>

ከራስ ጋር ሙግት፤ የጸብ አታሞ፣ ግብዝነት እና ከእኔ በላይ...!!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከራስ ጋር ሙግት፤ የጸብ አታሞ፣ ግብዝነት እና ከእኔ በላይ…!!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ምነው ጸብ ጸብ አለን? ምነው በነጋ በጠባ የጸብ አታሞ መደለቅ ሆነ ሥራችን? ምነው እንደ ሥልጡን ሰው ቁጭ ብሎ መወያየት አቃተን? ምነው ሁሉም ጉልበቴን ልፈትሽ አለ? ምነው ተከባብሮ መኖር ተሳነን? ምነው መደማመጥ ከእኛ እራቀ? ምነው ሁላችንም የነገር ሰይፋችንን መዘን ለአንባጓሮ አቆበቆብን?
በከፋ ድህነት እና በአፈና ውስጥ ለረዥም ጊዜ ታምቆ መቆየት ስሜትን ያሳሳል መሰለኝ። ምነው ሲበዛ ስሜተ ሥስ ሆንን? በትንሽ በትልቁ እንደ ቄብ ዶሮ ቁፍ ቁፍ የምንለው ምን ሆነን ይሆን? ከሚያፋቅሩት ይልቅ በሚያጋጩት፣ ከሚያከባብሩት ይልቅ በሚያናንቁት፣ እርስ በርስ እንድንተሳሰብ ከሚያደርጉን ይልቅ አንዳችን በአንዳችን ላይ እንድንከፋ በሚገፉን፣ ከሚያቀራርቡን ይልቅ በሚያራርቁን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን ማጥፋታችን ምነዋ?
ውይይቶቻችን ሁሉ በልዩነቶቻችን ላይ ያተኮሩ ብቻ ለምን ሆኑ? የጋራ ታሪክ፣ የምንጋራው ኃይማኖት ወይም ባህል፣ የምንጋራቸው የማንነት መገለጫዎች፣ የምንጋራው መሬት፣ የምንጋራው ኃብት፣ የምንጋራው ትውፊት፣ የምንጋራው ባህሪ የለንም ወይ? እነዚህ የምንጋራቸውን ነገሮች ማበልጸግ ለምን አቃተን? ለምንስ የአንዳችንን ህመም እና ስቃይ ሌሎቻችን አብረን መታመም እንኳን ባንችል መረዳት አቃተን? ለበደሎች እውቅና መስጠት እና ከተበዳዮች ጎን መቆም ለምን ተሳነን? የበደልናቸውን ይቅር የምንልበት ድፍረት ለምን አጣን? የበደሉንንስ ይቅር የምንልበት ጽኑ ልብ ማግኘት ለምን ቸገረን? ከበዳይ ተበዳይ የታሪክ አዙሪት ለመውጣትስ የምንችልበት መላ መቀየስ ለምን አቃተን?
በዚህ ሰሞን እንኳን ያለውን የአገራችንን የፖለቲካ አየር ብንቃኝ ሦስት ነገሮች እናስተውላለን፤
+ የጸብ አታሞ፤ 
አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጠር ሁሉም ከያለበት ሆኖ የጸብ አታሞውን ይደልቃል። መንግስት ይፎክራል፣ ባለሥልጣናት ይፎክራሉ፣ ጋዜጠኞች ይፎክራሉ፣ የመብት ተሟጋቾች ይፎክራሉ (እራሴን ጨምሬ ነው)፣ የኃይማኖት አባቶች ይፎክራሉ፣ ጦማሪዎች ይፎክራሉ፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እና አባሎቻቸው ይፎክራሉ፣ ተማሪው እና ወጣቱ ይፎክራል፣ ደራሲው፣ ከያኒው፣ ሙዚቀኛው፣ አዝማሪው፣ ምሁሩ ሳይቀር ሁሉም ይፎክራል፣ ያቅራራል፣ የጸብ አታሞውን እየደለቀ ና ይዋጣልን ይላል። ኸረ ምን ሆነናል።
+ ግብዝነት፤ 
እንደኛ በአለም ግብዝ ፍጥረት ያለ አይመስለኝም። እጅግ ሲበዛ ግብዞች ነን። በእዝጌር ሳይሆን በብሔር ወይም ከኋላችን ባሰለፍነው መንጋ ወይም ዙሪያችንን ሆይ ሆይ በሚለን አጃቢዎች የምንታበይ፤ በሕግ የበላይነት ሳይሆን በአቅማችን ባፈረጠምናት ጡንቻ የምንተማመን፤ በፍቅር ሳይሆን በጸብ ነገሮቻችንን ሁሉ የምናጸና፤ በውይይት ሳይሆን በዛቻ እና በጩኸት ብዛት መደመጥን የምንሻ ግብዞች ነን። እንረሳዋለን እንዲሁ በወጀብ፣ በጡንቻ፣ በገንዘብ እና በጩኸት ተፈርተው የኖሩ እቡዮች አናታችን ላይ እንደወጡ እዛው የሚቀሩ የሚመስሉ እንደ ሰው ተሸንፈው እና አፈር ለብሰው ዛሬ ከምንረግጠው መሬት ስር መሆናቸውን።
+ ከእኔ በላይ፤
በእኔ በሽታ ተለክፈናል። እኔ የተናገርኩት፣ እኔ ያሰብኩት፣ እኔ ያልወጠወጥኩት፣ እኔ ያልባረኩት፣ እኔ ያልቀደስኩበት፣ እኔ ያልመራሁት፣ እኔ ያላቦካሁት፣ እኔ ያልደገፍኩት፣ እኔ ያላጸደኩት ነገር ሁሉ ፉርሽ ነው ብለን የምናምን ቅርብ አዳሪዎች። በእኔ ክቦች የታጠርን፤ የእኔ ኃይማኖት፣ የእኔ ብሔር፣ የእኔ ከተማ፣ የእኔ መንደር፣ የእኔ ባንዲራ፣ የእኔ ሃሳብ እያልን ከፊል አቃፊ ብዙ አግላይ በሆኑ አጥሮች የተከበብን የራስ ምርኮኞች።
ከእኔ በላይ እና ግብዝነት እጅግ ተንሰራፍቶ ማህበራዊ ቀውስ በፈጠረበት ማህበረሰብ ውስጥ ትንኮሳ እና የጸብ አታሞ ሲደለቅበት ነገራችን ሁሉ የንቧይ ካብ፤ የንቧይ ካብ ይሆናል።
እስቲ ከራሳችን ጋር እንሟገት፤ ከራሳችን ጋር እንጣላ፤ ለአንዳፍታ ትንፋሽ ሳብ አድርገን እራሳችንን እንጠይቅ። ምን እያደረኩ ነው? ምን እየተናገርኩ ነው? ምን እያሰብኩ ነው? ምን ውጤት ለማምጣትስ ነው ያሰብኩትን የተናገርኩት፣ የተናገርኩትን ያደረኩት ብለን እራሳችንን እንሞግት።
እራሱን ከዚህ ሁሉ ንጹ ሆኖ ያገኘ ሰው ካለ እሱ እድለኛ ነው። በማህበረሰባችን ውስጥ የተረጨው ፋይረስ ቆዳውን ሰርስሮ ደሙ ውስጥ አልሰረጸም ማለት ነው። ዝም አይነቅዝም ብሎ የተቀመጠውም ሰው በዝምታው ውስጥ እነዚህ ክፉ የእሳቤ ልክፍቶች አለመኖራቸውን ይፈትሽ። እንደ አገር ለመቀጠለ እነዚህን የሃሳብ ደዌዎች ማከም ሳያስፈልገን አይቀርም።
ድንፋታ፣ ፉከራ፣ ግብዝነት፣ እኔ ብቻ ባይነት፣ ጩኸት፣ ዛቻ እና መጠለሻሸቱ እንደ ሱናሜ ጎርፍ ጠራርጎ ሳይወስደን በፊት እራሳችንን እናክም።
ከራሴ ጋር ሙግቴን ቀጥያለሁ፤
Filed in: Amharic