>

ቲም ዐቢይ Vs ቲም ለማ  (ሙሉአለም ገ.መድህን)

ቲም ዐቢይ Vs ቲም ለማ
 ሙሉአለም ገ.መድህን
ዐቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ከመሆናቸው በፊትም ሆነ ከሆኑ በኋላ በመንግሥታዊም ሆነ በፓርቲ አደረጃጀት ደረጃ ዕውቅና የሌለው ‹‹ቲም ለማ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ቡድን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስያሜው አቶ ለማ መገርሳ በኢህአዴግ ውስጠ-ግንባር መተጋገል ሂደት የተጫወቱትን ሚና ከኦሮሞ ትግል አኳያ ዋጋ በመስጠት የተቸረ ቢሆንም በውስጠ ድርጅት መተጋገል ሂደቱ የራሳቸው ጉልህ ሚና የነበራቸው የብአዴን አመራሮችና ከደኢህዴን ውስጥ እንደ ሙፈሪት ካሚል ያሉ አጃቢዎችም የ‹‹ቲም ለማ›› አካል መሆናቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ኦሮሞው የህዝብ ቁጥሩን ያህል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ያህል፣.. ወዘተ ድርሻና ስልጣን የለውም ከሚል ቁጭት የሚነሳው የ‹‹ቲም ለማ›› ፖለቲካ በሂደት የአካሄድ ልዮነት ገጥሞታል፡፡ ‹‹የኦሮሞው ብሔራዊ ጥቅም አልተከበረም›› በሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ የተቃኘው ትግል ስትራቴጅካዊ ባይባልም ታክቲካዊ የትግል ስትል ልዮነት እንዳሳየ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡
አቶ ለማ መገርሳ ከክልል ርዕሰ-መስተዳደርነታቸው ተነስተው ወደመከላካያ ሚኒስትር ካቀኑ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ በሚዲያ የታዪት ከሰኔ አስራ አምስቱ የባህርዳር እና የአዲስ አበባው ክስተት ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን ወክለው በሰጡት መግለጫ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሰማንያ ቀናት ሚዲያዎች ላይ ቀርበው  ማብራሪያም ሆነ መግለጫ ሲሰጡ አልታየም፡፡ (በቅርቡ የታየው የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ስምምነት መድረክ፣ ብዙ ትንታኔ የሚያስፈልገው ነገር ነው፤ ለማን ‹‹ጋቢሳ›› ውስጥ ልናገኛቸው የምንችልበት ጊዜ ስላለመቃረቡ ርግጠኛ መሆን አይቻልም) የሰውየውን ከተለምዷዊው ‹ሜን ስትሪም› ሚዲያ  መሰወር ከጤንነት ጋር ለማያያዝ የሞከሩ የኦህዴድ ካድሪዎች ቢኖሩም በክረምቱ አጋማሽ ለንባብ በበቃው ‹‹የተጠለፈ ትግል›› የተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደተመለከተው አቶ ለማ በትግል ጓዳቸው ሊቀመንበር ዐቢይ አህመድ እንደተካዱ፣ ትግሉም እንደተጠለፈ ሮሮ  በተጫነው ፖለቲካዊ ምሬት  ተዘግቧል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ‹‹የቀድሞው ኢህአዴግ ከነድክመቱ ይሻል ነበር›› ሲሉ መሰማታቸው የመከፋታቸውን ጥግ አመላክቷል፡፡
በግልጽ እንደሚስተዋለው ‹‹ቲም ዐቢይ›› ሊባል የሚችለው ቡድን ሽመልስ አብዲሳ፣ አዲሱ አረጋ፣ ብርሃኑ ጸጋየ፣ ታከለ ኡማ፣ ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣… የጠ/ር ዐቢይ አህመድ አጋር ሆነው ይታያሉ፡፡ በሂደት በኦሮሞ አምሳያ የተቀረጸች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን የሚለው ይሄ ስብስብ፣ የጸጥታውንና የደህንነት መዋቅሩ ይሁንታ ‹ከእጀ ሊወጣ አይችልም› የሚል በራስ መተማመን አለው፡፡ የምዕራባውያንን ድጋፍ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ጉልበት የሚቆጥረው ‹‹ቲም ዐቢይ›› በሀገር ቤት እንደፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የአቢሲኒያን የፖለቲካ ጥርስ የማራገፍ ራዕይ ያላቸው ኃይሎች ምንጣፍ ጎታቹ መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ ይመስላል፡፡ ላይ ላዮን ሲያዮት ለ‹‹ቲም ዐቢይ›› ስጋት ሆኖ የሚታየው ‹‹ቲም ለማ›› ቢመስልም ከጀርባው የተፈጠረውም ሆነ ሊፈጠር የሚችለው የፖለቲካ አሰላለፍ ዋነኛ የሥልጣኑ ስጋት ሆኖ ይታየዋል፡፡ ከሚዲያ ተጽዕኖ አኳያ ማህበራዊ መሠረቱን ሊነጥቀው የሚችለው ኃይል በባለሃብቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ አክራሪ ብሄረተኞች የሚመራ መሆኑ እንቅል የነሳው ይመስላል፡፡
‹‹ቲም ለማ›› የቀደመ ስብስቡን አራግፎ እንደ አዳነች አበቤ ያሉ አስታራቂ/ አሸማጋይ ፖለቲከኞችን ሳያንገዋልል በአመለካከት ደረጃ አክራሪውን ቡድን ለሃሳቡ መደርጀት መጠቀም ምርጫው ያደረገ ይመስላል፡፡ የታችኛውን የካድሬ መዋቅር የመቆጣጠር ፍላጎት ያለው ይሄ ስብስብ ማህበራዊ ሚዲያው የፕሮፖጋንዳ መዘውሩ አድርጎ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ የቤተ-መንግሥቱን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በመከታተል የመንጋ ውግዘትና እርግማን ሲያዘንብ የሚውለው ይሄ ኃይል እንኳንስ ለጠ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በሃያዎቹ መግቢያ ላይ የምትገኝ አንዲት ታዳጊ ላቀረበችው ግጥም አጸፋዊ ምላሽ ወደኋላ የማይል መደዴ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡
ከታሪክ አንጻር ከዛሬ ነባራዊ ሁኔታ እና ከመጭው ጊዜ አኳያ ነገሮችን የሚመለከተው “ቲም ለማ”፤ የኦሮሞ ሚና መነሻው በኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመናት ታሪክ ቢያንስ ደግሞ ባለፉት 150 ዓመታት የሰሜን ሰዎች እየተፈራረቁ የገዟት ሀገር ነች፡፡ አሁን ተራው የኦሮሞ ነው የሚል አቋም ይዟል፡፡ በአቋሙ ጥላ ስር እንደጃዋር መሀመድ፣ ሕዝቄል ጋቢሳ፣ ጸጋየ አራርሳ፣ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ አክራሪዎችን በማሰባሰብ የ‹‹ቲም ዐቢይ››ን እጅ በመጠምዘዝ ነገሮችን የማስፈጸም ፖለቲካዊ ዝንባሌ ይታይበታል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያና በግሉ የሚዲያ ዘርፍ ለሃሳቡ የበላይነት ያላሰለሰ ድጋፍ የሚደረግለት ‹‹ቲም ለማ›› ኦነግ ከያዘው የተገንጣይነት ዓላማም ሆነ ዛሬም ድረስ ብረትን እንደትግል መንገድ መያዙ ለሥርዓቱ አደጋ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ‹‹አጋር›› አድርጎ የማሰብ ፖለቲካዊ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከወራት በፊት የኦህዴድ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ የቲሙን መሪ በኦነግ አመለካከት ተሸካሚነት እስከመገምገም የደረሱት፡፡
‹‹ቲም ለማ›› የውጭ ሀገራት ድጋፍ አለው ለማለት ፈጽሞ ቢቸግርም በሀገር ውስጥ የህወሓት፣ የሲአን፣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዎሕዴፓ)፣ ድጋፍ ያለው ሲሆን፤ በደቡብ ብተና ሂደት ‹እናተርፋለን› ብሎ የሚያሰላ ስብስብ ነው፡፡ ስብስቡ ወደ ፓርቲ የመቀየር ዕድሉ ጠባብ ቢሆንም እንኳ ‹የኦሮሞ ጊዜው አሁን ነው› የሚለውን የታሪክ ግምገማ ገቢር ለማድረግ በጠቅላይነት ጉዞው የመበርታት ዝንባሌ ይታይበታል፡፡ በአንጻሩ ‹‹ቲም ዐቢይ›› ኦሮሞ ሃምሳና ስድሳ ዓመት የዘለቀ ጥያቄ ቢኖረውም አዳዲስ ጥያቄዎችንም ፈጥሮ በማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናው ሱታፌ ላይ እናተኩር የሚል አተያይ እንዳለው ሂደቱ ያሳያል፡፡ ያም ሆኖ የሁለቱ አረዳድ የታሪክ ሚናችንን መወጣት አለብን ከሚለው ጋር ተዛምዶ አለው፡፡ ልዩነቱ ‹‹ቲም ለማ›› ‹ጊዜው አሁን ነው›› የሚል ሲሆን ‹‹ቲም ዐቢይ›› ‹በሂደት እናሳካው› የሚል ነው፡፡ አሁናዊው የ‹‹ቲም ለማ›› ስብስብ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች (አክቲቪስቶች እና ታዋቂ የብሄሩ አርቲስቶች) የተወሰኑ የኦሮሞ ባለሃብቶች የቡድኑ አጋሮች ሆነው ይታያሉ፡፡ ‹‹ያሳደኩት እባብ ዘንዶ ሆኖ ሊውጠኝ መጣ›› በሚል ፖለቲካዊ መብሰልሰል ላይ የሚገኙት አባ ዱላ ገመዳ የዚህኛው ቲም ሃሳብ ደጋፊ ሆነው መታየታቸው አሰላለፉን የአባት እና ልጅ አስመስሎታል፡፡
ይህም ሆኖ ኦህዴድ በአንድነት መቆም ቢሳነውም በአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች እየተደረገፈ አንዳንዴም እየተገፋ ከጉዞው አልቆመም፡፡ የሁለቱ ቲም ልዮነት የታክቲክ እንጅ የስትራቴጂ ልዮነት የለበትም፡፡ ከኢህአዴግ ውህደት በኋላ የሁለቱ ተቃርኖ ምን ይዞ እንደሚመጣ አብረን የምናይ ይሆናል፡፡
Filed in: Amharic