>

የፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጊቢሳ ነገር. . . (አቻምየለህ ታምሩ)

የፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጊቢሳ ነገር. . .
አቻምየለህ ታምሩ
የታሪክ መምሕሩ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጊቢሳ ገራሚ ሰው ነው። ከዚህ በፊት ኅብር ሬዲዮ ላይ በተከራከርንበት ወቅት «ኃይለ ሥላሴ አማራ ነኝ ብለው ያውቃሉ፤ ማስረጃውም አለኝ» ብሎኝ ነበር። እስከዛሬ ግን አለኝ ያለውን ማስረጃ ሊያቀርብ አልቻለም። የሚገርመ ነገር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን «ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ» ቁጥር ሁለት ግለ ታሪክ ወደ እንግሊዝኛ ከተረሞቱ ሰዎች መካከል አንዱ እሱ ሁኖ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብለዋል  ያለውን  የትም ብታ አለመናገራቸው ጠንቅቆ እያወቀ  ሆነ ብሎ ሰው ለማሳሳት እንዲያ ብሎ መናገሩ ነው።
ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል እንደ ታሪክ መምህር ኃላፊነት ሊሰማው የሚገባ ሰው ቢሆንም ለዲግሪ ማሟያ በሚጻፉት ወረቀቶችና በታዋቂ ጆርናሎች ላይ በሚታተሙ ጽሑፎች ይዘትና ጥራት ላይ ቀልድ ስለሌለ በነዚህ ወረቀቶች ላይ ታሪክ ነው ብሎ ደፍሮ ሊያቀርበው የማይችለውን ማስረጃ የማይገኝለት ትርክት ለኦሮሞ ልጆች ሲሆን ግን ታሪክ ነው ብሎ እሥኪያሥታውካቸው ድረስ  ሲግታቸው የሚውል የፕሮፓጋንዳ ሰው ሆኗል።
እንደ ኦሮሞ ብሔርተኞች ባለፉት አርባ አራት ዓመታት ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ እየፈጠሩ በየሜዲያውና ባገኙት መድረክ ሁሉ እያስተጋቡ የኦሮሞ ወጣት ከነሱ ፈጠራ ውጭ ሌላው የሚጽፈውን እንዳያነብና እንዳመረምር አድርጎ የሚነግሩን ሁሉ እንደወረደ የሚቀበል ትውልድ እንዲፈጠር ያደረገ ቡድን ያለ አይመስለኝም። የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ እየፈጠሩ በየሚዲያው የሚዘበዝቡትና በሚያወጡት ጥራዝ ሁሉ የደርቱት ጅል ስለሆኑ አይደለም። ሌላው መሳቂያ መሳለቂያ ቢያደርገንም ኦሮሞው ያምነናል የሚል እምነት ስላላቸው ነው። በሌላ አነጋገር የኦሮሞ ብሔርተኞች «ኦሮሞ ጅል ነው» ብለው ከልባቸው ያምናሉ።
ፕሮፌሰር ሕዝቅኤልም ከሰሞኑ ባስተጋባው ፕሮፓጋንዳ  ያደረገው ይህንኑ ነው። የታሪክ መምህር ሆኖ ተረት ተረት ከነገርን ተረት ተረቱን ሲጨርስ «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው»  በማለት የተለመደውን የኦሮሞ ብሔርተኞች ውንጀላ ደግሞታል።
አንድ የማምንበት መርኅ አለ። ማንም ሰው እንዲጠራ በማይፈልገው ስም መጠራት የለበት። መከባበር ማለት አንድ ሰው እንዲጠራበት የሚፈልገውን ማክበርን ይጨምራል። ባጭሩ አንድ ሰው «ኦሮሞ እንጂ ጋላ መባል አፈልግም» ካለ መከባበርን ባሕሉ የሚያደርግ ማንኛውም ሥልጡን የሆነ ሰው ሁሉ ምርጫውን ሊያከብርለት ይገባል። ሆኖም ግን  አንድ ሰው እንደ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጊቢሳ ወደኋላ ሄዶ «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» የሚል ውንጀላ ውስጥ የሚገባ ከሆን በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ውንጀላውን ማጋላጥ ያባት ነው።
ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» የሚል ተራ ውንጀላ ውስጥ የገባው ለዲግሪው ማሟያ «From Mutual Animosity to Mutual Understanding Evolution Of Oromo-Gumuz Relations Sixteenth to Nineteenth Centuries» በሚል ርዕስ በጻፈው ወረቀት ውስጥ ለማስረጃነት ያቀረባቸውን ጉምቱ የሌቃ ባላባት  የአባት ስምና ታሪክ ረስቶ ነው።
ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል በመመረቂያ ጽሑፉ ኦሮሞዎች ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ጉምዞችን እንደምን ይመለኳቷቸውው እንደነበር እንዲህ ሲል  ጽፏል፤
«The Gumuz were specifically identified as diina (literally the enemy), and a permanent diinnuma (literally feud), existed between the Oromo and Gumuz»
ኦሮሞዎች ጉምዞችን እንደ ጠላት እንደሚቆጥሯቸው የነገረንን ታሪክ ለማስገንዘብ የታሪክ ምንጭ አድርጎ የጠቀሰው ከሌቃው ባላባት ከግራዝማች ደሬሳ ጋላ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ነው። አዎ  ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው የሌቃ ባላባት ስምን  ደሬሳ ጋላ ይባላሉ። ደሬሳ ስማቸው ሲሆን ያባታቸው ስም ጋላ ይባላል።
ግራዝማች ደሬሳ ጋላ የምስራቅ ወለጋ ገዢ የነበሩት የደጃዝማች ሀብተ ማርያም ቁምሳ የንብረት ክፍል ኃላፊ ነበሩ። ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጊቢሳ ኦሮሞ ጉሙዝን እንደ ጠላት ይቆጥረው እንደነበር ነገሩኝ ያለውን ታሪክ የመዘገበው ከግራዝማች ደሬሳ ጋላ ጋር እ.ኤ.አ. August, 1982 ነቀምቴ ውስጥ ከሳቸው ጋር ቃለ መጠይቅ ካደረገ በኋላ ነበር። ግራዝማች ደሬሳ ጋላ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ቃለ መጠይቅ ባደረገላቸው ወቅት የ96 ዓመት አዛውንት ነበሩ። ግራዝማቹ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት  በ99 ዓመታቸው እ.ኤ.አ. በ1985 ዓ.ም. ነው።
የግራዝማች ደሬሳ ጋላ አባት ጋላ ዋሪ ይባላሉ። አቶ ጋላ ዋሪ በበከሬ ጎዳና ዘመን አባ አባቆሮ የነበሩት የአባቆሮ ዋሪ ልጅ ናቸው። ሞቲ በከሬ ጎዳና ሌቃ ለቀምትን እስከ 1863 ዓ.ም. የገዙ የምስራቅ ወለጋ ንጉሥ ሲሆኑ የተወለዱት በ1793 ዓ.ም. ነው። እ.ኤ.አ. በ1985 ዓ.ም. በ99 ዓመታቸው ከዚህ አለም ያለፉት ግራዝማች ደሬሳ ጋላ የተወለዱት በ1877 ዓ.ም. ነው። የግራዝማች ደሬሳ አባት አቶ ጋላ ዋሪ ሞቲ በከሬ ሞተው ልጃቸው ሞረዳ በከሬ አባታቸውን ሞቲ በከሬን  ተክተው «ሞቲ» ሲሆኑ አባቆሮ ሆነዋል። በገዳ የእድሜ አቆጣጠር መሰረት አቶ ጋላ ዋሪ በ1863 ዓ.ም. አባ ቆሮ ለመሆን ቢያንስ የ33 ዓመት ሰው መሆን አለባቸው። ይህ ማለት አቶ ጋላ ዋሪ በ1863 ዓ.ም. አባ ቆሮ ለመሆን ቢያንስ በ1830 ዓ.ም. መወለድ ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት አቶ ጋላ ዋሪ አባታቸው አባቆሮ ዋሪ ለልጃቸው ስም ሲያወጡ ጋላ የሚል ስም ያወጡላቸው ቢያንስ በከ1830 ዓ.ም. በፊት ነበር ማለት ነው።
ዳግማዊ ምኒልክ የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም. ነው። ይህ ማለት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሲወለዱ አቶ ጋላ ዋሪ የስድስት ዓመት ልጅ ናቸው ማለት ነው። የአቶ ጋላ ዋሪ ትውልድ አካባቢ ወለጋ ለዳግማዊ ምኒልክ የገበረው በ1874 ዓ.ም. ነው። ይህ ማለት ወለጋ ለዳግማዊ ምኒልክ የገበረው ግራዝማች ደሬሳ ጋላ ከተወለዱ ከ3 ዓመታት በኋላና አባታቸው አቶ ጋላ ዋሪ ደግሞ ከተወለዱ ከ44 ዓመታት በኋላ ነው።
ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል! «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» የምትለው አንተ የዲግሪ ማሟያ ወረቀትህን ስትጽፍ ቃለ መጠይቅ ያደረግህላቸው የፊታውራሪ ደሬሳ ጋላ አባት አቶ ጋላ ዋሪ ከተወለዱ በስድስት ዓመታት በኋላ የተወለዱት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከመወለዳቸው ከስድስት ዓመታት በፊት ወለጋ ሄደው ለአባቆሪ ዋሪ ልጅ ጋላ የሚል ስም አወጡላቸው ነው የምትለን? ጋላ የሚለውን ስም አማራ ለኦሮሞ የሰጠው መጠሪያ ከነበር፤ ወለጋ ለዳግማዊ ምኒልክ ሳይገብር፣ ዳግማዊ ምኒልክም ገና ሳይወለዱ የወለጋው ባላባት የነበሩት አባቆሮ ዋሪ ለወለዱት ልጅ ጋላ የሚል ስም ለምን አወጡ? እስቲ ንገረን? ጋላ የሚለውን ስም አማራ ለኦሮሞ ያወጣው ስድብ ከሆነ፤  ወለጋ ለማንም በማይገብርበት ወቅት፤ ዳግማዊ ምኒልክ ሳይወለዱ፤ ወለጋ በራሱ ንጉሥ ሲተዳደርበት በነበረ ወቅት እንዴት አንድ የወለጋ ባላባት ለልጁ ጋላ የሚል የስድብ ስም ይወጣል?
እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም. «The Italian Invasion, the Ethiopian Empire, and Oromo Nationalism: The Significance of the Western Oromo Confederation of 1936» በሚል ያሳተምኸው ወረቀት ውስጥ በምንጭነት የተጠቀምህባቸው የወለጋ ባላባቶች ለእንግሊዝ መንግሥት የላኳቸው ደብዳቤዎች ውስጥስ የወለጋ  ባላባቶቹ ራሳቸውን ማን ብለው ነበር የሚጠሩት? ኦሮሞ ብለው ነበርን? በዚያ  የኢትዮጵያ  ማዕከላዊ መንግሥት በፈረሰበት  የወረራ ዘመን  የወለጋ ባላባቶችን ማን አስገድዷቸው ነው ራሳቸው ጋላ እያሉ ይጠሩ የነበረው?
ለአንባቢ ግንዛቤ ይሆን ዘንድ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም. ባሳተመው ጥናቱ ላይ ከጠቀሳቸው ደብዳቤዎች መካከል አቶ ይልማ ደሬሳ እ.ኤ.አ. በ1936 ዓ.ም. «የምዕራብ ጋሎች ኮንፌድሬሽን» በሚል በወለጋ ባላባቶች የተቋቋመውን ኅብረት ወክለው እ ከጎሬ ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸሐፊ ለነበሩት ለአንቶኒ ኤደን በጻፉት  ደብዳቤ ውስጥ ሶስት አንቀጾችን በመጥቀስ አቶ ይልማም ሆነ ባላባቶቹ ራሳቸውን ማን ብለው ይጠሩ እንደነበር እንዲህ አቀርባለሁ፤
____________
His Excellency
Anthony Eden,
Secretary of state for foreign Affairs
I have the honor to inform you that His Excellency Dejazmatch Habre Mariam (Governor of Wallaga and head of the Western Gallas Confederation) has appointed me chief of the delegation which is now in Gambella to get in touch with His Britannic Majesty’s Government in Great Britain and Northern Ireland.
Consequently I have to inform your Excellency that HIS Excellency Dejazmatch Habte Mariam has taken note of the communication made to him by His Britannic Majesty’s consul at Gore to the effect that Italy has defeated the Shoa army and has occupied Addis Ababa to form a new Government. He has also taken note that a new provincial Government is in the process of getting formed at Gore for the Western Gallas.
As your Excellency is well aware, the people of Western Gallas have never completely lost their independence. On the contrary they have always enjoyed a full measure of autonomy within the frame of Ethiopian Empire. This autonomy was fully experienced in the form of complete independence in maters of local government administration. The people of Western Gallas have always been ruled by their own hereditary chiefs, of which His Excellency Dejazmatch Habtemariam’s family has become most prominent.
.
(Signed)
Yilma Deressa
Principal Delegate of The Western Gallas Confederation
_________
ይህ የአቶ ይልማ ደብዳቤ ሙሉውና ዋናው ቅጂ በክምችቴ ውስጥ ይገኛል። በዚህ የአቶ ይልማ ደብዳቤ ላይ እንደሚታየው የወለጋ ባላባቶችን ማን አስገድዷቸው ነው «የምዕራብ ጋሎች ኮንፌድሬሽን» የሚል ኅብረት ሲመሰርቱ ራሳቸው ጋላ እያሉ የጠሩት? እስቲ ንገረን! የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረሰበት በዚያ ወቅት አማራ አስገድዷቸው  ራሳቸው ጋላ እያሉ የሚጠሩት?
የወረ በኬሬን ዜና መዋዕል የጻፉት የልጅ ልጃቸው ደጃዝማች ቁምሳ ሞሮዳ በከሬስ ቢሆኑ  በራሳቸው ተነሳሽነት በጻፉት ዜና መዋዕል ውስጥ የራሳቸውንና የሚገዙትን ሕዝብ ማንነት ምን ብለው ነበር የጻፉት? ጋላ ብለው አይደለምን? ልጃቸው ደጃዝማች ሀብተ ማርያም ኩምሳስ ቢሆን  የእንግሊዝ ሙከራቸው አልሳካ ሲል ወደ ፋሽስት ጥሊያን ዞረው ማንም ሳያስገድዳቸው ግራዚያኒን ሲቀበሉ በጻፏቸው ደብዳቤዎችና ለሕዝባቸው ባወጧቸው  አዋጆች  ራሳቸውንና ይገዙት የነበረውን ሕዝብ ማንነት ምን ብለው ነበር የሚጠሩት? «መላው የጋላ ሕዝብ» ብለው አልነበረምን?
«ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» ከተባለ ጋላ የሚለው ቃል የአማርኛ  ትርጉም ምን ማለት ነው? ለመሆኑ ቃሉ አማርኛ ነውን?  አማርኛ ከሆነ  ከቃሉ ግንብ ጀምረህ ፍቺውን እስቲ ወዲህ በል? ነው አማራ በአማርኛ ትርጉሙ ምን እንደሆነ በማያውቀው ቃል  ሌላው ለመጥራት ተጠቀመበት ነው የምትለን?
እንዴውም ጥናቶችን ስናገላብጥ የምናገኘው እውነት ጋላ የሚለው ቃል እንደሆነ ነው። ጋላ ስለሚለው ቃል ትርጉም ጥናት ያደረጉ የኦሮሞ ጥናት ባለሞያዎች ያሳተሙትን ምርምር ለፈተሸ  ቃሉ የኦሮምኛ ቃል መሆኑን ተመራማሪዎች ያጠኑትን ያገኛል። ማንበብ የሚሻ ቢኖር ፕሮፌሰር ኢኔሪኮ ቸሪሊ እ.ኤ.አ. በ1922 ዓ.ም. ባሳተመው «The Folk Literature of the Galla of Southern Abyssinia» ጥናት ውስጥ  ገጽ 26 ላይ እና ፕሮፌሰር ዜትልማን ቶማስ እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም. «Nation der Oromo: Kollektive Identitäten, nationale Konflikte, Wir-Gruppenbildungen» በሚል በጀርመንኛ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 35 ላይ ይመልከት። ፕሮፌሰር ቼሩሊ ጋላ የሚለው የኦሮምኛ ቃል መሆኑን በመግለጽ  ትርጉምም ከእንግሊዝኛው wanderer ጋር አንድ አይነት ነው ይላሉ። ጀርመናው ፕሮፌሰር ቶማስ ደግሞ  ጋላ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል መሆኑን ጠቅሰው ትርጉሙም immigrant ማለት ነው ይላሉ።
እንግዲህ! እነ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» የሚሉን ፕሮፌሰር ኢኔሪኮ ቸሩሊና ፕሮፌሰር ዜትልማን ቶማስ የኦሮምኛ ቃል እንደሆነ የነገሩንን ቃል ነው። ይህ ማለት እነ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል እንደሚሉን ከሆነ አማራ ለኦሮሞ የኦሮምኛ ስም አውጥቷል ማለት ነው። አማራ ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደለምና ለኦሮሞ የኦሮምኛ ስም ሊያወጣለት አይችልም! ዘማራ ትርጉሙን በማያውቀው ቃል ኦሮሞ የነበረውን ጋላ የሚል ስያሜ ሊያወጣ የሚችል ወፍ ዘራሽ አይደለም!
ከኦሮሞ ብሔርተኛ ምሁራን ባሻገር «ጋላ የሚለውን መጠሪያ  አማራ ለኦሮሞ ወጣው ነው» የሚለውን  ውንጀላ ኦነግ እንደ ድርጅት ለዘላለም የሚያራምው አቋሙ ነው። አማራውን እንደዚህ የሚወነጅለው ኦነግ ግን ራሱ  ሲቋቋም ለራሱ መጠሪያ አድርጎ ያወጣው ስም ኦነግ የሚል አልነበረም። የኦነግ የመጀመሪያ ስም ጋነግ ወይም የጋላ ነጻነት ግንባር [Galla Liberation Front]] የሚል ነበር። ኦነግ ራሱን ጋነግ ወይም Galla Liberation Front ብሎ ሰይሞት የነበረው አማራ አስገድዶት ይሆን? ለማንኛውም ወደፊት በምናወጣው ዶሴ ኦሮሞን ነጻ አወጣለሁ ብሎ የተቋቋመው ኦነግ ራሱ ሲመሰረት የነበረው ስም ኦነግ ሳይሆን ጋነግ ወይም የጋላ ነጻነት ግንባር [Galla Liberation Front] እንደነበር  የሚያሳይ ለዚያድ ባሬ  የጻፈውን በእጃቸውን የሚገኝ ደብዳቤውን እናትማለን!
ከታች የታተመው ታሪካዊ ደብዳቤ ከፋሽስት  ጣሊያ ወረራ በፊት የወለጋው ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ሀብተ ማርያም ገብረ እግዚያብሔር [ቁምሳ] መስከረም 24 ቀን 1929 ዓ.ም. ለጣሊያን ሲገቡ ለሕዝባቸው ያስነገሩት አዋጅ ነው። ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል «ጋላ የሚባል አልነበረም» ፤«አማራ ያወጣልን ስም ነው» ቢለንም ደጃዝማች ሀብተ ማርያም ቁምሳ ግን ማንም ሳያስገድዳቸው ለወለጋ ሕዝብ ያወጡትን አዋጅ ሲያውጁ «ለመላው የጋላ ሕዝብ» ብለው ነበር።
Filed in: Amharic