>

እውነትም ስምን መላክ ያወጣዋል - ደጀን ከተማና አካባቢዋ ያሳዩት ኢትዮጵያዊነት! (ግርማ በላይ)

እውነትም ስምን መላክ ያወጣዋል – ደጀን ከተማና አካባቢዋ ያሳዩት ኢትዮጵያዊነት!

ግርማ በላይ 

የአንዳንድ ስያሜዎች እውናዊ ልጨኛነት የሚገርም ነው – የአንዳንዶች ደግሞ ከማስገረምም አልፎ በለበጣ የሚያስፈግግ ነው፡፡ “ዐመለ ወርቅ” ተብላ ነጭናጫ፣ “ሽመክት” ተብሎ ባንድ ጥፊ የሚዘረር፣ ደም መላሽ ተብሎ ከእናትና አባቱ ገዳይ ጋር በጎን ተመሳጥሮ ባንድ መሸታ ቤት አሥረሽ ምቺው የሚል ወስላታ… የመኖሩን ያህል እንደስማቸው “አለልኝ”ና “ድጋፌ” ሆነው ለተመካባቸው ሰው ደጀንና ከለላ የሚሆኑ ድንቅ ዜጎች አሉ፡፡ እርግጥ ነው ስም አይገዛምና በስም ዙሪያ ብዙ ተቃራኒ ነገሮች መኖራቸው እውነት ነው፡፡

የአባይን በረሃ ተሻግረን ለደብረ ማርቆስ 70 ኪሎ ሜትሮች ያህል ሲቀሩን አፋፍ ላይ የምናገኛት ደጀን ከተማ እንደስሟ ለወገኖቿ ደጀን መሆንዋን የተረዳንበት የሰሞኑ ዜና እውነትም በአባት ግዕዝ “ስም ይቀድሞ ለነገር” የተባለውንና ልጁ አማርኛም “ስምን መልኣክ ያወጣዋል” የሚለውን የመሳሰሉ ነባር ብሂሎች በተግባር የሚያሳይ ነው፡፡ ፈጣሪ ምድርን ጨርሶ አይበድልም፡፡

ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ በመንጋ ፍርድ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ በሦስተኛው ቀን እሁድ እኩለ ሌሊት ገደማ ሞትን አሽንፎ ተነሣ፡፡ ከዚያን ዘመን ወዲህ ዐርብ የምትታወሰን በስቃይና በህማም ነው፡፡ የስቅሎ ስቅሎ የመንጋዎች ታሪክም ሲብስ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ የንጹሑን የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት አስቆርጦ ወንጀለኛውን በርባንን በምትኩ ከእስር ያስፈታው የመንጋ ፍርድ ነው፡፡ የመንጋ ጦስ አያድርስ፡፡

ዐርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ልጄ የተሣፈረበት የሕዝብ ማመላለሻ ከአንድ የአማራ ክልል ከተማ በጧት ተነሣና ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ ጀመረ፡፡ ጉዟቸውን በስልክ ስከታተል ግስጋሴያቸው እጅግ ፈጠነና – ዐይን ገብቷቸው መጨረሻቸው ላያምር – ስድስት ሰዓት አካባቢ አባይ በረሃን አቋርጠው ጎሐጽዮን ዳርቻ ደረሱ፡፡ እዚያ ሲደርሱ ግን ያልጠበቁትና ኢትዮጵያውያንን አልፎ ዓለምን ጉድ ያሰኘ የአጋች ታጋች ድራማ በኦሮሞ ቄሮዎችና በኦሮምያ ፖሊስ መርግ መርግ የሚያካክል ድንጋይ አስፋልቱ ተዘግቶ አታልፉም ተባሉ፡፡ ከብዙ መኪኖች ጋርም ተደርድረው በአሳልፉን አታልፉም ውርክብ ምሽቱ ለዐይን ሊይዝ ሆነ፡፡ መንገድ ላይ ሊያድሩ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ደጀን ተመለሱ፡፡

ጉዳዩን ቀድሞ የሰማው የደጀን ሕዝብ ከ3000 የሚበልጠውን ተሣፋሪና ባለመኪና በፍቅርና በወገናዊ የአለኝታነት ስሜት ተቀብሎ ካለው ብቻ ሳይሆን ያለውን ሁሉ በማውጣት በደስታ ማስተናገዱን ቀጠለ፡፡ እነዚህን ወገኖች ዘርና ብሔር ፣ ሃይማኖትና አገር ሳይለይ ሁሉንም እኩል ተመልክቶ በሚቆዩባቸው ሦስት ቀናት ምንም ሳያወጡ ተራ ገብቶ ተንከባከበ፡፡ ሁለት ሌሊቶችን እዚያ ሲያድሩ ምግብም መጠጥም እያመጣ ወገኖቻችን ምንም ሳይሰማቸው ከረሙ፡፡ ማታ ማታም ወደየቤቱ እየወሰደ አልጋውን በመልቀቅ ራሱ ሰሌንና አጎዛ በማንጠፍ ግገን ላይ እየተኛ እንግዶቹን በፍቅር አስተናገደ፡፡ የኔ ልጅ ያደረበት ስምንት ሰዎችን የተቀበለ ቤት – ለምሣሌ – ሴቶች ተሣፋሪዎችን ከባለቤቱና ከሕጻናት ልጆቹ ጋር አስተኝቶ አባውራው ከወንድ እንግዶቹ ጋር መሬት አስነጥፎ ተኝቷል፡፡ ይህ ነገር በየትም ዓለም የለም፡፡ ይህን ኢትዮጵያዊነት ነው እንግዲህ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ኃይሎች ሊበጣጥሱት እየጣሩ የሚገኙት፡፡

ነባሩ ቱባ የኢትዮጵያዊነት ባህል እንደዚህ ነው፡፡ ይህን እውነተኛ ታሪክ ልጄ ሲነግረኝ ወደ ደጀን ወዲያውኑ ብረር ብረር የሚል ስሜት ተሰማኝ፤ ይህን ደስታየን ለመግለጽ ወደዚያው ሥራየ ብዬ እንደምሄድ ባውቅም ጊዜው ተንቀራፈፈብኝ፡፡ በዚህች እየሞተች በምትመስል ሀገር ይህን የመሰለ እንደብርቅዬው ዋልያ እንስሳ ሊጠፋ የደረሰ መልካም ወግና ባህል ስንመለከት ውኃ እንዳገኘች የበረሃ ጽጌ ረዳ ነፍሳችን ትለመልማለች፡፡ ለባሰ ቀን እንዲሆነኝ ብዬ ዕንባየን እንደምንም በዘዴ ያዝኩት እንጂ ዐይኖቼ ተንቆርዘው ነበር፡፡

መለስ ዜናዊ ቀድሞኝ በመናገሩና እንደተሳሳተም ብዙ ጊዜ በመዘገቡ እንጂ እርሱ ያለውን አሁን ብለው ደስ ባለኝ፡፡ እርሱ የሁላችንም መሪ ሆኖ ተናገረ የተባለውን መናገሩ ከኔው የሚከፋ መሆኑን ብረዳም አንዳንዴ በበጎ ጎኑ ካየነው በርግጥም ከዚህን መሰል የፍቅር ተምሣሌት ማኅበረሰብ መወለድን ቢመኙትና ምኞትንም በአደባባይ ቢገልጹ ክፋት የለውም ባይ ነኝ፡፡ ዱብቲ ላይ የተሠራውን መልካም ሥራ፣ አርሲ ነገሌ ላይ የተሠራውን መልካም ሥራ … በሰማሁ ወቅት ይሄው ስሜት ተሰምቶኝ ነበርና ቁም ነገሬ ከመልካምነት አኳያ እንጂ ከዘርና ከቋንቋ አንጻር እንዳይወሰድብኝ አደራ፡፡ በተቃራኒው አንድ ወቅት አንድ አካባቢ አንድ ዕብድ ሰው ዘሎ ገብቶበት ገጭቶት በመሞቱ ምክንያት በህግ ጥላ ሥር የነበረን ሹፌር ከሁለቱ የፖሊስ ጣቢያው ጠባቂዎች ሕዝቡ በመውሰድ – (ጠባቂዎቹም ወደው ሰጥተው) – ቆራርጠው በገደሉበት የአንድ ኢትዮጵያዊ ከተማ ነዋሪ መሀል መወለድ ቀርቶ በዚያ በኩል ማለፍም አልፈልግም፡፡ ….

ለማንኛውም መለስ ያን ያስባለው ለክፋትና በክፋት ነው – ለሌላው ማኅበረሰብ በነበረው ጥላቻና ንቀት ኅሊናው ታውሮ ነው፡፡ እርሱ የተዋረደበት ንግግር ምንጩ ስንቅና ትጥቅ እንዲሁም ለጦርነት ግብኣት የሚሆን ተዋጊ ኃይል ነው፡፡ እኔ ብወለድበት የተመኘሁትና ስለተወለድኩበትም የምኮራበት ማኅበረሰብ ያሳዬው ተግባር ግን ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው ካለትግርኛና ኦሮምኛ የማይሰሙ ግን በበላይ ልሂቃን ተብዬዎች “ጠላቶችህ ናቸው! አጥፋቸው!” እየተባለ እስኪያንገሸግሸው የባጀበትን ወሬና አሉቧልታ ንቆ ትቶ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ያላንዳች መድሎና መገለል እኩል ተንከባክቦ መንገዱ ሲከፈት በሰላም መሸኘቱ ነው፡፡ ሁሉም ሊማርበት የሚገባ ግሩም አርአያነት ነውና ደጀኖች በዚህ አኩሪ ተግባራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ የአካባቢው የክብር ኗሪነት መብት እንዲሰጠኝ ማመልከቴ አይቀርምና በተለይ ኃላፊዎች አቤቱታየን እንድትቀበሉኝ ከወዲሁ በትኅትና እጠይቃለሁ፡፡ ዕድሜ ይስጠኝ እንጂ በጡረታ ዘመኔ በዚህች ድንቅ ከተማ ውስጥ መኖር እንድችል አንድዬ ዕድሉን ቢያመቻችልኝ ደስታየ ገደብ የለውም፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ አሁን ጣዕር ላይ ናትና የእምዬን የጣር ዘመን ያሳጥርልን፡፡ ትንቢትን ጨርሶ ማስቆም ባይቻልም በኢትዮጵያና በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን አርማጌዴዖናዊ ጦርነት በአመክሮ እንዲያለዝብልን ሁላችን በየእምነት ቤቶቻችን ከክፋት ርቀን በቅን ልቦና ፈጣሪን እንለምነው፡፡

 

ግርማ በላይ gb5214@gmail.com

Filed in: Amharic