነገ ዛሬ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል በሚል ጉዳዩን እኔ በምመራውም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች እንዳይዘገብ ስከላከል ቆይቻለሁ፡፡
ይሁንና በነገው ዕለት (11 ቀን 2012 ዓ.ም) መዝገቡን የያዘው ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ የቀጠረኝ በመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ስለ ጉዳዩ በይፋ እንዲያውቅ እና የደደቢቱ እንክርዳድ ቡድን የመሰረተውን የሐሰት ክስ በ‹ሪሞት ኮንትሮል› በማንቀሳቀስ ሚዲያውን በተዘዋዋሪ መንገድ ለማጥቃት የሚያደርገው ሴራ እንዲጋለጥ፣ ምናልባትም የመጨረሻ ሊሆን የሚችለውን ‹‹ቃሌ››ን በዚህ መልክ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡
የለውጥ ኃይሉም እንዲህ አይነት ደባ የሚፈፅሙ ‹‹የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች››ን ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ በመመንጠር፣ በንፁሐን ላይ የትላንትናውን መከራ ሊመልሱ የሚጥሩትን በፍጥነት አስቁሞ ነፃነቴን እንዲያስከብርልኝ እጠይቃለሁ፡፡ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የተከሰሱበትን የፈጠራ ወንጀላ እንዲቋረጥ ያደረገው መንግሥት ከእኔም ጎን በመቆም ፍትሕን እንዲያስከብር እጠይቃለሁ፡፡ በእኔ ላይ የሚጣለው የትኛውም ዓይነት “ፍርድ” በአሁኑ ወቅት በስደት የሚኖሩ በተመሳሳይ መንገድ የተከሰሱ ከአርባ በላይ ጋዜጠኞችንም ሥጋት ላይ የሚጥል እንደሆነ ሁሉም ሰው ልብ ሊለው ይገባል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሀሰት የተመሰረተብኝን ክስ እንዲያቋርጥልኝ፣ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንባቢያን ተቀባይነት ያገኘችው ‹ግዮን መጽሔት› ከመዘጋት እንድትተርፍ ያደርግ ዘንድ በአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ
Filed in: Amharic