>
5:13 pm - Friday April 18, 1997

የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ለትህነግ መግለጫ የሰጠው ምላሽ!

የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ለትህነግ መግለጫ የሰጠው ምላሽ!
ደጀኔ አሰፋ
 
* ይህን ለውጥ በመቃወም በተፃራሪ የሚያጣጥል መግለጫ የሰጠው ቡድን (ትህነግ)  << ለውጡ መጣበት እንጅ ለውጡ አልመጣለትም ማለት ነው!!!
የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ 7 ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ የጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት የፕሬስ ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለ VOA Amharic ዛሬ ማታ ምላሽ ሰጥተዋል።
ትህነግ በትላንቱ መግለጫው “እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ አይችሉም ፣ ከተዋሃዱም ኢህአዴግን ከማፍረስ ባሻገር ሃገርን ያፈርሳል” ማለቱ ይታወሳል።
አቶ ንጉሱ ዛሬ በሰጡት ምላሽ  “በህወሃት የወጣው መግለጫ ለውጡ ከመጣላት ሳይሆን ከመጣበት ህዝብን የማይወክል አካል የወጣ ነው” ብለዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱም “መግለጫውን ያወጣው ቡድን በለውጡ ምክንያት የተቋረጠበት ጥቅም መኖሩን እና የነበረው ግፍ እንዲመለስ መመኘቱ ነው” ብለዋል፡፡
የኢህአዴግን የውህደት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ህወሃት በመግለጫው ያሰፈረውም ለዓመታት ሲያንፀባርቀው ከነበረው አቋም የተለየ እንደሆነ አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡አክለውም፥ ይህ የውህደት ሃሳብ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከ 7ኛ የድርጅት ጉባኤ ጀምሮ ሲብላላ የነበረና ለብዙ አመታት ውይይትና ጥናት ሲደረግበት የነበረ ነው ብለዋል። ይህ ውህደት አገራዊ አቅምን የሚጨምር እና የተሻለ ብሄራዊ መግባባትን የሚፈጥር ነው። በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።
አሁን የመጣው የለውጥ ሂደት መቶ በመቶ ሳንካ አልባ ባይሆንም በርካታ አወንታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ ነው። ይህ የለውጥ ሂደት ሁለት ነገሮች ላይ አበክሮ እየሰራ ነው።
1ኛ) ለሶስት አሰርት አመታት የቀጠሉ ችግሮችን ፣ ቁርሾዎችን ፣ የጥላቻ ትርክቶችን ወዘተ የማስተካከል እና ብሄራዊ መግባባትን የመፍጠር ስራዎችን ይሰራል ፤
2ኛ) የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ፣ የልማት ፣ የፍትሃዊነት ፣ የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን የመመለስ ተግባራት ላይ ያተኮረ ነው።
ይህን ለውጥ በመቃወም በተፃራሪ የሚያጣጥል መግለጫ የሰጠው ቡድን (ትህነግ)  << ለውጡ መጣበት እንጅ ለውጡ አልመጣለትም ማለት ነው። >> ብለዋል።
ይህ ቡድን (ትህነግ) የህዝብ ፍላጎት እያፈነ ፣ የራሱ ህዝብ ወደ አደባባይ እንዳይወጣ እየከለከለ መሆኑን እናውቃለን። ይህን ሁሉ የሚያደርገውና ለውጡን እየተቃወመ ያለው ጥቅሙ ስለቀረበት መሆኑም ይታወቃል።
በጣም የሚገርመው ይህ ቡድን (ትህነግ) ለሁለት አስርት አመታት አጋር ያላቸውን ድርጅቶች ወይም ዜጎች አይደላችሁም ብሎ በአጋርነት ፈርጆ ከፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጭነት ያገለላቸውን ድርጅቶች፣ ዛሬ ጥሪ እያቀረበላቸው ይገኛል በማለት አቶ ንጉሱ አግራሞታቸውን ገልፀዋል።
መተቸት ካለበት ከለውጡ በፊት የነበረው ፌደራሊዝም በትህነግ ብቻ የሚዘወር እና አሃዳዊ የነበረው ፌደራሊዝም ነው መተቸት የነበረበት ብለዋል አቶ ንጉሱ። ቀጥለውም << #የጡት_አባት ቀርቷል ፣ ህወሃት ብቻውን የሚዘውረው አሃዳዊ አገዛዝ አክትሟል >> በማለት እቅጩን ተናገርዋል።
በአጠቃላይ፣ አሉ አቶ ንጉሱ ፣ የህወሃት መግለጫ ከጊዜው ጋር የማይሄድና #ጊዜውን የማይመጥን መግለጫ ነው በማለት የህወሃትን መግለጫ አፈር ድሜ አብልተውታል። ይህ የጠ/ሚር ፅ/ቤት የሰጠው ምላሽ ግሩም ነው ማለት ይቻላል። የተለመደ አይነት አለመሆኑ አስደናቂ ነው።
ይህ የሚያሳየው በፌደራል መንግስት በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን እና ትህነግ ከዚህ ቀደም እምቧ ከረዩ ሲል ለማግባባት በሚል የሚደረግ ትርፍ እንቅስቃሴ እንደሌለ ነው። በአንፃሩ ትህነግም ይህን የፌዴራል መንግስት ቁርጥ አቋም በሚገባ የተረዳ ይመስላል። ለዚያም ነው ዛሬ ከመሼ በራያ ወረዳዎች ለሚገኙ ሚሊሺያዎች እና የልዩ ሃይል አባላቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
Filed in: Amharic