>

የኦሮሞ ብሄርተኞች ትምክህት ምንድን ነው? (መስከረም አበራ)

የኦሮሞ ብሄርተኞች ትምክህት ምንድን ነው?

 

መስከረም አበራ

 

ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነዋሪቿን በሚያሳስብና በሚያሰጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡የዚህ ስጋት ዋነኛ ምንጭ ማን ነው?የሚለው ግን በውል የተመረመረ አይመስልም፡፡ይህን የስጋት ምንጭ መመርመር በሞት እና ህይወት መሃል የምትገኘውን ሃገራችንን ለማዳን ይጠቅማል፡፡ሃገራችን አሁን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ስጋት ዋነኛ  ምንጭ መለዘብም መብሰልም ያልቻለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ነው፡፡እንደሚታወቀው ሃገራችን የብሔር ፖለቲከኞች መናኸሪያ ከሆነች ከረምረም ብላለች፡፡ሆኖም በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ብሄርተኞች ከህወሃት መውደቅ በኋላ የቀደመ አክራሪነታቸውን ለዘብ አድርገዋል፡፡የመለዘባቸው ምክንያት ሃገሪቱ አሁን በምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ የአንድ ብሄርን ዳርቻ አልቦ ጥቅም ለማስከበር የሚሽቀዳደሙበት ሳይሆን ሃገሪቱ ራሷ የምትቀጥልበትን መንገድ የሚተለምበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነ በማሰብ ነው፡፡

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ‘ሃገር ከመገንጠል ሌላ ዓላማ የለውም’ እየተባለ በአፍራሽነት ስሙ ሲብጠለጠጠል እና ሲፈራ የኖረው ኦብነግ ነው፡፡ሆኖም ኦብነግን የሚመሩ የሶማሌ ልሂቃን ለውጥ መጥቶ ወደ ሃገርቤት ሲገቡ ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ኦብነጎች እነሱ ራሳቸው የሃገር ህልውና ፈተና ሊሆኑ ቀርቶ በህወሃት ዘመን በጎሳ ተከትፎ የነበረውን የሶማሌ ክልል አንድ የማድረጉን አስቸጋሪ ስራ ወደማገዙ ገብተው ለመልካም መስራት ጀመሩ፡፡ከክልላቸው አልፈው ለሃገር ሰላም ስፍነት አጋዥ እስከመሆን፣ብሄርተኝነታቸውን አብስለው ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ለመሆን እስከማቀድ ድረስ ደርሰዋል፡፡ በሃገር አጥፊነት ሲከሳቸው የነበረውን ቡድን አሳፍረዋል፡፡ኦብነግ ይህን ሁሉ ፖለቲካዊ ብስለት ያመጣው እንደ ኦሮሞ ብሄርተኞች የፌደራል ስልጣን ላይ የመቀመጥ መደለያ ሳይጠይቅ ነው፡፡

ኦብነግ በታሪክ ላይ ላላዝን ቢልም የኦሮሞ ብሄርኞች ከሚያላዝኑበት የሚበልጥ ምክንያት ያለው ድርጅት ነው፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች እዬዬ የሚሉበት የፊውዳሉ ዘመን የኢትዮጵያ አመሰራረት ቀርቶ ‘ብሄረሰቦችን ከእስር ቤት ፈትቼ ለቀቅኩ’ በሚለው ህወሃት የስልጣን ዘመን የሶማሌ ህዝብ ትልቅ በደል ደርሶበታል፡፡በህወሃት ዘመን የሶማሌ ህዝብ ወደ ዋነኛ የፌደራል መንግስት የስልጣን እርከኖች እንዳይወጣ በአጋር ድርጅትነት ስም ተሸብቦ ሁለተኛ ዜጋ ተደርጎ ኖሯል፡፡በክልሉ ሲፈፀም የኖረው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ራስ የሚያስይዝ እንደ ነበረ ዓለም ያወቀው ገመናችን ነው፡፡የሶማሌ ፖለቲከኞች ይህን እያነሱ ወደኋላ እያዩ ማልቀስ ሲችሉ ይህን አልመረጡም፤ሃገር ለዲሞክራሲያዊ መዳረሻ ለምታደርገው ጉዞ እንቅፋት መሆንን አልፈለጉም፤የሃገርን ህልውና በሚፈታተን መንገድ አልነጎዱም፡፡ይልቅስ የሃገራቸውን ህልውና የማፅናቱን ስራ ካገዙ በኋላ በመሃል ሃገር ፖለቲካ ተዋናይ መሆንን ያለመ የባለ አእምሮ እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

እንዲህ ያለውን የሱማሌ ብሄርተኝነትን ፖለቲካ የማብሰሉን ስራ የሚመሩት አቶ ሙስጠፌ ሌላው ቀርቶ በቤተሰብ ደረጃ ግፍ የተሰራባቸው ሰው ናቸው፡፡እንደ ክልል ላስብ ካሉም በጎጣቸው ሰዎች ላይ የሚሰቀጥጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ሆኖም እንደ ልጅ ወደኋላ እያዩ ከማልቀስ ይልቅ ወደፊት መራመዱ የተሻለ መሆኑን ተረድተው በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ከሚጠቀሱ ጠንካራ ዋልታዎች አንዱ ሆነው የሚቆጠሩ ሰው ሆነዋል፤የክልላቸው ህዝብም እንደዛው፡፡ዛሬ በሱማሌ ክልል አጣና ይዞ፣ጎራዴ ስሎ፣ድንጋይ ተሸክሞ ጎዳና የሚወጣ ጎረምሳ የለም፡፡ከዚህ የምንረዳው የጎራዴ እና አጣና ትርዒት በዘረኛ ፖለቲከኞች ልቦና ውስጥ ካልተጠነሰሰ የማንኛውም ጎጥ ጎረምሳ መግደያ ይዞ አደባባይ እንደማይወጣ ነው፡፡ስለዚህ የመጋደሉ ትርዒት ንድፈ ሃሳብ የሚያልቀው በጎጥ ፖለቲከኞች አእምሮ ጓዳ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ጉልበታቸውን የጎጣቸውን ጎረምሳ ይዞ በሚወጣው የመግደያ ቁሳቁስ ላይ በማስደገፉ የቀጠሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ብቻ ናቸው፡፡ይህ ደግሞ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ዋነኛ የሃገር ህልውና ስጋት አድርጓቸዋል፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች የሃገር ህልውና/ሰላም ስጋት ምንጭ ሆነው እንዲቀጥሉ ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡እነዚህን ምክንያቶች መርምሮ አካሄዳቸውን ማወቅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን የሚፈልገውን አብዛኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃገሩን ለማዳን በየት በኩል መሰለፍ እና  እንዴት መስራት እንዳለበት የሚጠቁም ይሆናል፡፡

ምክንያት አንድ፡የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና

እንደሚታወቀው በሃገራችን ከሁለት አመት በፊት የመጣውን ለውጥ ለማምጣት ትግል የተጀመረው ህወሃት ከጫካ ከተመልሶ ሃገራችንን የሚጎዱ የውጭ እና የውስጥ ወንጀሎች መስራት ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ነው፡፡ይህ በተግባር ሲገለፅ ደግሞ ህወሃት ሃገራችንን አንድ አይሉ ሁለት ወደቧን አስረክቦ ወደብ አልቦ ክርችም ቤት ካደረጋት እና በውስጥ አስተዳደሩም ዘረፋውን እና ማባላቱን አጠናክሮ ከቀጠለበት ዘመን አንስቶ በትቂትም በብዙም የተደረጉ ትግሎችን ያካትታል፡፡ከዚህ ዘመን ጀምሮ የሚደረገው ማንኛውም ትግል ህወሃትን ከስልጣን የማውረዱን ትግል ውሃ ያሞቀ ነው፡፡በዚህ ረዥም የትግል ዘመን ውስጥ ህወሃትን ለመጣል ፈርጀ ብዙ የማዳከም ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ህወሃትን በማዳከሙ ትግል ውስጥ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተደረጉትን ትግሎች የሚስተካለል የለም፡፡ ይህ ትግል የህወሃት ገበና በአለም ፊት ግልፅ ብሎ እንዲወጣ ያስቻለ፣በሃገር ውስጥም በህወሃት መራሹ አስተዳደር ስር ዲሞክራሲ እንደማይታሰብ ያስመሰከረ ትግል ነው፡፡ይህ እውነት ይገለፅ ዘንድ እስርቤት የገቡ፣ህይወታቸውን ያጡ፣የተሰደዱ፣የተገረፉ ሁሉ ህወሃነትን የመጣሉ ትግል እንዲበስል እንጨት ሆነው የነደዱ አርበኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች “ከአንድ ጀግና ዘር” የመነጩ የአንድ ጎጥ ሰዎች ሳይሆኑ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ ዜጎች ናቸው፡፡

የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በሃገርቤት ከአምባገነን መንግስት ጋር የተደረገውን ትንቅንቅ ለማገዝ በውጭ ሃገር ብድር እና እርዳታ የማስከልከል ዲፕሎማሲያዊ ፍልሚያም ተደርጓል፡፡ይህ ነገር አቶ መለስ እስከ ዕለተ ሞታቸው ሲያስቡት ቱግ የሚያደርጋቸው “በሃገራች ሰዎች የተሰራብን የኢኮኖሚ አሻጥር” ሲሉ ንዴታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው በግነው የሚገልፁት አመርቂ ትግል ነበር፡፡ በዛ አስፈሪ ወቅት በሃገር ቤት ውስጥ መንግስትን የሚተቹ ጋዜጣ እና መፅሄቶች መስርተው በነፍሳቸው ቆርጠው ህዝብን ሲያነቁ የነበሩ ዜጎች ሁሉ ህወሃትን የጣለው ትግል እንዲፈላ እሳት ያነደዱ ታጋዮች ናቸው፡፡

ይሄ ሁሉ እሳት ነዶበት የፈላው ህወሃትን የመጣሉ ትግል ላይ የመጨረሻውን ማገዶ የጨመረው የዛሬ ሁለት አመት በኦሮሚያ ክልል፣በአማራ እና በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ የታየው ትግል ነው፡፡እነዚህ ትግሎች የፈላ ውሃ እንዲገነፍል የሚረዳውን የመጨረሻ ማገዶ አስገቡ እንጅ በረዶ የነበረውን ትግል አቅልጦ ውሃ አድርጎ፣ውሃውን አፍልቶ ያገነፈለ ትግል ያደረጉ አይደሉም፡፡ይህ የመጨረሻውን ማገዶ የማስገባት ስራም ቢሆን የተሰራው ኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች በየደረሱበት እንደሚናገሩት በኦሮሞ ወጣቶች ብቻ አይደለም፡፡የአንድ ወገን የአንድ ሰሞን ትግል ለብቻው ህወሃትን የመሰለ ስር የሰደደ መንግስት ሊገለብጥ ከቶውን አይቻለውም፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዛሬ እንደሚያወሩት ህወሃትን ከውጭ የተገዳደረው የኦሮሞ ወጣት ፣ከውስጥ ደግሞ ኦህዴድ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሁለቱንም ድባቅ መትቶ መልሶ በመንበሩ ለመቀመጥ የሚከለክለው አንዳች ነገር አይኖርም ነበር፡፡

ህወሃትን ግራ ያጋባት በአጠቃላይ በሃገሪቱ የረበበውን ህወሃት በቃኝ የማለት አስፈሪ ሁኔታ ነው፡፡ይህ እንቅስቃሴ ስጋ ለብሶ መታየት የጀመረው የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን የመተግበር እንቅስቃሴን ተከትሎ በመጣው የኦሮሚያ ወጣቶች የተቃውሞ ትግል ቢሆንም ህወሃት በሃገሪቱ ምድር ውስጥ የቀድሞ አድራጊ ፈጣሪነቷ አብሯት እንደሌለ ያወቀችው ግን ጎንደር ተሻግራ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን እጁን ይዛ አምጥታ ማዕከላዊ መደብደብ እንደማትችል ከእውነቱ ጋር የተፋጠጠች ዕለት ነው፡፡

ይህ የህወሃት ስንፈተ-ጉልበት እውን የሆነው በብአዴንም ትብብር በመሆኑ ህወሃት በኢህአዴግ ላይ የነበራት የኖረ ጌትነት እንዳበቃ የመጀመሪያውን ፊሽካ የሰማችውም ከወደ ብአዴን ነበር፡፡ስለዚህ በትግሉ ወቅት አጓጉል ጀግንነቱ ሲወራለት የነበረው ኦህዴድ እምቢ ማለትን የለመደው ከብአዴን ነበር ማለት ነው፡፡ብአዴን ህወሃትን እምቢ ብሎ ምንም አለመሆኑን ያየው ኦህዴድም ተደፋፍሮ የውስጥ ትግል ጀመረ፡፡የኦህዴድ የውስጥ ትግል ጀማሪዎች የብአዴንን አጋርነት ብቻ ሳይሆን መከታነት ባያገኙ ኖሮ በህወሃት ጎራዴ ከመከተፍ እንደማይድኑ ዛሬ አደባባይ ወጥተው ሌላ የሚያወሩት የኦህዴድ ካድሬዎች ሳይቀሩ የማይክዱት ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ከተለያየ ወገን በተሰባሰበ ጉልበት የበሰለው ትግል ነው እንግዲህ ህወሃትን ጥሎ ዛሬ ላለንበት ቀን ያበቃን፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የኦሮሞ ብሄርተኞች ግን ህወሃትን ታግሎ የጣለው የእነሱ ዘር ወጣት  ብቻውን ትግሉን ጀምሮ እና ጨርሶ ያመጣው ጀግንነት አስመስለው ሲያወሩ የዕሩብ ምዕተ-ዓመቱን ህወሃትን የመጣሉን ትግል ወደ ስምንት ወር ትግል አሳንሰው ያቀርቡታል፡፡ የስምንቱ ወር ትግልም ቢሆን በኦሮሞ ወጣቶች ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ትግሉም እነሱ እንደሚያስቡት ከወደ ኦሮሞ ወጣቶች ብቻ በተወርውሮ ህወሃት የመሰለ ስር ሰደድ ክፉ ስርዓት ለመጣል የቻለ አይደለም፡፡

እውነተኛው ነገር ህወሃትን የመጣሉ ትግል ስኬቱን ያገኘው ከውስጠ-ፓርቲም ከፓርቲ ውጭ በህዝብ ትግልም ስለታገዘ ነው፡፡በሁለቱም የትግል መስመሮች የኦሮሞ ተወላጅ ብቻውን ታግሎ ያመጣው ድል የለም፡፡ለትግሉ ስኬት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሲያደርግ ሩብ ምዕተ አመት አሳልፏል፣በስተመጨረሻ የህወሃት የበላይነት ፍፃሜውን እንዲያገኝ ያደረገው ትግልም ቢሆን በኦሮሞዎች ብቻ የተደረገ አይደለም በሚለው ላይ ስምምነት ከተደረሰ ቀጣዩ ንግግር ማን የበለጠ ታግሏል የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚያዘወትሩት ነገር ይሆናል፡፡

ህወሃትን በመጣሉ ትግል ላይ አዘውትረው እና አበክረው ጎዳና ላይ በመውጣት ሲታገሉ የነበሩት የኦሮሞ ወጣቶች መሆናቸው የታመነ ቢሆንም ትግሉን ለፍሬ በማብቃቱ ረገድ የአማራ ወጣቶች በባህርዳር እና በጎንደር ጎዳናዎች ደማቸውን ማፍሰሳቸው መረሳት የለበትም፡፡ከህወሃት ስልጡን ወታደር ጋር ሊጋጠም ከአማራ ገጠራማ ቦታዎች  ጠመንጃውን አንግቶ ከመጣው የአማራ ገበሬ የህወሃትን ጉልበት በማራድ በኩል የነበረው ሚና ከኦሮሞ ወጣቶች ያነሰ ይሁን የበለጠ ወንበሯላይ የተቀመጠው ኦሮሞ ሆኖ ሳለ አማራን አምርራ የምትረግመው ህወሃት ታውቃለች፡፡በውስጠ-ፓርቲው ትግልም ቢሆን ከኦዴፓ እና ከአዴፓ የህወሃትን ግበዓተ መሬት ማን እንዳፋጠነው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ከሁለቱ ፓርቲዎች ማንን አምርራ እንደምትጠላ በማጤን የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ማንን አምርራ እንደምትጠላ ለማወቅ ደግሞ ሌላው ቀርቶ የአማራ ክልሉን ግድያ አስከትላ በማያገባት ገብታ ህወሃት ለአዴፓ የፃፈችውን ደብዳቤ ማንበብ በቂ ነው፡፡

ሲጠቃለል ዛሬ የመጣውን ለውጥ ለማምጣት የታገለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን የትግሉ ዘመንም የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደሚያስቡት ስምንት ወር ብቻ አይደለም፡፡ የስምንት ወሩ ትግል የፈላውን ትግል  የሚያገነፍል  አስተዋፅኦ አደረገ እንጅ ትግል አሙቆ፣አፍልቶ፣አገንፍሎ ህወሃትን የሚያስወግድ ማዕበል አላመጣም፡፡ይህ በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ይህ የስምንት ወሩ ትግልም ቢሆን በኦሮሞ ወጣቶች እና ፖለቲከኞች ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ዛሬ ያለ እነሱ ጀግና ያለ የማይመስላቸው፣አድራጊ ፈጣሪ የሆኑት የአትላንቲክ ማዶ የወንጭፍ ታጋይ የኦሮሞ ብሄርተኞች የኪቦርድ ጀግንነት ማዕከላዊ ገብቶ ከወጣ ዛሬ ስሙ ከማይነሳ አንድ ታጋይ ጀግንነት ይብለጥ ይነስ ማወዳደር የሚወዱት እነሱው እንዲበይኑት ልተወው፡፡

ስለዚህ ህወሃትን በመጣሉ ትግል ውስጥ የኦሮሞ ብሄረተኞች እና ወጣቶች ሚና እነሱ የሚያገዝፉትን ያህል እንደ ዝሆን የገዘፈ የሌላው ደግሞ እንደ አይጥ ያነሰ አይደለም፡፡በውስጠ ፓርቲው ትግል ውስጥ እንደውም የብአዴን ትግል እንደሚልቅ ግልፅ ነው፡፡አልተወራም ማለት የለም ማለት አይደለም፡፡ ለኦህዴዶች ህወሃትን እምቢ ማለትን ያስተማራቸው ብአዴን ነው፡፡ለዚህ ማመሳከሪያው ደግሞ የጎንደሩ የኮሎኔል ደመቀ ክስተት ነው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የኦሮሞ ብሄርተኞች ለራሳቸው እና ለጎሳቸው ወጣቶች ትግል የሚሰጡት የተጋነነ ጀግንነት እና የበለጠ የድል ባለቤትነት በራሱ ስህተት ከመሆኑ ባሻገር ብዙ ስህተቶችን እየወለደ ሃገራችንን ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየመራት ይገኛል፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች ስለጀግንነታቸው ደጋግመው የሚያወሩት ጎበዝ ተብለው እንዲጨበጨብላቸው፤ወይ የገዳይነት ሎቲ ጆሯቸው ላይ አንጠልጥለው የመሄድ ፈቃድ ብቻ እየጠየቁ አይደለም፡፡እንደዛ ቢሆን ኖሮ ለማንም አይከብድም ነበር፡፡

ነጋጠባ ጀግንነታቸውን የሚዘምሩብን፣በሃገሪቱ የተደረገው መልካም ነገር ምክንያቶች እነሱ እና የዘራቸው ወጣቶች እንደሆኑ የሚነግሩን ለበላይነታቸው እያመቻቹን ነው፡፡ ለጀግና እንደሚገባ ፈሪዎችን ቀጥቅጦ የመግዛት፣በልጦ የመኖር፣ተፈርቶ የመግዛት የይለፍ እንዳላቸው እየነገሩን ነው፡፡እሳቤያቸው በስሙ ሲጠራ ‘እኔ ጀግና ስለሆንኩ ከሌላው ጋር እኩል እኖር ዘንድ አይገባም፤ የበላይ እሆን ዘንድ ጀግነንነቴ ያዛል’ አይነት መልዕክት ነው፡፡ይህ ደግሞ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት የፖለቲካ ንቃት ደረጃ በእጅጉ ወደኋላ የቀረ፣ሃገራችንን አብረን የምንኖርባት የሰላም ሃገር ሳይሆን የምንተላለቅባት የደም መሬት የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡

ምክንያት ሁለት፡ የብዙ ቁጥር ነኝ ዕብሪት

የኦሮሞ ብሄርተኞች ሌላው መመኪያ የኦሮሞ ቁጥር በሃገሪቱ ካሉ ብሄረሰቦች ላቅ ማለቱ የበለጠ ጉልበተኛ ያደርገናል ብለው ማመናቸው ነው፡፡የዘር ፖለቲካ ባረበባት እና ህወሃትን በመሰለ ለምንም ማይታመን አስተዳዳሪ ስር በቆየችው ሃገራችን ውስጥ በህዝብ ቆጠራ ተደረሰበት የሚባለው የብሄረሰቦች ቁጥር ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ የሆነው  ሆኖ የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ከሌሎቹ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ላቅ ማለቱ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ላቅ ማለቱ የሚያስማማ ሆኖ የማያስማማው ግን ከተከታዩ የአማራ ህዝብም ሆነ ከሌሎች ብሄረሰቦች በምን ያህል ቁጥር ይልቃል የሚለው ነው፡፡በህወሃት ዘንድ ማነሱ እንጅ መጉላቱ የማይፈለገው የአማራ ህዝብ ሌላው በሚጨምርበት ሁኔታ ለብቻው ተለይቶ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ቁጥር እንደቀነሰ የተነገረውን ቁጥር ተቀብለን ብንሄድ እንኳን በኦሮሞ እና በአማራ ህዝብ መሃል ያለው የቁጥር መበላጥ የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚያወሩት አንዱን ጌታ ሌላውን ባሪያ ለማድረግ በሚደርስ ርቀት ላይ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ የህዝብ ብዛት አለመሆኑ ላይ መግባባት ቢቻል ደግሞ ይህ ሁሉ ባልመጣ ነበር፡፡

የህዝብ ብዛት ዋነኛ ነገር አለመሆኑን ለመረዳት በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ አንደኛ የሆነችው ናይጀሪያ እና በህዝብ ቁጥሯ አናሳ የሆነችው ሞሪሽየስ ያሉበትን የዲሞክራሲ እና የሰላም ሰማይ እና ምድር ማጤን ነው፡፡ከሃገር ቤት ልምዳችን እናውሳ ካልንም ዋናው ነገር የህዝብ ብዛት ቢሆን ኖሮ ባለ ብዙ ቁጥሩ ኦነግ ያላሳካውን የትጥቅ ትግል ድል ንዑሱ ህወሃት በአስራ ሰባት አመት ትግል ማሳካቱ ነው፡፡የኦሮሞ ናሽናሊስቶች ከዚህ ከቁጥራቸው መላቅ ጋር የሚያነሱት ክርክር ብዙ ችግሮችን ያዘለ ነው፡፡የመጀመሪያው ችግር በቁጥር ስለምንልቅ ኢትዮጵያን ዘለዓም መግዛት ያለብን እኛ ነን ሲሉ የኦሮሞ ስርወ-መንግስት መመስረት እንደሚገባ በአደባባይ የሚያወሩት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የዘለቁ የኦሮሞ ምሁራን ናቸው፡፡እነዚሁ ምሁራንም ሆኑ አውቃለሁ ባይ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ይህን ክርክር ይዘው ወደ ዲሞክራሲ መንደር ያቀናሉ፡፡በዚህ አካሄዳቸው የዲሞክራሲ መርሆ የሆነውን የሃሳብ ብዝሃነትን ከብሄር ብዝሃነት ጋር አዋቅተው ጥያቄያቸውን ከህገመንግስቱ፣ከፌደራሊዝሙ እና ከብሄር ፖለቲካው ጋር ፈትለው ያቀርቡታል፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች አሁን ያለው ህገ-መንግስትም ሆነ የብሄር ፌደራሊዝም አይነካብን ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡በህወሃት ዘመን የነበረው ችግርም ህገ-መንግስቱን ስራ ላይ ያለማዋል እና ፌደራሊዝምን ዲሞክራሲያዊ ያለማድረግ ችግር እንጅ ሌላ ስላልሆነ ህገ-መንግስቱ በስራ ላይ ይዋል፤ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን፤ይህ ከሆነ ሰላም ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ይህ ክርክር የራሳቸውን ምቾት ብቻ የሚያስጠብቅ አብሮ ለመኖር ቅንጣት ያህል ግድ የሌለው ነው፡፡ህገ-መንግስቱ በስራ ላይ ይዋል፣ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን ሲሉ ህገ-መግስቱ በስራ ላይ ከዋለ በፓርላማ ብዙ ወንበር መያዝ የሚችለው ኦሮሞ ሁልጊዜ ከስልጣን አይጥፋ ማለታቸው  ነው፡፡ፌደራሊዝሙ ዲሞክራሲያዊ ይሁን እንጂ አይነካ ሲሉም እንደዛው ኦሮሚያን አለቅጥ አስፍቶ የመተረው አከላለል ለእነርሱ የሚመች ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡ፌደራሊዝሙ ዲሞክራሲያዊ ይሁን የሚሉት ደግሞ የሃሳብ ብዝሃነት ያሸንፋል የሚለውን የዲሞክራሲ መርሆ ባለማወቅ ሳይሆን ሆን ብለው የብሄር ብዝሃነት ያሸንፋል በሚለው ትርጉም ተክተው የኦሮሞ ገዥነትን እና የበላይነት ዘላለማዊ ለማድረግ የሄዱበት የትም የማያደርስ መንገድ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኞች ህገ-መንግሰቱ በስራ ላይ ይዋል እንጅ አይከለስ፣ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን እንጅ አይነካካ የሚሉት በሁለቱም በኩል እነሱ በሚጠቀሙበት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ስለሚያውቁ ነው፡፡ከህወሃት ጋር ለቆ የማይለቅ ፍቅር የያዛቸውም ለወደፊቱ ስንገዛ የምንኖርበትን ሰፊ ግዛት የሸለመን፣ሽልማቱንም በህገ-መንግስት ያፀናልን እርሱ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ስለሆንም የማታ ማታ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከህወሃት ጋር ገጥመው ሃገር ለማጥፋት የማይመለሱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ህወሃት በበኩሉ እርሱ ከስልጣን ከወረደ ሃገር ከምትኖር ባትኖር የሚመርጥ፣ስልጣን የማጣት እልህ ምላጭ ሊያስውጠው የደረሰ ስብስብ ነው፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞችም የኢትዮጵያ መኖር አለመኖር እንቅልፍ አሳጥቶ የሚያሳስባቸው ነገር አይደለም፡፡እነሱን የሚወዘውዛቸው ኦሮሚያ አሁን በተንሰራፋችበት ስፋት እና ግዝፈቷ ላይ ከአማራ ክልል ቆረስ አድርጋ ወሎን፣ከወደ ምስራቅ ሃረርን፣በላዩ ላይ አዲስ አበባን፣ከዘም ራያን ጨምረው ከልለው ግዙፏን ኦሮሚያን መመስረት መቻል አለመቻላቸው ላይ ነው፡፡

ምክንያት ሶስት፡ የኦሮሚያ መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ

ካላይ እንደተጠቀሰው የኦሮሞ ብሄርተኞች አሁን ያለው ህገ-መንግስት እንዳይነካ የሚያስጠነቅቁት ህገ-መንግስቱ የሰፊ ክልል ባለቤት ስላደረጋቸው ነው፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞችን የሚያረካቸው የክልላቸው ስፋት ብቻ ሳይሆን ክልሉ የተቀመጠበትን ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ ስትራቴጅካዊ አድርገው ሲለሚቆጥሩት ነው፡፡በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ የኦሮሚያ ክልል ከሌላው ክልል የበለጠ ስትራቴጅካዊ ቦታ ላይ እንዳለ የሚያስቡበት አንዱ ምክንያት የሃገሪቱን መዲና አዲስ አበባን ከቦ በመዘርጋቱ እኛ ከተቆጣን ከተማዋን በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በአራት መዕዘን ዘግተን እንዳትተናፈስ ማድረግ እንችላለን የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ተመሳሳይ ምክንያታቸው ደግሞ ኦሮሚያ በሃገሪቱ መሃል ላይ ያለች በመሆኗ እኛ ከፈለግን የሃገሪቱ ሌሎች ክልሎች እንዳይገናኙ አድርገን መንገዶችን መዝጋት እንችላለን የሚል ነው፡፡

እነዚህ ክርክሮች እውነት መሆናቸው አያነጋግርም፡፡ የሚያነጋግረው ይህን ማድረግ የሚፈይደው ነገር ካለ የሚፈይደው የሌላው ኢትዮጵያዊ ትዕግስት እስካላለቀ ድረስ፣ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሃገርም እንደ ሃገር እስካለችና የኦሮሞ ፖለቲከኞች አበክረው የሚያነሱት ህገ-መንግስትም በስራ ላይ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ከፈረሰች በሃገሪቱ የሚነሳው ብጥብጥ ይህ ህገ-መንግስት የከለላትን ኦሮሚያን ሳይነካ በጎን በጎኗ እያለፈ የሚሄድ አይሆንምና ኦሮሚያ ቀርታ የግለሰብ መኖሪያ ቤትም የግል መሆኑ ያበቃል፡፡ በዚህ ሰዓት አዲስ አበባን እከባለሁ የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ራሳቸውን የሚያኙት በሌላው የኢትዮጵያ ክልል ተከበው ነው፡፡ በሰላሙ ጊዜ መሃል በመሆናቸው የኮሩበት አቀማመጥ ክፉ ቀን ሲመጣ መውጫው በጨነቀ እሳት መከበብ ማለት እንደሆነ አላሰቡትም፡፡አሁን ኦሮሚያ የሚባለውክልል መለኮት የከለለው ስላልሆነ ክፉቀን የመጣ ዕለት ያለው እንዳለ እንደማይቀጥል ማወቅ ከባድ ነገር ባይሆንም እየታሰበ ያለው ግን እንደዛ ነው፡፡

የኦሮሚያ መሃልነት የሚያኮራው ኢትዮጵያ በሰላም ውላ እስካደረች ድረስ ነው፡፡አዲስ አበባን መክበብ ማስፈራሪ የሚሆነው ኦሮሞ ተቆጭ ሌላው ታጋሽ መሆኑ እስኪያከትም ብቻ ነው፡፡ሌላውም የሰውልጅ ነውና ትዕግስቱ ያለቀ ዕለት አዲስ አበባን በመክበቡ የሚመፃደቀው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ራሱን በመላው የተቆጣ ኢትዮጵያዊ መሃል ያገኘዋል፡፡ ያኔ ህገ-መንግስቱ ይከበር ማለት የሚቻል ከሆነ ደርሰን እናየዋለን! ህገ-መንግስት በዋስትና የማይጠራበት፣ብዙ ቁጥርነት የማያመፃድቅበት ወቅት የመጣ ዕለት ማን የበለጠ እንደሚጎዳ ደርሰን እንየው ማለት አልፈልግም፡፡ስላልተፈለገ እንደማይቀርም ግልፅ ነው፡፡ሳይነገር መቅረት የሌለበት ነገር ግን አሁን የኦሮሞ ብሄርተኞች በያዙት አያያዝ ከቀጠሉ የጥፋቱ ዘመን ሩቅ እንደማይሆን ነው፡፡ ያየጥፋት ዘመን የመጣ ጊዜ ብዙ ቁጥር ያለው ዘር በገዳይ፣ትቂት ቁጥር ያለው ዘር በሟች መስመር እንደማይሰለፍ፤ሁሉም ለጥፋት እንደማያንስ በተግባር የምናይበት ይሆናል፡፡ያኔ ሁሉም እየገደለ የሚሞትበት እንጅ ብዝሃነት ያለውን ኦሮሞን ፈርቶ የሚንቀጠቀጥበት ወቅት እንደማይሆን እድሜም ሆነ ትምህርት ላላስተማረው ሁሉ ተግባር ያስተምረዋል፡፡

ምክንያት አራት፡የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጉልበት መመናመን

የኢትዮጵያ ብሄርተኝት ሰልፍ የተመናመነው ህወሃት ስልጣን ይዞ የዘውግ ፖለቲካን ህገ-መንግስታዊ እና መዋቅራዊ ካደረገ ወዲህ ነው፡፡ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት ፈርጆ የፖለቲካ ጥርሱን የነቀለው ህወሃት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚፈልግው እርሱ መንበረ ስልጣኗ ላይ ሆኖ መዝረፍ እስከቻለ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለመዝረፍ እንዲመቸው ደግሞ ህዝቦቿን በዘር ከፋፍሎ ማባላት ነበረበት፡፡ ያሰበውን በደምብ ለማሳካት ደግሞ ለኢትዮጵያ የማሰቡን በጎ እድል ተሳስቶ በደግ አንስቶት ለማያውቀው የአማራ ህዝብ አሸከመው፡፡ ስዚህ ኢትዮጵያን ማለት አማራ መሆን ማለት እስኪመስል ድረስ የታላቋ ሃገር የመኖር አለመኖር እጣ ህወሃት ሊያጠፋው ከቆረጠው የአማራ ህዝብ ጋር ተፈተለ፡፡ ህወሃት የአማራን አከርካሪ ሰበርኩ ሲል ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ሽባ አደረግኩ ማለቱ ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ማለቱ ያስጠቃው አማራም መዳን የሚችለው በሚያሳድነው አማራነቱ መደራጀት እንጅ የሞቱ መንስኤ በሆነው ኢትዮጵያዊነት አለመሆኑን ውሎ አድሮ በመረዳቱ ሳይወድ በግድ ወደ አማራነቱ መደብ ገባ፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትም በሞት ጥላ ስር ሆነ፡፡ይሄኔ የዘውግ ብሄርተኝነት በህገ-መንግስት ተደግፎ እናቱቤት እንዳለ ህፃን ሲዝናና ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሰልፈኛ እንደ እንጀራ እናት ሆነች፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ቅሪት ያለው በኢትዮጵያ ከተሞች ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሃገሪቱ ከተሞች ከገጠር በመጡ የዘውግ ብሄርተኝነት ምልምሎች ቁም ስቅላቸውም ያያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተሞች ያለ ስጋት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ያለበትን “የእልም ስልም” ኑሮ ያሳያል፡፡

እንዲህ ያለውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመጥፋት የተቃረበ መዳከም እንደ ድል የሚያየው ኢትዮጵያ በግድ እንደተጫነችበት የሚተርከው  የኦሮሞ ብሄርተኝነት ነው፡፡ከአክሱምጀምራ ስትሰፋ ሞያሌ የደረሰችውን ኢትዮጵያ “ነይልኝ” ብሎ ጋብዞ የተቀላቀለ ያለ ይመስል “ኢትዮጵያ መጥታ ተጭናብኛለች” በሚል የጫኝ ተጫኝ ተረክ የተገነባው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንደ ህወሃት ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ለአማራ ለመሸለም ይቃጣዋል፡፡ ስዚህ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ሰማይ ምድር የሚደፋበት አማራው ብቻ እንደሆነ ያስባል፡፡ አማራውን ግራ ማጋባት ካስቻለ ደግሞ ኢትዮጵያ ብትፈራርስም ለኦሮሞ ብሄርተኞች ችግር አይደለም፡፡

የኦሮሞ ብሄረተኞች ኢትዮጵያ ስትፈርስ  ኦሮሚያን እንዳትነካ ተጠንቅቃ ይመስላቸዋልና ኢትዮጵያ ብትፈርስም ኦሮሚያ በፍፁም ሰላም ውስጥ የምትኖር አድርገው ያስባሉ፡፡ኢትዮጵያ ስትፈርስ ትልቁ ስባሪ ኦሮሚያ ስለሆነ፣ትልቁን ድርሻውን ይዞ ለመሄድ ያሰፈሰፈው የኦሮሞ ብሄርተኛ በርካታ ነው፡፡ እዚህ ላይ የተረሳው ነገር ሃገር ሲፈርስ የሃገር ስብርባሪ ለመካፈልም ጊዜ እንደሌለ ብቻ ሳይሆን በመፋረስ ሁኔታ ውስጥ ሁሉም ለራሱ ብዙ ለመውሰድ የሚሮጥ፣ መግደል የሚገባውን የሚገድል፣ማጥፋት የሚገባውን የሚያጠፋ ጉልበታም እንደሚሆን ነው፡፡

ምክንያት አምስት፡የኦሮሞ ብሄርተኝነት ንረት

የኦሮሞ ብሄረተኝነት ስኬት ባያጅበውም የኖረበት እድሜ ከሁሉም በሃገራች የሚንቀሳቀሱ የዘውግ ብሄርተኞች የሚልቅ ነው፡፡ይህ የኖረበት ረዥም እድሜ ስኬት ቢርቀውም የተበድየ ፖለቲካን በህዝብ ዘንድ ለማስረፅ ግን ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ በመሆኑን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከማደግ አልፎ ወደ አክራሪነት ተመንድጓል፡፡ይህ ዝንባሌ ከሁለት አመት ወዲህ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ለስልጣን የማብቃቱ ድል የእኔ ነው ከሚለው የድል አድርጊነት ስሜት ጋር ሲደመር የብሄርተኝነቱ ንረት ወደ አደገኝነት እንዲነጉድ አድርጎታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከማንኛውም ብሄረተኝነት በሚልቅ መልኩ እንደ አንድ ሰው የሚነጋገር እና የሚግባባ፣ተነስ ሲባል አፍታም ሳይቆይ የሚነሳ ሆኗል፡፡ይበልጥ አሳሳቢው ነገር ደግሞ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ቁጭ ብድግ የሚያደርገው ጃዋር የተባለ ግለሰብ መረጋጋት ያልጎበኘው፣ሃላፊነት የማይሰማው፣የሚፈልገው ነገር ገደብ የለሽ  መሆኑ ነው፡፡በዚህ ሰው የሚመራው አደገኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትክክለኛው የኦሮሞ ህዝብ ትግል ትርጉም ተደርጎ እየተወሰደ  ነው፡፡ በዚህ ትግል እሳቤ መሰረት ደግሞ ኦሮሚያ ወሎንም፣ሃረርንም፣ድሬዳዋንም፣አዲስ አበባንም ጠቅልላ መግዛት አለባት፡፡በነዚህ ግዛቶች የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በኦሮሞ ገዥ ፀጥ ለጥ ብለው፣እንዳች የፖለቲካ ጥያቄ ሳያነሱ ለመገዛት ካልፈለጉ ወደ መሄጃቸው መሄድ እንዳለባቸው ያምናል፡፡ አልፎ ተርፎ ኦሮሞ ያልሆኑ ብሎ ያሰባቸው የሃገራች ዜጎች ወደ ሃገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ መግባት አለመግባታቸውን በሰላሌ ኦሮሞ ጎረምሶች በኩል መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ይህ እሳቤ ሃገሪቱን እየመራ ያለውን ኦዴፓ የተባለ ፓርቲ ከሞላ ጎል አዳርሶ፣ይህ ፓርቲ የሚመራውን የመንግስት ክንፍ በአመዛኙ በቁጥጥሩ ስር ከማስገባቱ የተነሳ ህግ አስከባሪ አካላት ሳይቀሩ በጃዋር ከሚታዘዙ ጎረምሶች ጋር መንገድ በድንጋይ ዘግተው በዘጉት መንገድ ላይ ጠመንጃቸውን ወድረው መታየት ጀምረዋል፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት እያደር መክረሩ ሳያንስ በአንድ ሃላፊነት የማይሰማው ሰው እጅ ተጠቃሎ እየገባ መሆኑ ነገሩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡የሚብሰው አደገኛ ነገር ይህ ብሄርተኝነት የሚያመጣው እልቂት የሚጎዳው ራሱን ኦሮሞውን ጭምር መሆኑን የብሄርተኝነቱ መሪ የተረዳው አለመሆኑ ነው፡፡ ከላይ እንደተቀመጠው የኦሮሞ ብሄርተኝነት በዚህ አናናሩ ቀጥሎ እኔ ብቻ ነኝ ነፃነት የሚገባኝ፣እኔ ብቻ ነኝ የመብት ያለኝ፣እኔ ብቻ የፈለግኩት እና ያልኩት ነው በሃገሪቱ መሆን ያለበት በሚለው አካሄዱ ከቀጠለ ሃገሪቱ ወደ ተሟላ ውድቀት ማዝገሟ አይቀርም፡፡ ይህ ውድቀት በሚያስከትለው እልቂት ጃዋር  የእልቂቱ አሰናጅ እንጅ የመራራው ፅዋ ተካከፋይ እንደማይሆን ግልፅ ነገር ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት መዘውር በአንድ ሃላፊነት የማይሰማው ሰው እጅ ተጠቃሎ መግባቱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ ብሄርተኞቹ ግን የአደገኛው እንቅስቃሴ በአንድ ሰው የሚከፈት የሚዘጋ መሆኑን እንደ ትምክህት ወስደውታል፡፡ሃገሪቱን በአንድ ቀን ቀጥ ማድረግ እንደሚችሉ ያስፈራራሉ፡፡በአንድ የማህበራዊ ድረ-ገጸ መልዕክት የጎጡን ጎረምሳ ለጥፋት መሰለፍ መቻሉን እንጅ ይህ ጥፋት ትእግስቱን አስጨርሶ ለሌላ ጥፋት የሚያስነሳው የሌላ ጎጥ ጎረምሳ እንዳ ለጊዜው ዘንግቶታል፡፡ለጥፋት መታጠቁ ሌላ ጥፋት አምጥቶ ሃገር ሲነድ እሱ ባህር ማዶ ቁጭ ብሎ የእኛን እውነታ እንደ ፊልም እስካላየ ድረስ ሌላም ቤት እሳት እንዳለ መረዳት አልቻለም፡፡

ምክንያት ስድስት፡የኦዴፓ ወቅታዊ አቋም

በአሁኑ ወቅት በሃራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የማይተነበይ፣በምን ሰዓት ምን አይነት ችግር ይዞ እንደሚመጣ የማይታወቅ ነው፡፡ችግሩን የሚያብሰው ደግሞ ሃገሪቱን የሚመራው ኦዴፓ የተባለው ፓርቲ ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ ከውጭ ሆኖ ለሚያስተውለው እጅግ ግራ የሚያጋባ መሆኑ ነው፡፡የሃገሪቱን የአመራር መንበር በአመዛኙ የያዘው ኦዴፓ ዋና ባለስልጣናቶቹ ሳይቀሩ ሃገር እግር በራስ የሚያደርግ ንግግር በአደባባይ የሚናገሩ፣በማህበራዊ ድረገፅ የሚፅፉ ናቸው፡፡ይህ ንግግራቸው ኦዴፓ የተባለው ፓርቲ እስከ ሞት አብረን እንዘልቃለን ካሉት አዴፓ ጋር ጭምር ወደ ለየለለት ግብግብ ውስጥ ሊነክራቸው የሚችል ነው፡፡ይህ ማለት የሃገር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡በዋናነት እነዚህን ሁለት ፓርቲዎች (አዴፓ እና ኦዴፓን) ተማምኖ ሃገር ይድናል ብሎ ያሰበው ህዝብ የኦዴፓ ባለስልጣናት ጃዋርን እየመሰሉት ሲሄዱ ቢመለከት “የምንመራው በጃዋር ነው” እስከማለት ደርሷል፡፡በጃዋር መመራት ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ አይነገርም፡፡

አደባባይ ወጥተው እንደ ጃዋር የሚያወሩ የኦዴፓ ባለስልጣናት ለሃገር መኖር አለመኖር ግድ የሌላቸው፣በኦዴፓ ውስጠ የመሸጉ የጃዋር ሰልፈኞች እንደሆኑ ህዝብ መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ያውም እጅግ አደገኛ በሆነ ፈታኝ ወቅት ሃገር የማስተዳደር ትልቅ እምነት የተጣለበት ኦዴፓ አብዛኛው ባለስልጣናት መታመን የማይከብዳቸው መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡የሃገር ህልውና ከኦሮሙማ ህልም የበለጠ የሚያሳስበው የኦዴፓባለስልጣን ምን ያህሉ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አይቻለም፡፡ሌላው ቀርቶ ለውጡ ሲመጣ በሰፊው ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ወደ ስልጣን ለመቅረብ ከተላበሱት ገፀ-ባህሪ ጋር አብረው ይኑሩ ከገፀ ባህሪ ይውጡ ለማወቅ በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ናቸው፤በኦህዴድ ውስጥ የጃዋር ሰልፈኛ ላለመሆናቸውም አፍ ሞልቶ መናገር ያዳግታል፡፡

የፌደራል መንበረ ስልጣን በያዘው ኦዴፓ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አቋም ዝብርቅርቅ ሃገሪቱን ወደመቀመቅ ይዞ እንዳይወርድ ያሰጋል፡፡ስልጣን ወደ እጃቸው ስትቀርብ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ያሉት ኦህዴዶች ውለው አድረው የሃገር ፈተና እየሆኑ ነው፡፡ሃገር በሚመራው ኦህዴድ ውስጥ ሃገር ለማዳን ሲባል የሚወሰድ አንድ የፖለቲካ አቋም በሌለበት ሁኔታ፣ጭራሽ ከመሃከላቸው ኢትዮጵያን ለማዳን የሚሰራ አንድስ እንኳን ሰው ሲገኝ በአማራ አሽከርነት ተፈርጆ ከየ አቅጣጫው ጦር የሚመዘዝበት ከሆነ ሃገሪቱ ያለችበትን ችግር መገመት አያዳግትም፡፡በግሌ ኦህዴድ ወደ ስልጣን ሲቃረብ አእምሮየን ሞልቶት  የነበረው ጥያቄ “እውን ኦህዴድ ኢትዮጵያን መምራት የሚፈልገውን ስፋት ሰፍቶ ሃገር ማዳን ይችላል ወይ? በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ስር የሰደደው የኦሮሙማ መንፈስስ እንዲህ በቀላሉ የሚነቀል ነው ወይ?” የሚለው ነገር ነበር፡፡ኦሮሙማ የሚለውን ጠባብ ጥብቆ የለመደ ቡድን ሃገር የሚያክል ስፋትን ከመቅፅበት ሊያመጣው አይችልም፡፡ ቢያመጣው እንኳን ሁሉም በኦዴፓ ውስጥ ያለ ፖለቲከኛ በአንዴ ሊያመጣው አይችልም፡፡ በዚህ መሃል ቀድሞ በኢትዮጵያ ልክ የሰፋ አስተሳሰብ ማምጣት የቻለው ጥቂት ቡድን ከየአቅጣጫው በሚወረወር ጦር መቁሰሉ አይቀርም፡፡ቁስለቱ ይህን ቡድን በሚገድለው ደረጃ ከበረታ የሃገራችን እጣ ፋንታም አሳሳቢ ይሆናል፡፡

በገልፅ ለማስቀመት በአሁኑ ወቅት በኦህዴድ ውስጥ ብዙ አይነት  የፖለቲካ ሰልፈኛ አለ፡፡አንደኛው ሃገር እግር በራስ ብትሆን ግድ የማይሰጠው ሲሆን ሁለተኛው ሃገር እጁ ላይ እንዳትፈርስ የሚቸገረው ቡድን ነው፡፡ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ መሆኑም የሚያምረው ኦሮሙማንም ለመተው የሚቸግረው ወላዋይ ነው፡፡ሶስስተኛው የኦሮሞ የበላይነትን ያሰፈነች ኢትዮጵያን መገንባት የሚፈልግ ነው፡፡ኦህዴድ እንዲህ ባለው ድብልቅልቅ ሰልፈኛ መከፈሉ ለአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሌላው ትምክህታቸው ነው፡፡ሃገር በሚመራው ኦህዴድ ውስጥ ቀላል የማይባል ሰልፈኛ ማሰለፋቸው የመንግስትን ስልጣን እንደ መቆጣጠር ሳይወስዱት አልቀሩምና በሃገሪቱ ውስጥ ሁሉን ማድረግ የመቻል እብሪት እየተሰማቸው ነው፡፡

አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከላይ የተጠቀሱትን ዋነኛ ሁኔታዎች እንደ መመኪያ ወስደው የሃገራችንን ፖለቲካ ወደ ፈለጉበት አቅጣጫ ለመውሰድ በማናለብኝት ሲንቀሳቀሱ ሌላው ኢትዮጵያዊ መታገስን መርጧል፡፡ይህ መልካም ውሳኔ ቢሆንም የኦሮሞ ብሄርተኞችን እንቅስቃሴን በማጤን እና አካሄዳቸው ሃገርን እንዳያጠፋ ለመግታት የሚያስችል መስመር ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት በኦዴፓ ውስጥ ያለውን የሃይል አሰላለፍ አንድ ወጥ አለመሆኑን ተረድቶ በጅምላ ከመውቀስ መቆጠብ ነው፡፡ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ማንም ከማን የማይበልጥባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር  የሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች ተሰባስበው ተጨባጭ የሆነ ህብረት መፍጠር ነው፡፡ይህ ህብረት የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጎራ ሆኖ ሲፈጠር የኦሮሞ ብሄርተኞች ትምክህት የሆነው የብዙ ቁጥር ትርክት ውድቅ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን የሚፈልገው ኢትዮጵያዊ አለመመሰባሰቡ እንጅ ኦሮሞ የገነነባት ኢትዮጵያ እውን ትሁን ይሁን ከሚለው ቡድን እንደሚበልጥ እርግጥ ስለሆነ ነው፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን የሚፈልግ ኦሮሞም በርካታ ስለለሚሆን የልብለጥ ባይ ኦሮሞዎችን ግማሽ እውነት ከሆነው ትርክታቸው ጋር ለብቻቸው እንዲቀሩ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ካልሆነ የሚከሰተው ነገር ሃገራችንን እንድናጣ የሚያደርግ አደገኛ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ይህ አደገኛ ነገር እውን የሚሆነው በሃገሪቱ ለእኩልነት የሚሰራ አካል የለም ተብሎ ተስፋ መቁረጥ ላይ ከተደረሰ ነው፡፡እንዲህ ያለው ተስፋ ማጣት በሃገራችን የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች የኦሮሞ ብሄርተኝነት አሁን እየሄደበት ባለው መንገድ ተጉዘው የየዘውጋቸውን ደህንነት ከኦሮሞ ብሄረተኞች የበላይነት ለማዳን በተናጠል መንቀሳቀስ እንዲጀምሩ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እልህን አዝሎ የሚመጣ የመጨረሻ እንቅስቃሴ ስለሚሆን ከዚህ ውስጥ ሃገር በሰላም ትወጣለች ብሎ ማሰብ ዩጎላቪያ ተመልሳ ሃገር ትሆናለች ማለት ነው፡፡ከዚህ ለመዳን በአሁኑ ወቅት ያለውን የሃገራችንን የፖለቲካ ሃይች አሰላላፍ በእርጋታ ማጤን፣በተለይ የኦሮሞ ብሄርተኘነትን አደገኛ ጉዞዎች ለመግታት በተናጠል ከመሮጥ ይልቅ መተባበር ያስፈልጋል፡፡

Filed in: Amharic