>
5:13 pm - Thursday April 19, 8931

የጠ/ሚሩ ተግባር እንጂ  "ልብ" ምን ይሰራልናል?!? (ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ)

የጠ/ሚሩ ተግባር እንጂ  “ልብ” ምን ይሰራልናል?!?
ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ
 
“ጠ/ሚ ዓብይ አህመድ ልባቸው ጥሩ ነው አብረዋቸው ያሉ ሰዎች ናቸው አላሰሩ ያሏቸው እንጂ” የሚሉ አባባሎች ሲበዛ ያናድዳሉ። የልብ ቅንነት በተግባር ላይ ውሎ ካልታየ ምን ያደርጋል?  በመጀመሪያ አንድ ሰው አቅሙ አለኝ ብሎ ምሎና ተገዝቶ የሀገሪቱን የመጨረሻውን ሥልጣን በእጁ ካስገባ፤ በምንም መንገድ አድርጎ ሀገር አረጋግቶና ሰላም አስፍኖ መምራት መቻል አለበት። በምንም መንገድ። ያ የተመሪው ሕዝብ ጉዳይ አይደለም። ያን ማድረግ ካልቻለ ለምን የእናት ልጅ አይሆንም ኧረ እንደውም ለምን ወላጅ እናት ራሷ አትሆንም ጉዳዩ እዚያ ጋር ያበቃል። ሀገር እና ሕዝብ መለማመጃ ቤተ ሙከራ አይደሉም።
ኢትዮጵያ እጅግ ትልቅ ሀገር ነች። በዚያ ላይ ፈፅሞ ጊዜ በማይሰጡ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ችግሮች የተተበተበች። ጊዜ እንስጥ እየተባለ ደቂቃ ሊሰጥ ወደማይችል መከራ ውስጥ እየገባን መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ጠ/ሚ ዓብይ ጊዜ ይሰጠው እየተባለ፣ ጊዜን መጠቀም በሚችሉ አጥፊዎች ሀገር እየተሰቃየች ነው። እናም ጠ/ሚ ዓብይን መወጣት ባልቻሏቸው ግዴታዎቻቸው ላይ በሚቻለው ሁሉ ጫና ማሳደር ሲገባ፣ “ጊዜ እንስጠው፣ እሱ እኮ ቅን ነው፣ በተለይ ልቡ” እያሉ ወሬ ማሰማመር እና በሀገር መቀለድ ተገቢ አይደለም።
ገና ለገና በጠ/ሚሩ ፊት ሞገስ አገኝ ይሆን ያሉ ሰዎች ዐይናቸውን ጨፍነው በሀገር ችግር ላይ ሲያላግጡ ማየት ያናድዳል። ሕዝብ መካሪ አይፈልግም። ጥሩ ለሰራ ቀርቶ ጥሩ ለተናገረ እንኳ ፅንፍ የለሽ ድጋፍ መስጠት እንደሚችልበት ከዳር ዳር በተግባር አሳይቷል። ስለሆነም ሀገር ለቀለድ፣ ለስንፍና ለአቅመቢስነት ቦታ የላትም። ጠ/ሚ ዓብይ ጊዜ ይሰጠው የሚባለው አነጋገር የሚሰጠው “ጊዜ” መጨረሻው የት ድረስ ነው? ወሬ እና ማስመሰል ጠላን።
Filed in: Amharic