>

የኖቬል ሽልማቱ መዳረሻ!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

የኖቬል ሽልማቱ መዳረሻ!!!
ኤርሚያስ ለገሰ
የኖቬል ሽልማቱ በተሰጠ ሁለተኛ ቀኑ ደግሞ ከዚህ በፊት የገለጥነው እና የሽልማቱ ምክንያት ብለን የጠረጠርነው ነገር ሳይውል ሳያድር እየመጣ ይመስላል። በኢትዬ 360 “ዛሬ ምን አለ?” ፕሮግራማችን ” የኖቬል ሽልማቱ ነገር” በሚል ርዕስ ስንወያይ ” የኖቬል ሽልማቱ ኢትዩ-ኤርትራን እንደ ጭንብል ወስዶ መዳረሻው ግን ግብፅ ይሆናል” ብለን ነበር።
ዶክተር አቢይ አህመድ ገንግኖ ከወጣበት በራስ ፍቅር መውደቅ(ናርሲዝም) እና የስልጣን ጥማት ኢትዬጵያን እስከ መሸጥ ሊሄድ እንደሚችል ከሚጠረጥሩ ወገኖች አንዱ ነኝ። ይህን እምነትን ከወዲሁ ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ።  በዚህም ምክንያት የሚፈጽማቸው ተግባራት የተጠኑ እና ተቋማዊ ይዘት ያላቸው ሳይሆኑ በግብታዊነት የራስን ስልጣን እና ከፍታ የሚያሳዩ ሆነው የሚታዩ ናቸው። ለምሳሌ ዛሬ ለኖቤል ሽልማት ብቁ አደረገው ተብሎ የተገለፀው የኢትዬ-ኤርትራ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ማንንም ሳያማክር በራሱ መንገድ እንደሄደበት ሰሞኑን ሮይተርስ አስነብቦናል። ከመገረም እልፎ እጅግ በሚያስቅ መልኩ የአቢይ አህመድ “yes man!” ሚኒስትሮች የሰውየውን ኤርትራ መከሰት የተመለከቱት ከኤርትራ ቴሌቭዥኖች እና ድረ ገፆች ነው። ሮይተርስ እንደዘገበው። ወደው አይስቁ!
እርግጥ ዘግየት ብሎ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደገለጡት በኢትዬጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መካከል ለተፈጠረው ፈጣን ግንኙነት አገናኝ ድልድይ እሳቸው መሆናቸው ሚስጥሩ ከባለስልጣናት ተሸሽጐ ሊሆን ይችላል። ይህን ፈጣን ግንኙነቱ ሚስጥራዊ ሆነ ማለት ግን በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል የተደረጉት ስምምነቶች ተደብቀው ይቀራሉ ማለት አይደለም።
አቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ምንድነው የተስማሙት? አሁን አሁን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከማፈግፈግ አልፈው ሁሉንም ቦርደሮች ለምን ዘጉ? ባድመ መቼ ነው ለኤርትራ የምትሰጠው? —ወዘተ የሚታወቅ መልስ የላቸውም። አይደለም ተራው ዜጋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልሱን አያውቁትም። እንደማንኛውም ኢትዩጽያዊ ሊገምቱ ይችሉ ይሆናል። ለምሳሌ በባለስልጣናት ዘንድ በሰፊው የሚጠረጠረው አንዱ ስምምነት ዶክተር አቢይ ለፕሬዝዳንቱ ቃል የገቡት ትላልቆቹን የህውሓት ባለስልጣናት ( ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ስዩም መስፍን፣ ጌታቸው አሰፋ፣ በረከት ስምኦን—) ጠራርጐ እግረ ሙቅ ማጥለቅ እንደነበረ ነው። እስር ቤት መወርወር። ነገሩ ” እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ” ሆነና የጨለማ አበጋዞቹ ሸሽተው መቀሌ ከተሙ።
እንዲህ እንዲህ እያልን ብንዘረዝር በሁለቱ የኢትዩ-ኤርትራ መሪዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት እስከዛሬም እንቆቅልሽ ሆኗል። ዛሬም ድረስ ሚስጥሩንየሚያውቁት አቢይ አህመድ(ለማ መገርሳ) እና ኢሳያስ አፈወርቂ ብቻ ናቸው።  ጠርጥር ካላችሁኝ አይበለው እና አቢይ አህመድ አንድ እክል ቢያጋጥመው ደመቀ መኮንን ስለ ስምምነቱ የሚያውቅ አይመስለኝም። ለነገሩ ከርቀት ሲያዩት ለማወቅም ፍላጐት ያለው አይመስልም። የሌሎችን ለጊዜው እንርሳው።
 በሌላ በኩል ግን የኖቬል ሸላሚዎቹና በሸላሚዎቹ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳራፊዎች የሆኑት ምዕራባውያን በዝርዝር በማያውቁት ጉዳይ ላይ ተመስርተው የኢትዬ-ኤርትራን ኬዝ እንደ ጭምብል ተጠቅመውበታል። ከጭምብሉ ውስጥ ያለው ወርቅ ደግሞ ግብፅ ናት።  ለማንም ግልፅ እንደሆነው ምእራባውያን በተለይ ሰሜን አሜሪካ ከብሄራዊ ጥቅም በመነሳት ለግብፅ ያላት ወገንተኝነት የትየለሌ ነው። ሰሞኑን ደግሞ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ፓርላማው ” የግብጽን ጥቅም በማንኛውም መንገድ ለማስፈፀም ዝጉጅነቱም፣ ቁርጠኝነቱም አለን” በማለት ዝተዋል። ፓርላማው ምን አይነት እርምጃ ይወሰድ የሚለውን ለመወሰን አጥንቶ የሚያመጣ ኮሚቴ አቋቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ የቀድሞ ስምምነቱን ጥሳ አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎች በየቀኑ መደርደር ጀምራለች። አሜሪካን በአደራዳሪነት እንድትገባ ጥሪ አቅርባለች። እንግዲህ ደርግ ሲወድቅና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት አሜሪካ አደራዳሪ ሆና የተፈጠረውን ላጤነ ሰው ግብፅ ለምን አሜሪካንን ፈለገች የሚለው ግልፅ ይሆንለታል።
እሰከ አሁንም አሜሪካ በአባይ ግድብ ጉዳይ ከዶክተር አቢይ ጋር አልመከረችም ብሎ የሚያስብ ካለ የዋህ መሆን አለበት። ነገሮች በከረሩበት እና የሁለቱ አገሮች ባለስልጣናት “ቀይ መስመር አልፈሃል/አልፈሻል” እየተባለ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዛሬ ሬዲዬ ፋና ያስነበበን የሁለቱ አገሮች የስልክ ውይይት የሚነግረን በርካታ ነገሮች ይኖራሉ። በራስ መውደድና የስልጣን ጥማት በአንድ በኩል ፣ የሰላም የኖቬል ሽልማት በሌላ በኩል አቢይ አህመድን እረፍት የሚነሳ ነው። የግብፁ ፕሬዝዳንት ደግሞ በህዝብ እምቢተኝነት የስልጣናቸው ወንበር ተነቃንቋል። ይህም በመሆኑ ግብፃውያንን አንድ ሊያደርግ የሚችል አጀንዳ መፈለጋቸው አይቀርም። መቼም ለግብፃውያን ከአባይ በላይ ሌሎች አጀንዳቸውን የሚያስጥል ማግኝት ዘበት ነው። ለዚህም ይመስላል ፕሬዚዳንት አልሲስ በቅርብ ወጣቶች ሰብስበው ” የግብፅ አብዬት ባይነሳ ኖሮ ኢትዬጵያ አባይን አትገድብም” የሚል ይዘት ያለው ዲስኩር ያሰሙት።
ለማንኛውም ፋና እንዳስነበበን  ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት አልሲስ በስልክ ተወያይተዋል። በውይይቱ አሜሪካን አትኖርበትም ብሎ ማሰብ የዋህነት ቢሆንም ከዚህ ጥያቄ በላይ ሌሎች የሚያሳስብ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የስልክ ንግግራቸውን ለካቢኔያቸው በተለይም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዝርዝር ያቀርባሉ ወይ? የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዬጵያ ህዝብስ የማወቅ መብቱ ይጠበቅለታል? የኢትዬጵያ ዉሃ ሃብት ሚኒስትርና ሌሎች ባለስልጣናት ሰሞኑን ግብፅን በተመለከተ የተናገሩበት ቃና እና ቶን ይቀየራል ወይንስ ተጠናክሮ ይቀጥላል? በአባይ ግድብ ዙሪያ የግብፅ ፍላጐት እንደማይፈፅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ይገባሉ? ወይንስ የሰላም ኖቬል ሽልማቱ መዳረሻ እርቃኑን ግልጥ ብሎ ይታያል? — መልሱን በአጭር ጊዜ የምናውቀው ይሆናል
Filed in: Amharic