>

እስክንድር ይለያል !!! (ታመነ በየነ)

እስክንድር ይለያል !!!
ታመነ በየነከዳላስ 
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣናቸውን እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ ስልጣን ከያዙበት ማግስት ጀምሮ ከህውሃቱ መለስ ዜናዊ በላቀ መልኩ ተክለሰውነታቸውን ለመገንባት የሄዱበት ርቀት እጅግ አስገራሚ ነው። በሌሎች ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ሊሰሩ የሚገባቸውን አያሌ ጥቃቅን  ክንውኖች  ጭምር ራሳቸው ሲከውኑ ታዝበናል።
    ለዚሁ ገፅታ ግንባታ ይረዳቸው ዘንድ በዙሪያቸው በርካቶችን አስልፈዋል። እኒህ ሰልፈኞች ተግባራቸው ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ፖሊሲ መቅረፅና ተቋማት እንዲገነቡ የሚረዳ ሃሳብ የሚያቀርቡ ሳይሆን ¨ንጉስ ሆይ ሺ አመት ንገስ!¨ እያሉ ከበሮ የሚመቱ ናቸው ።
     ጠቅላዩ በኢትዮጲያ ውስጥ ከሳቸው በቀር ሌላ የህዝቡን ትኩረት ሊስብ የሚችል ፖለቲከኛ፣ ግለሰብም ሆነ የሚዲያ ሰው እንዲኖር ፍፁም እንደማይሹ ከጭብጨባና ድጋፍ በስተቀር በፍፁም ተቃውሞን ሊያስተናግድ የሚችል ስብዕና እንደሌላችው በተደጋጋሚ አሳይተውናል ።
              የተካኑበትን  ብልጣ – ብልጥ የሆነ አቀራረብ ተጠቅመው እንደ አይን ብሌን የምንሳሳላቸውን  በሃገር ውስጥም ይህን በኢንተርናሽናል ኮሚውኒቲው ዘንድ ከባድ ሚዛን የሆኑ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ የመብት  ተሟጋችና ጋዜጠኞችን ሳይቀር ከጥቅም ውጪ አድርገው ከሚወዳቸውና የድጋፍ መሰረታቸው ከሆነው ማህበረሰብ ጋ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ሰርተዋል። በተግባርም በአለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሳቸውን ፓርቲ አሸንፌ ስልጣን ይዛለሁ ብሎ የሚወዳደር ፓርቲ መሪ በየመድርኩ ስለ እሳቸው በተደጋጋሚ እንዲናገር አድርገዋል።
       በዚህ ረገድ ሊያገኙት ያልቻሉት ብቸኛው ሰው እስክንድር ነጋ ነው። አንደበት ርቱዕነቱ፣ ስነ ስርአቱ፣  የሚያነሳቸው ሃሳቦች ጠጣርነት ፣ ስለ ሰላማዊ ትግል ያለው ጥልቅ  እውቀት እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሰው በመሆኑ ቀስ በቀስ ህዝቡ እየተረዳው ሲመጣ ሚሊየኖች ሊከተሉት ይችላሉ። ይህ ደግሞ እኔ እያለሁ የሚሆን አይደለም ብለው ያቄሙበትና እንቅስቃሴውን ለመግታት ማንኛውም እርምጃ ከመውሰድ እንደማይመለሱ የባልደራሱን አመራር አባላት በማሰር የእስክንድርን አካሄድ ሞመንተም ለማቀዝቀዝ እርምጃ በመውሰድ አሳይተውናል።
        ዛሬ ዘግይቶም ቢሆን የእስክንድ አካሄድ የገባቸው በርካቶች  እየተከተሉት ነው። እሳቸውም  በባልደራሱ ላይ በወሰዱት እርምጃ በተለይም  የዛሬውን ሰልፍ በማን አለብኝነት በመከልከላቸው እስክንድር  አሸንፏቸዋል። ስለዚህ ከሳቸው የኖቤል ሽልማት ዜና በላይ እስክንድር ሲወደስ ውሏል። በዚህም በኢትዮጵያ ምድር  የሚቃወማቸውና ከሳቸው በላይ ትኩረት የሚስብ ሰው እንዳይኖር የመፈለጋቸው አባዜ  በእስክንድር ላይ የሰራላቸው አይመስልም። የመጀመሪያውን የባልደራሱ ጋዜጣዊ መግለጫ በ መከልከልና ለ እስክንድር ደህንነት ስንል ነው የከለከልነው ከፈለገ በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት ይችላል በማለት ያጠመዱለትን የማምከኛ መንገድ በጥበብ  በማለፍ ማንነቱን አሳይቷቸዋል። ምክኒያቱም እስክንድር ይለያልና።

ቪቫ ታላቁ  እስክንድር!!!

Filed in: Amharic