>

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው ስብሰባ አሁን የደረስንበትን የትግል ምዕራፍ እና በፓርቲው ውስጥ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን በጥልቀት በመገምገም የፓርቲው ውስጣዊ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በቀጣይ ጊዜ የሚደረገውን ትግል ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡
ሰሞኑን የድርጅታችን ሊቀመንበር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸውን ተከትሎ መላው የኦሮሞ ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ያሳዩትን ድጋፍና የደስታ መግለጫ ፓርቲያችን በልዩ አድናቆት ይመለከተዋል፡፡ ይህ አለም አቀፍ ሽልማትም የድርጅቱ አመራርና የሕዝባችን የትግል ውጤት እንደሆነም ያምናል፡፡ በጋራ በምናስመዘግባቸው የድል ምዕራፎች በዚህ መልኩ የሚታዩ ድጋፎችና የደስታ መግለጫዎችም ለፓርቲው ቀጣይ የትግል አቅም እንዲሆን ይሰራል፡፡
ትላንት እንደ ፓርቲ ታግለን ድል እያስመዘገብን ዛሬ የደረስነው ከኦሮሞ ሕዝብና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ነው፡፡ አሁንም የኦሮሞ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይዘን በድል እንደምንሻገር ጥርጥር የለንም፡፡ የፓርቲያችንን የትግል እርምጃዎች እየቆጠሩ የሚያኮርፉና ስጋት የሚገባቸው ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን የሚፈጥሩ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ እኛ ደግሞ ባካበትነው የትግል ባህል ሕዝባችንን ይዘን የነሱን የውሸት ፕሮፖጋንዳና የማፍረስ ህልማቸውን የምናመክን መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
በዚሁ መሰረት የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፉት ሁለት ቀናት ስብሰባው ባካሄደው ግምገማ ላይ ተመስርቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ኦዲፒ ሕዝብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ የትግል ፓርቲ ነው፡፡ በትግል ጉዞው ውስጥ በሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ላይ በመመስረት ራሱን በማየትና በመገንባት ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባው ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ባለ መዋቅር ላይ የአመለካከት አንድነት ጉድለትን ከመሰረቱ በመቅረፍ የሕዝቡን ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ እየመለሰ መሄድ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚፈልገው መሆኑ ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡
እንደ ፓርቲና እንደ መንግስት የሚሰጥን ተልዕኮ በተቆርቋሪነትና በሕዝብ ወገንተኝነት መወጣትና በተጠያቂነት መንፈስ መንቀሳቀስን በተመለከተ ክፍተት እንዳለ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በአመለካከትና በተግባር አንድነት እንዲሁም በተጠያቂነት መንፈስ የሕዝባችንን ጥያቄና ፍላጎት መመለስ ወሳኝ መሆኑ ላይ ከመግባባት ተደርሷል፡፡ የውስጠ ፓርቲ የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጠናከር እስካሁን ምላሽ የተሰጠባቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን እንደ መነሻ፣ምላሽ ያላገኙትን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በመመልከት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቆጥረው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚታገል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች፣ብዙ ቋንቋና ባህሎች በሚገኙበት አገር ውስጥ የፌዴራሊዝም ስርዓት አማራጭ የሌለው ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት የብዝሃነትን ውበት በመንከባከብ የአገራችንና የሕዝባችን የጋራ ባህሎች መገንባትን የምናረጋግጥበት ወሳኝ መሳሪያ ነው፡፡ ስለሆነም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ትክክለኛና እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ስርዓትን በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ የአገራችንን ሕዝቦች እኩልነትና ነጻነት ለማረጋገጥ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት በአፈጻጸም የታዩ ተግባራት የፌዴራሊዝም ስርዓትን የአስተዳደር ባህልና እሴትን የሚቃረኑ ብዙ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ በግምገማ መድረካችን እንዳየነው ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሁሉንም ሕዝቦች በፍትሃዊነት እንደማያሳትፍ እውነተኛ ዴሞክራሲ በውስጡ ያልተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡
ከዚህም ሌላ የሕዝቡ ጥቅሞችና ፍላጎቶች  የመንግስትን ስልጣን እጃቸው ባስገቡት ጥቂቶች ሲጋጥ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እነዚህ ድክመቶች ታርመው እውነተኛ የብዝሃነት ፌዴራሊዝም ስርዓት መሬት እንዲይዝ የጀመረውን ትግል በማስቀጠል ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በነጻነት፣በእኩልነት፣በወንድማማችነትና በብልፅግና የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት ጠንክሮ እንደሚሰራ ይገልጻል፡፡
በሌላ በኩል ትላንት ትክክለኛው የፌዴራሊዝም ስርዓት መሬት እንዳይይዝ ሕዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች በያዙት የመንግስት ስልጣን ሕገመንግስቱንና የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ሲጥሱ የነበሩ ቡድኖች ዛሬ ራሳቸውን ለሕገመንገስቱ የቆሙና የፌዴራሊዝም ስርዓት ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን ለመፍጠር የሚነዙት የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኦዲፒ ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡
የኢህአዴግ ዉስጣዊ ሪፎርም የፓርቲዉን የትግል አካሄድ፤ የህብረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡ ይህም በሐዋሳ ከተማ በተደረገዉ የፓርቲዉ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በምሁራን ተጠንቶ እንዲቀርብና ዉሳኔ እንዲያገኝ አቅጣጫ የተሰጠበት ነዉ፡፡ የህዝቡ ጥያቄና የፓርቲዉ ዉስጣዊ ዉሳኔዎች በጥቅሉ  ሲታይ ፓርቲዉ በአደረጃጀቱ ፤ በዴሞክራሲዊነቱና፤ በአሳታፊነቱ እራሱን እንዲያይ የተሻለ ዕድል የፈጠረ ነዉ፡፡
የተደረገዉ ጥናትም የኢህአዴግ አመሰራረት ዴሞክራሲያዊና አቃፊ ያልሆነ፤ የሀገር ግንባታ አቅምን የሚሸረሽር ፣ ገሚሱን የሀገሪቱ ህዝቦች ወደ ጎን በመተዉ በጥቂት ቡድኖች የሚወሰን መሆኑ ተለይቷል፡፡
የኢህአዴግ አወቃቀር ሲመራበት የነበረዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝብን ዉሳኔ ሰጪነት የሚገድብ ስለሆነ ለደረስንበት የትግል መድረክ የሚመጥን አይደለም፡፡ ባለፉት ጊዜያት የነበረዉን የዝርፊያ መዋቅር ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፤ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙበት የነበረዉን መዋቅር በማፈራረስ፤ ዴሞክራሲና ነፃነት የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በኢህአዴግ አወቃቀር ላይ ሪፎርም ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ኦዲፒ ያምናል፡፡
በብዙ ጉድለቶች የታጠረዉ የኢህአዴግ አወቃቀር የኦሮሞንና የአገራችን ህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት ለመመለስ ያልተመቻቸ መሆኑን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተንትኖ ተግባብቶበታል፡፡
በዚሁ መሰረት ኢህአዴግን በማደስ፤ በዘመነ አሰራርና ስርአት የሚመራ ፓርቲ በመፍጠር፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብን በማስወገድ በመደመር ፅንሰ ሀሳብ ለመተካት ውይይት እየተደረገ መሆኑ የታወቃል፡፡
የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ያለፉትን ስኬቶች ይበልጥ በማጎልበት የሚታዩትን ጉድለቶች ከመሰረቱ በመፍታት የአዲሱን ትዉልድ መብትና ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆኑን ኦዲፒ ያምናል፡፡
በዚሁ መሰረት የኢህአዴግ ሪፎርም ጉዳይ እዉነተኛ የፌደራሊዝም ስርዓት ዴሞክራሲዊ ብሄርተኝነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛኑን ጠብቆ ብዝሀነት የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር በመገንባት የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የተመረጠ ዘዴ መሆኑን በማመን ለስኬታማነቱ ለመስራት ወስኗል፡፡
በመጨረሻም የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የተወሳሰበ ቢሆንም የፓርቲዉን ዉስጣዊ ድክመት በመቅረፍ ሰፊዉን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀዉን ፈተና በማሸነፍ አዲስ ታሪክ እንዲመዘገብ ለማድረግ የጀመረዉ ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አዲፒ የገልፃል፡፡
በኦዲፒ ስወሰኑ የነበሩ ዉሳኔዎችና ሲቀመጡ የነበሩ አቅጣጫዎች ህዝባችንን ድል እያጎናፀፉ ለዚህ ምእራፍ አድርሰዉናል፡፡ አሁን የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ህዝባችን በመስዋዕትነት የተጎናፀፋቸዉን ድሎች ጠብቆ እንዲያቆያቸዉና ተጨማሪ ድሎችን የሚያጎናፅፉት መሆኑን ተረድቶ ለአፈጻጸማቸዉ በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ ትውልድ አያሌ መስዋዕትነት የከፈለበት የሕዝባችን ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ እንዲያገኙ ከምንጊዜዉም በበለጠ የሚታገል መሆኑን ኦዲፒ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡
ተባብረን ከሰራን የማንወጣው ችግር አይኖርም !!
 ጥቅምት 2012
 የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ
 ፊንፊኔ
Filed in: Amharic