>
5:13 pm - Monday April 20, 8595

የኖብል ሽልማቱና ቀጣዩ የቤት ስራ (አልይ እንድሬ)

የኖብል ሽልማቱና ቀጣዩ የቤት ስራ

 

አልይ እንድሬ

በርካታ የፈጠራ ስራዎች (356 ገደማ) ለዓለም ያበረከተውና በተለይም በዲማሚት ፈጠራው በጎላ ሁኔታ የሚታወቀው አልፍሬድ ኖብል እ.አ.አ ጥቅምት 21/1833 ዓ.ም በስዊድን፣ ስቶኮልም የተወለደ ሲሆን በ63 ዓመቱ እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም. በክንታሮት በሽታ ህይወቱ እንዳለፈ ይነገራል፡፡ ባለ ሀብት የነበረው አልፍሬድ ኖብል ብዙ ቋንቀዎችን አቀላጥፎ በመናገርና ግጥምና ድራማ በመፃፍም የሚታወቅ ሲሆን የኖብል ሽልማት ድርጅት መስራችም ነው፡፡

አልፍሬድ ኖብል የኖበል ሽልማት ድርጅትን ለመመስረት የተነሳበትን ምክንያት ስንመለከት ታላቅ ቁም ነገር እናገኝበታለን፡፡ የኖብል ሽልማት ድርጅት ምስረታ መነሻው እንዲህ ነበር፡፡እ.ኤ.አ በ1888 ዓ.ም አንድ ግለሰብ የሸንኮር አገዳ ማሳውን በመጎብኘት ላይ እንዳለ በድንገት ይሞታል፡፡ በወቅቱ ስለ ሟቹ የዘገበው የፈረንሳዩ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ ጎላ አድርጎ “የሞት ነጋዴው ሞተ” (“The merchant of death is dead”) የሚል ርዕስ በመስጠት ስለሞተው ግለሰብ ዘገባውን ያስነብባል፡፡ ጋዜጣው ስለ ሟቹ ባቀረበው ዘገባ የሰው ልጅ ህይወት የሚቀጥፈውን ዲማሚት ፈልስፎ ለዓለም ገበያ ያቀረበና ከዛ ገቢ በማግኘት የሚጠቀም ሲል ሟቹን በማውገዝ “የሞት ነጋዴው ሞተ” በማለት አልፍሬድ ኖብል ማረፉን ያወሳል፡፡ ሆኖም ” የቸኮለች እንዲሉ…ጋዜጣው ተሳስቶ እንጅ የሞተው አልፍሬድ ኖብል ሳይሆን የአልፍሬድ ኖብል ወንድም ሉድቪግ ሆኖ ይገኛል፡፡

አልፍሬድ ኖብል የራሱን እልፈተ ዜና የሚያስቃኘውን ይህን ጋዜጣ በአጋጣሚ አግኝቶ አነበበው፤ ባነበበው ነገርም እጅግ በጣም ተገረመ፤አዘነም፡፡ ለካስ እኔ ስሞት የምታወሰው በዚህ መልኩ በመጥፎ ነው በማለት ተብሰለሰለ፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ሲሞት በሰው ልጆች ሁሉ በመልካም ይታወስ ዘንድ አሁን በህይወት ሳለ ምን ዓይነት በጎ ስራ መስራት እንዳለበት ማውጠንጠን ጀመረ፡፡ በመጨረሻም በስድስት መስኮች (ፊዚክስ፣ኬሚስትሪ፣ሜዲሲን፣ሊትሬቸር፣ሰላምና ኢኮኖሚክስ) ለሰው ልጅ የሚጠቅም ጉልህ ስራ ያበረከተ ማንኛውም ግለሰብ (ዜግነት ሳይለይ) በሰራው መልካም ስራ በዓመት አንድ ጊዜ ተወዳድሮ በማሸነፍ የሚሸለምበት የሽልማት ድርጅት ለመመስረት ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ከ94 ፐርሰንት በላይ የሚሆነውን አጠቃላይ ንብረቱን ለዚህ ዓላማ እንዲውል በመፍቀድ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 1895 ዓ.ም ፊርማውን አኖረ፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 29/1900 ዓ.ም ድርጅቱ የኖበል ሽልማት ድርጅት በመሰኘት ተመሰረተ ሽልማቱም የኖብል ሽልማት ተባለ፡፡ የመጀመሪያው የኖበል ሽልማት አ.ኤ.አ በ1901 ዓ.ም በፊዚክስ መስክ ዊልሀልም ኮንራድ ሮገን ለተባለ ጀርመናዊ ተበረከተ፡፡ የመጀመሪያው የኖበል ሽልማት በተሰጠ በ118 ዓመቱ በዶ/ር አብይ አማካኝነት እነሆ እኛይቱ ኢትዮጲያም ሊገባ ቻለ፡፡ ጠሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በኢትዮጲያ ታሪክ የዓለም የኖበል ሽልማት ያገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ሲሆን እስካሁን በዓለም ላይ ለሰላም ከተበረከተው 100ኛውን የሰላም የኖብል ሽልማት አሸንፏል፡፡ ላገራችን ትልቅ ድል ነውና እኛም እንደዜጋ ደስ ብሎናል፤ የኢትዮጲያ ወዳጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን፡፡

እዚህ ላይ አልፍሬድ ኖበል ለመንገድ ስራና ለኮንስትራክሽን ይውል ዘንድ የፈለሰፈው ዲናሚት በሰው ልጆች ላይ ያስከተለው ጥፋት በህዝብ ዘንድ ቅሬታ በማስከተሉ ሲሞትም የሚታወስበት የጥላቻ ሌጋሲ እንደሆነ በመረዳቱ ዘምን አልፎ-ዘመን በመጣ ቁጥር የሰውን ልጆች በበጎ ስራው ስለሚክስበት ጉዳይ ሃላፊነት ወስዶ በመስራት የኖበል የሽልማት ተቋምን አቋቋመ፡፡ ስለሆነም ዛሬ አልፍሬድ ኖበል በሰላሙ፣በማህበራዊው፣በሀክምናው ወ.ዘ.ተ ዘርፍ በዓለም ዙሪያ በበጎ አስተዋፅኦው ሲዘከር ይኖራል፡፡

የኖቬል ሽልማቱን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከአግላይ ጠቅላይ የብሄር ፖለቲካ መርዘኛ አስተሳሰብ የተላቀቀችና ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ዜጎቿን በእኩል ዓይን የምታይ ኢትዮጲያን ከመገንባት አንፃር እርሰዎ ካለፉ በኋላ የኢትዮጲያ ህዝብ እንዴት እንዲያስታውሰዎት ይፈልጋሉ? ይህን ጥያቄ ያነሳሁት በእድሜየ ካየኋቸው የኢትዮጲያ መሪዎች ሁሉ ስለ ሰላምና ፍቅር እንደርሰዎ የሰበከና የታገለ አለመኖሩን ሳላውቅ ቀርቼ ሳይሆን አሁን-አሁን የኔ-የኔ ማለት ላይ የሚያተኩረው የጎሳ ፖለቲካ ተምልሶ እየተካረረ መምጣቱ ብዥታ ስለፈጠረብኝ ነው፡፡

Filed in: Amharic