>

ቄሮው አራርሳና ተራኪው አብዲሳ!!! (እንዳለጌታ ከበደ)

ቄሮው አራርሳና ተራኪው አብዲሳ!!!
እንዳለጌታ ከበደ
ሌሎች አደረሱብን ከምንለው ግፍ ይልቅ እኛው ራሳችን በራሳችን ላይ ያደረግነው ይበዛል !!!
…..
አራርሳ …በጽሞና ሲከታተለኝ ቆየና፣ ‹‹ዐየህ! የምንታገለው የተነጠቅነውን ሥም ለማስመለስ ነው፡፡ የምንታገለው አባብለው አጃጅለው የወሰዱብንን መብታችንና መሬታችንን ለማስመለስ ነው›› አለኝ፡፡
‹የጉዋደኛህ የደበላ፣ የመታወቂያ ስም ማን ነው? ኦሊያድ አይደል? ማን ነው ያወጣለት? አባቱ፣ እናቱ ዘመዶቹና የዚህ ሰፈር ሰው ሁሉ ደበላ ነው የሚለው፡፡ እሱ ግን በራሱ ፍቃድ ውልና ማስረጃ ነው ፍርድ ቤት ሄዶ ስሙን ኦሊያድ አስባለው፡፡ ደበላም ኦሊያድም የኦሮምኛ ቃል ነው››
አባቴ ሣቅ ሲል ሰማሁና፣ ‹‹ይገርማል አይደል?›› አልኩት፡፡
‹‹ምኑ?››
‹‹ደበላ ሳያውቀው በራሱ ስም፣ በራሱ ሕግና በራሱ ባሕል ላይ የሚያደርገው አመጻ?›› ስለው፣ እሱ ደግሞ ተጨማሪ ማብራርያ አከለበት፡፡
‹‹መቸ እሱ ብቻ? አንድ ጓደኛዬ ትዝ ብሎኝ ነው እንጂ፡፡ ከዚህ ትዝ ካለኝ ሰው ጋር አብረን ተማርን፣ በደርግ ዘመን፡፡ ስሙ ገመቺስ ነው፡፡ እሱ ግን፣ ‹እባካችሁ በዚህ ስም አትጥሩኝ› አለ፡፡ ራሱንም አራዳ መሆን ስም በማሳመር መስሎት፣ ስሙን  ሳምሶን፣ ወይም ሳሚ አለው፡፡ በትክክለኛ ስሙ ሲጠሩት ይናደድ ጀመረ፡፡ ኋላ ኢሕአዴግ ሲገባ፣ ሥርዓቱ ስለነፍጠኞች ሲያወራ፣ በተሟሟቀ መድረክ ላይ እጁን አውጥቶ፣ ‹ነፍጠኞቹ ምን የመሰለ ስም እያለኝ፣ ገመቺስ መባል ሲገባኝ እነሱ ግን ሳሚ ይሉኝ ነበር› አለ፡፡ ‹ከእንግዲህ ገመቺስ እንጂ ሳሚ አይደለሁም› አለ፡፡ ምን ለማለት ነው? ሌሎች አደረሱብን ከምንለው ግፍ ይልቅ እኛው ራሳችን በራሳችን ላይ ያደረግነው ይበዛል ለማለት ነው፡፡ ስማኝ አራርሳ ጓደኛህም ደበላ መባል አነሰበት፡፡ የድሮ ሰው መሆን መሰለው፡፡ ‹እኔ ኦልያድ አይደለሁማ ዋጋውን ካልሠጠሁት!› እያለ በሰበብ አስባቡ ራሱን እያስተዋወቀ ኖረ፤ ግን አልተሳካለትም፡፡ ፌስ-ቡክ ላይ ብቻ ሆኗል – አዲሱ ስሙን የሚጠቀምበት፡፡
‹‹ሆኖም ስም መቀየር በአንተ፣ ወይም በእኔ ዘመን ብቻ የነበረ ታሪክ አይደለም – በአያታችን ዘመንም ይፈጸም የነበረ እንጂ፡፡ /…./ በዘመኑ የከተሜነት መገለጫ አንዱ ‹ባማረ ሥም› መጠራት ስለነበር አንዳንድ አማሮች ሁሉ ስማቸውን ከሸዋ አነሰሽ፣ ወይም ከሙሉ ጎጃም ወደ ሜላትና ሄለን ተሸጋግረው ነበር፡፡ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ፣ ጠላት አማራን ብቻ ነጥሎ መምታት ጀምሮ ስለ ነበር፣ ስንቱ አማራ ነው፣ ስሙን ወደ ጌዴኦና ቡርጂ የለወጠ? አሁን ግን ስም መቀየር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ዕድሜ ለደርግ አስተሳሰቡንም ሥርዓቱንም አሽቀንጥሮ ጣለው›› ሲል አባቴ፣ እኔ ደግሞ ማጠናከርያ ሰጠሁት፡፡
‹‹ያም ሆኖ፣ ዶናልድ ሌቪን፣ ‹Greater Ethiopia› በሚለው መጽሐፉ እንደ ሚለው፣ አጼ ኃይለሥላሴ ዘረኛ አልነበሩም፤ ዘረኛ ቢሆኑ ኖሮ ድሬዳዋን፣ ሐረርን፣ አዋሳን፣ አርባ ምንጭን፣ ጅማንና ሌሎችንም ከተሞች ከማልማት ይልቅ ትኩረታቸውን ሸዋ ላይ ብቻ ባደረጉ››
አራርሳ የሚበገር አልሆነም፡፡ ‹‹ሁሉም ያው ነው፤ እነሱም እነሱ የወጡበት ማኅበረ-ሰብም በደም ሥራቸው ውስጥ ያለው ለእኛ ያላቸው ንቀት ብቻ ነው››
‹‹እናንተ ልጆች ከቀበሌያዊ አስተሳሰብ የምትወጡት መቼ ነው?›› ብዬ ጠየቅሁት፡፡
‹‹አንተም እንደ ነፍጠኞችና ነፍጠኛ ወዳጆች ቄሮ ጠባብ ነው እያልከኝ እንዳይሆን?››
‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ይመን ሲባል፣ ሁሉም አንድ ዓይነት ይሁን ማለት አይደለም፡፡ ቄሮ ውስጥም ምርቱ ከግርዱ ጋር ተደባልቋል፡፡ መርጠህ መጠጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በፊትም አሁን እንደሆንነው ዓይነት ለውጥ ሲከሰት፣ ወጣቱ ከልማቱ ይልቅ ወደ ጥፋቱ ያዘነብላል፡፡ ስለ ሚያፈርሰው እንጂ ስለ ሚገነባው ነገር አይጨነቅም››
አባቴ፣ ስለ እሱ ዘመን ቄሮነት ማውራት ጀመረ፡፡
Filed in: Amharic