>

ሽመልስ አብዲሳ፤ በቃሉ እንዲጸና እንጂ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልሻም። (ሃራ አብዲ)

ሽመልስ አብዲሳ፤ በቃሉ እንዲጸና እንጂ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልሻም።

አለባብሰን እያረስን፤ በአረም ተወረስን፤

 

ሃራ አብዲ

 

በሳምንትም ፤ በወርም መለስ ቀለስ የሚለው የኢትዮጵያ በሽታ ሰሞኑን በከባድ ማገርሸት ጀምሮአል።
ብለነዉ ብለነዉ የተዉነዉን ነገር፤
ባልዋ ትናንት ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር። እንዳለዉ ተወዳጁ ኤርምያስ ለገሰ (የመለስ ልቃቂት) ብዙዎች ብለዉት ብለዉት ያልሰማነዉን ነገር አሁን እንደ መብረቅ ሲያንጎደጉድ ጥቂቶች ለመስማት ተገደናል። ከሽመልስ ንግግር ጀርባ ብዙ ዝክንትል ስላለ፤ ይህ ጽሁፍ የሚጠራርበዉ እርሱን ብቻ አይደለም ። ከጃዋር መሀመድ ይጀምራል። ለመሆኑ፤ ጃዋር መሀመድ፤ እንዴት ሃይ የሚለዉ አጣ? የኦሮሞ አክቲቪስት ነን ባዮችና «ነጻይቱን ኦሮምያን» እንመሰርታለን የሚሉ ፓርቲዎች አልጋ ላይ ሲባሉ አመድ ላይ የሚንደባለሉት፤ ምን እስከሚያደርጉ ነዉ የሚጠበቀዉ? አሁን ሽመልስ አብዲሳ፤ ጥብቅና የቆመለት ታዬ ደንደአ፤ ከርሞ ማን ይሆን በወንጭፋቸዉ የሚጠለፍ? ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የለዉጥ ሃይሉን እስከ መጨረሻ አምኖ መከተል የሚቻለዉ ምን ሲሆን ነው?

ጥያቄ፤ ጥያቄ፤ መልስ አልቦ ጥያቄ!!

በስልጣን ዘመንዋ ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ቁም ስቅል ስታበላ ኖራ፤ አሁንም በህዝባችን መሀል መለያየትና ጥላቻን እስፖንሰር የምታደርገዉ ወያኔ ፤ ያለአንዳች ከልካይ ከጫፍ እስከጫፍ እሳት በመለኮስና ለዉጡን እንጦሮጦስ ለማዉረድ በመትጋት ላይ ትገኛለች። በሌላ ጉኑ፤ ወያኔንንም የሚጠየፉ የአሁኑን አስተዳደርም የጎሪጥ የሚያዩ፤ ምንም ይሁን ምን በሀገራችን የመጣዉ ለዉጥ የማይጥማቸዉ አሉ። ከዚህ የተነሳ፤ በረባዉ ባልረባዉ የነገር ድሀ ማሳደጉን ስራችን ብለዉ ተያይዘዉታል። ጥቂት የማይባሉ፤ የሀገራችንን ፖለቲካ የእጃቸዉ መዳፍ ያህል የሚያዉቁት ደግሞ የለዉጥ ሀይል የሚባለዉን ማመን እንደማይቻል ማስረጃ እየጠቀሱ ሲሞግቱ ሰንብተዋል።

ከሁሉም የባሱት፤ የወያኔን ጫማ ለመሙላት በኦሮሞ ልጆች መቃብር ላይ ቆመዉ ከወያኔ የእጅ እባሽና የፖለቲካ ቃሪያ የሚቃርሙት ረብ- የለሽ፤ የኦሮሞ አክቲቪስት ነን ባዮች አሉ።ወደ ዝርዝሩ መግባት ባያስፈልገኝም በዚያኛዉ ጥግ የምንገኝ ደግሞ፤ « እረ እስቲ ነገር አብርዱ፤ ሀገር ይረጋጋ ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሰድበን ለሰዳቢ አንስጥ፤ ወያኔን ደስ ይበላት ብለን ካልሆነ በቀር፤ አሁን አብይን ማብጠልጠል ለማን ይጠቅማል? » ስንል ከርመናል። የሀገራችን አንድነትና የህዝባችን ሰላም ወደለየለት መቀመቅ እንዳይወርድ በመስጋት። ወዲሁም፤ ፈረሱ፤ ተበተኑ የሚባሉት እንደነ ሶማሊያ ያሉትም ሀገሮች እኮ እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሞአቸዉ እንጂ፤ በአንድ ጀምበር ፈርሰዉ አላደሩም፤ በማለት ።

የጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፤ የሽመልስ ንግግር ሲያስደነገጠኝ፤ የታየ ደንደአ አሳቀኝ ( አይ ታዬ! ለካ ያለነገር የመጀመሪያ ድግሪ ለመስራት አስራ ስድስት አመት አልወሰደበትም ፤፤)) «ይለይልን »ይበል? አበበ ቢቂላ ፤ በባዶ እግሩ ማራቶን ሮጦ የክብርዋን ችቦ ለአለም ያበራላት ፤ በአሉ ግርማ ነፍሱን የሰጠላት ኢትዮጵያ፤ እፍኝ በማይሞሉ መደዴ፤ ሽርክት ፖለቲከኞች አትዋረድም። መላዉ የኦሮሞ ህዝብ ከጥንትም ዘብ እንደ ቆመላት ለወደፊትም ይቆምላታል።እንግዲህ፤ አንደ ሸረሪት አግድም መሄዱን ትቼ፤ ወደ ነገሩ ልብ ልግባ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የኦሮምያ ርእሰ- መስተዳድር ምክትል ፕሬዚዳንት በኢሬቻ በአል ላይ የተናገረዉ ንግግር በእጅጉ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በሁለት ምክንያት።
አንደኛ፤ አቶ ሽመልስ፤በኩሩ ኢትዮጵያዊነቱ፤ በችሎታዉና በምስጉንነቱ ብዙ ተመስክሮለት የነበረ ሰዉ በመሆኑ፤ እንዲህ ከዘጠነኛ ፎቅ ላይ ራሱን በድንገት ይወረዉራል ብሎ የጠበቀ ያለ ስለማይመስለኝ፤ሁለተኛ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠራራ ጸሃይ ፋኖስ አብርቶ ፈልጎ ያገኘዉና አጠገቡ አስቀምጦ ሜንተር የሚያደርገዉ ባለስልጣን፤ ያንን አይነት ንግግር ሲናገር፤ ማንን ተማምኖ ነዉ? በሚል።

ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ አጅሬዉ ሽመልስ ያበጠዉ ይፈንዳ ብሎ «የሰበሩንን ሰብረናል» ሲል፤ አንዴ ከፈሰሰ የማይታፈሰዉን ነዉረኛ ነገር አፉን ሞልቶ፣ በቁመቱ ሙሉ ለቅቆታል። ያሳዝናል።

ምነዉ፤ ደጉ፤ አስተዋዩና ገራገሩ ኦሮሞዉ ወገኔ ፖለቲከኛ አልወጣለት አለ??

ከዚህ በታች የምለዉን ፤የምለዉ፤ ነገሩ ሁላ የግራ እየሆነ ስላስቸገረኝ የመጣዉ ይምጣ ብዬ እንጂ፤ እስከ ወዲያኛዉ በአብይ አመራር ላይ ተስፋዬ ስለተጠነፈፈ አይደለም።
እነ ዳዉድ ኢብሳና፤ ጃዋር መሀመድን መሬት አይንካችሁ፤ ንፋስ አይንፈስባችሁ፤ አንተም የፈለከዉን ፈርስ፤ ፈርስ የሚሸት የዉሸት ታሪክ እንደፈለግህ በሚዲያህ ንዛዉ፤ አንተም፤ አስሩንም፤ ሀያዉንም ባንክ ገልብጠህ አስገልብጠህ ዝረፍ፤ አዘርፍ፤ ጊዜዉ የመደመር ነዉ፤እያለ የሚንከባከብ መንግስት ሲገኝ፤ ሽመልስ ምን ያድርግ?
ይህ ሳያንስ፤ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግስት፤ ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር፤ በጋራ እንሰራለን ብሎ ሲያበቃ፤በነካ እጁ ከጃዋር ጋርም ሲፈራረም ሲያይ፤ ሽመልስ ምን ያድርግ?? ለመሆኑ፤ ጃዋር መሀመድ የሚመራዉ የኦሮሞ ፓርቲ አለዉ? ወይንስ ራሱ ፓርቲ ነኝ ብሎ ተመዝግቦአል? ሁለቱም ካልሆነ ደግሞ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከጃዋር መሀመድ ጋር በጋራ የሚሰራዉ ነገር ምንድን ነዉ?

ህዝብ በሜንጫ ካልዘነጠልኩ፤ ሀገር እንደ አመድ ካልበተንኩ ፤ብሎ የኦሮሞን ወጣት ጃስ ብሎ ከሚያሰማራ የጥፋት መልእክተኛ ጋር መፈራረም ፤ ለክፉ ስራዉ ሽፋን መስጠት አይሆንም? ወይንስ እንደሚባለዉ ፤ኦዲፒን በኦነግ የመተካቱ የመሰረት ድንጋይ ባስተማማኝ ተጥሎአል? ያ፤ ከሆነ፤ «ኦሮሞ የተሰበረዉ እዚህ ነበር፤ የሰበሩንን ሰብረናቸዋል» ብሎ በእብሪት ለመደንፋት ጊዜዉ ነዉ።

ለመሆኑ፤ ከኦሮሞ ማይግሬሽን ( ከኦሮሞ መስፋፋት ) በፊት፤ የአሁኒቱ አዲስ አበባ ያለችበት ቦታ፤ በኢትዮጵያ ካርታ ዉስጥ ነበር? ከነበረስ የየትኛዉ ማህበረሰብ አባላት ይኖሩበት ነበር? ነዉ ? ወይንስ፤ ኦሮሞ መስፋፋት የጀመረዉ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ይኖርበት ከነበረዉ ፊንፊኔ ተነስቶ ነዉ ወደ ወሎም ወደ ሀረርም የተስፋፋዉ?
እነዚህ፤የታሪክ ዉርዴዎች! ጨዋዉንና ደጉን የኦሮሞ ህዝብ አይወክሉም። የኦሮሞ ህዝብ አይንና ጆሮ የሆንነዉ፤ ከኦሮሞ ማህበረ-ሰብ የወጣን፤ የተለያየ ማህበረ-ሰብም የፍቅር ዉጤት የሆንን፤ ሁለትም–አራትም ኢትዮጵያዊ ጎሳዎች በህብረት ወልደዉ በህብረት ያሳደጉን የሽመልስ አብዲሳ ሳይሆን፤ የአብዲሳ አጋ ልጆች የሆንን እልፍ ኢትዮጵያዉያን ነን። እነዚህ፤ በከንፈራቸዉ ላይ እንደ ማር የሚፈሰዉን አማርኛ ፤ለመርዘኛ ሃሳባቸዉ አሸንዳ ያደረጉት፤ የኦሮሞን ህዝብ ያለመልኩ መልክ ፤ያለስሙ ስም በመስጠት በስሙ የስልጣን ሃራራቸዉን የሚወጡበት፤ የኦሮሞ ህዝብ ባለፈበት ያላለፉ ናቸዉ። ጊዜ ከሰጠዉ ባለስልጣን ጉርስ እየተጣለላቸዉ ፤የኦሮሞን ወጣት ሲያስጨፈጭፉ፤ የኦሮሞን ገበሬ ከመሬቱ ሲያፈናቅሉና በትርፍራፊዉ የባንክ አካዉንታቸዉን ሲያዳብሩ የኖሩ ሀፍረተ-ቢሶች፤ያ ፤ አልበቃ ብሎአቸዉ፤ ዛሬ በተራቸዉ የኦሮሞን ህዝብ በብረት ልምጭ ራሳቸዉ ሊገርፉት ተዘጋጅተዋል።የኦሮሞ ህዝብ፤ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ፤አያት ቅድመ-አያቶቹ ደማቸዉን ገብረዉ ፤ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ከመጣዉ ወራሪ ጋር ሁሉ ተዋግተዉ ነጻይቱን ኢትዮጵያ አስረክበዉታል። ፖለቲከኞቹ፤ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዝታሀለች ይሉታል። የኦሮሞዉ ደም ደማችን ነዉ፤ በቀለ ገርባ ጀግናችን ነዉ ብሎ በአደባባይ መከራ የተቀበለላቸዉን የአማራ ህዝብ አይናቸዉን በጨዉ አጥበዉ፤ «የከረመ ቂም አለን ፤ ጠላታችን ነህ» ይሉታል።

This is sickening!!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፤በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ታይቶ የማይታወቅ ቅንነትና ልበ-ሰፊነት ይዞ እንደመጣ ዛሬም ጥርጥር የለኝም። ብዙ ጊዜ በጽሁፎቼ እንዳረጋገጥኩት፤ ዛሬም ፤ወደፊትም፤ «ኢትዮጵያንና ህዝብዋን እስካለ ድረስ፤ እንደ አንድ ዜጋ ድጋፌ አይለየዉም።

እስከ አሁንም፤ ይህን ቢያደርግ መልካም ነበር—- ያንንስ ባያደርግ ጥሩ ነበር– የምለዉ ቢኖረኝም ፤ ከላይ እንዳልኩት ሰድቦ ለሰዳቢ ከመስጠት፤ በትእግስት መከታተል ይሻላል የሚል አቅዋም ወስጄ አፌን በአጠገቤ አኑሬ ከርሜአለሁ። ከእንግዲህም፤ ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ፍላጎቴ ባይሆንም፤ ሲበዛ ማርም ይመራልና፣ አብዬ ሆይ፤ ጥርት ያለዉን አካሄድህን አሳዉቀን ልለዉ እወዳለሁ።

ከጃዋር መሀመድ ጋራ በጋራ ለመስራት ያሰብከዉ ምንድን ነዉ? ጃዋር፤አዲስ አበባን ከመጠቅለል በመለስ፤ ኢትዮጵያን ያለርህራሄ ሁለት ቦታ ለመተርተር ከመትጋት በመለስ እንቅልፍ እንደሌለዉ እየታወቀ፤ የምትታገሰዉና ይባስ ብለህ አብረህ ቃል ኪዳን የምትጋባዉ ስለምን ነዉ? ታማኙ ሹመኛህ፤ ሽመልስ አብዲሳ ብቻ ነዉ ወይንስ ክቡርነትህም በጃዋር ወጥመድ ውስጥ ወድቀሀል?ይህ ሳይዉል ሳያድር ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ መደረግ አለበት። «ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲዉ በነጃዋር ተጽእኖ ስር የወደቁት፤ ጃዋር ቄሮን እንዳያስነሳበት በመፍራት ነዉ »የሚለዉ ማፈሪያ ሃሳብ ፤መጨረሻዉ ምን ይሁን?

ለዚህ ነዉ በርእሴ፤ ሽመልስ ቃሉን እንዲያጸና እንጂ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልሻም ያልኩት።አቶ ሽመልስ፤ ወላፈኑ ሲበረታበት የአፍ ወለምታ ነዉ ብሎ ሊያገለግለዉ ቃል የገባለትን ህዝብ እንዳያታልል ፤ አደራዉን!! አለባብሰን እያረስን በአረም ተወረስን!! እነሱ ወዳጄ፤ አምቦ የተናገሩትን አዲስ አበባ ላይ ማስተባበሉን፤ በኦሮምኛ ለቄሮ ያስተላለፉትን መልእክት በአማርኛ ሽምጥጥ አድርጎ መካዱን የዉሃ መንገድ አድርገዉታል። አንዴ፤ ሁለቴ መሸወድ ያለነዉ። ነጋ ጠባ ልሸዉዳችሁ ማለት አጉል ንቀትና የበዛ ንቅዘት ነዉ። ነገሩ አለቅጥ ሳይወታተብና የአብሮነታችን ንጣፍ ከዉስጠኛዉ መሰረት ሳይናጋ በፊት፤ይህን ለዉጥ እነማን እንደሚመሩት አደባባይ ይዉጣ። ዶክተር አብይ፤ እርግጥ፤ የተናገርካቸዉ ወርቃማ ቃላት የልብህ ሃሳቦች ከሆኑ ( ናቸዉ ብየም አምናለሁ) ጃዋርንም ሆነ ቄሮን አትፍራ! መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮህ ይቆማል። አንተ ብቻ ቃል ተናገር። «እያስቸገሩኝ ነዉ» በለን ድምጽህን ዘለግ አድርገህ። በነሱ ካለዉ ይልቅ፤ ባንተና በእኛ ያለዉ ይበልጣል። ኢትዮጵያዊነት!! ሽመልስ አብዲሳንም እንዴት ትገስጸው እንደሆነም ለማየት በንቃት እንጠባበቃለን።
ጄናን ጄኔ መሌ፤ ዱር ቄሲ ወጂን አላ ቡላ? ( በአማርኛ ሲተረጎም ፤እኔም አስተባብላለሁ፦)

ኢትዮጵያ የልጆችዋ ሰላምና አንድነት ተጠብቆ ለዘላለም ትኑር

Filed in: Amharic