>

አብይ ይደምራል፤ ኦዴፓ ይቀንሳል፤ አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ! (ያሬድ ሃይለማሪያም)

 

አብይ ይደምራል፤ ኦዴፓ ይቀንሳል፤ አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ!

 

ያሬድ ሃይለማሪያም

 

ዶ/ር አብይ “መደመር” በሚል እሳቤ ከመንግስት ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆኖ የኖረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀልብ ለመሳብ እና ለውጡን ተስፋ አድርጎ በትእግስትና በጥንቃቄ እንዲከታተል ያደረጉትን ጥረት እና ድካም፤ ድርጅታቸው ኦዴፓ በአክራሪ ብሔርተኞች ተጠልፎ ይመስላል ልፋታቸውን በዜሮ እያበዛ ድምሩን ይንዳል።

  • እሳቸው አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ይላሉ ድርጅታቸው በመግለጫ መዲናዋ የኦሮሚያ የግል ሃብት ነች ይላል፤
  • እሳቸው ስለፍቅር እና እርቅ ያወራሉ፣ ይሰብካሉ፣ ይማጸናሉ፤ ድርጅታቸው የቆየ ቁስል እየጎፈደረ አሸናፊነት በሚመስል በተሸናፊነት እብሪት የትግል አጋሮቹን ጭምር በአደባባይ ይወርፋል፣ ይታበያል፣ ከሕዝብ ጋር ይላተማል፤
  • እሳቸው የሚኒሊክ ቤተመንግስትን አድሰው እና ሌሎች በመውደቅ ላይ ያሉ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ጭምር ታድገው የቱሪስት መስህብ ለመፍጠር ደፋ ቀና ይላሉ፤ ድርጅታቸው ከታሪክ እና ከባለታሪኮች ይላተማል፤
  • እሳቸው ስለ ኢትዮጵያ ብልጽግና ያወራሉ ድርጅታቸው ኦሮሞ እገሌን ሰበረ፣ ያንን ተቆጣጠረ፣ ብቻውን ታግሎ ነጻ ወጣ እያለ በተረኝነት ትርክት ተውጣል።
  • እሳቸው ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተቀራርበው ለመስራት እና ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድን በማደስ ጥረት ያደርጋሉ ድርጅታቸው እና ሹማምንቱ እኛ ክልል እነገሌ ፓርቲዎች ድርሽ እንዳይሉ ብለው ባደባባይ ያውጃሉ።

ዶ/ር አብይ የመደመርን ጽንሰ ሃሳብ በራሳቸው ድርጅት ውስጥ በቅጡ ሳያሰርጹ፣ ጓደኞቻቸውን በሃሳቡ ሳያሳምኑ፣ በሚመሩት ክልል ውስጥ ያሉ ልሂቃንን ሳያጠምቁ እና ቀልብ ሳይገዙ ሃሳቡን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስረጽ በመምጣታቸው እሳቸውም ሆነ ሃሳቡ አቅመ ደካማ እንዲሆኑ አድርጓcእዋል። ‘አለባብሰው ቢያራሱ በአረም ይመለሱ’ እንደሚባለው ችላ ብለው የተውት ድርጅታቸው የሳቸውንም ሆነ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ስህተቶችን በተደጋጋሚ ሲፈጽም እየተስተዋለ ነው።

የኦዴፓ አካሄድ ገና በጊዜ ያሳሰበን ሰዎች ድርጅቱ ኢትዮጵያን የመምራት ታሪካዊ እድል በእጁ ቢገባም የህውሃትን ስህተት ላለመድገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካላደረገ አገሪቱን ችግር ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ደጋግመን አሳስበናል። የዛሬ ስድስት ወር ግድም በሚያዝያ ወር በጻፍኩት አጭር ዳሰሳ “ኦዴፓ፤ ህውሃት የሄደበትን ቁልቁለት ባይጀምረው መልካም ነው!” በሚል ርዕስ ስጋቶቼን ገልጬ ነበር። የጽሁፉን ሙሉ ቃል ከዚህ ማስፈንጠሪያ ያገኙታል።

ዛሬ ኦዴፓ በአክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች መዳፍ የገባ ይመስላል። የክልሉ ሹማምንት በተደጋጋሚ በየመድረኩ የሚሰነዝሯቸው ብስለት የጎደላቸው የደመ ነፍትስ ንግግሮች ከአጋር ድርጅቶቻቸው ጭምር እያላተማቸው ነው። ከዛም አልፎ ብሽሽቅ በሚመስል መልኩ በየማህበራዊ ድረገጹ ሹማምንቱ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች እና ብሽሽቆች የአገሪቱ ፖለቲካ ምራቃቸውን ባልዋጡ ጎረምሶች እጅ መውደቁን ያሳያል።

የኦዴፓን እና የዶ/ር አብይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከቀረው ማህበረሰብ ሦስት ምልከታዎች እየተንጸባረቁ ነው

  • ፩ኛ/ የመጀመሪያው ዶ/ር አብይ መደመር በሚል ሽፋን የኢትዮጵያን ሕዝብ እያጃጃለ ለኦሮሞ የበላይነት ለሚታገሉት አክራሪ ብሔረተኞች ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል የሚል ነው። የዚህ እሳቤ መነሻው ዶ/ር አብይ እና አክራሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔረተኞች እየተናበቡ እና እቅድ አውጥተው በጋራ ነው የሚሰሩት ከሚል ግምት ይመነጫል። ለዚህ እሳቤያቸውም በየቀኑ እዚም እዛም የሚስተዋሉ ጥቃቅን ግድፈቶችን በመሰብሰብ እነሱ የሚፈልጉንት ሥዕል እንዲያሳይ ይጥራሉ። በተለይም በአደባባይ መወያያ የሆነውን የተረኝነት ነገር በማንሳት እና አንዳንድ መገለጫዎችን በማጣቀስ ይህ ሁሉ ሲሆን የአብይ ዝምታ ቀድሞም መስማማቱን ነው የሚያሳየው በሚል የእቅዱ አካል ነው ብለው ሙግት ያነሳሉ። በግልጽ የሚስተዋሉ መድሎዎች፣ በአዲስ አባባ ነዋሪ እና በከተማዋ ላይ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች፣ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ የመጠቃቀም ተግባራት፣ የማናለብኝነት ስሜት እና የአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከሕግ በላይ መስሎ መታየት ተደጋግመው ይህን ሃሳብ ለመደገፍ እንደ ምክንያት ይነሳሉ።
  • ፪ኛ/ ሁለተኛው ምልከታ አብይ ቅን አሳቢ እና የመደመር እሳቤውም ከልብ የመነጨ ሰው ነው። ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግ እና አገሪቱን በአንድነት ወደ ብልጽግና ለመውሰድ ትልቅ ህልም አለው። በብሄረተኝነት ቅዠት የተጠለፈ ሰው አይደለም። ትልቅ ህልም እና እራይ ያለው ሰው ነው። ይሁን እና የሥልጣኑ መሰረት የመጣበት ድርጅት እና ክልል ስለሆነ ከእነሱ ጋር ከተጣላ አንድ ሐሙስ እንኳ በሥልጣን ላይ መቆየት አይችሉም። የአብይ ስልጣን ህልውና ያለው በኦዴፓ እጅ ነው። አክራሪዎቹም አብይን ለመቆጣጠር ወይም ጸጥ ለማሰኘት ኦዴፓን መቆጣጠር እንደ እስትራቴጂ ነድፈው ስለተንቀሳቀሱ ተሳክቶላቸዋል። ባይቆጣጠሩትም ያሻቸውን ሲያደርጉ ዝም እንዲል አድርገውታል የሚል ነው። ይህ እሳቤም አብይ በየጊዜው በሚናገራቸው ነገሮች ውስጥ ወጥነት (consistency) መኖር እና እየተገበረ ያላቸውን አንዳንድ በጎ ሥራዎች በዋቢነት ያጣቅሳሉ።
  • ፫ኛ/ ሦስተኛው ምልከታ አብይ ጥሩ አሳቢ እና ትልቅ እራይ ያለው ሰው መሆኑን አምነው ነገር ግን የፖለቲካ አመራር ሰጪነቱ እና ብስለቱ እጅግ ደካማ ነው። የአገሪቱን የፖለቲካ ውስብስብ ባህሪ በደንብ የተረዱ፣ የማህበረሰቡን ስነ ልቦና በቅጡ ያጠኑ፣ ከስሜት የራቁ እና አደጋዎችን አርቀው አይተው ለመከላከል የመፍትሔ ሃሳብ የሚያመነጩ በሳል አማካሪዎች የሉትም። ባለፉት ሁለት አመታት ከተከሰቱት ችግሮች መካከል አብዛኛዎቹ በሳል እና ጠንካራ የፖለቲካ አመራር ቢኖር ቀድመው ሊመለሱ የሚችሉ ነበሩ። አብዛኛዎቹ ችግሮች ቀድመው የተተነበዩ ቢሆንም በመንግስት በኩል የቅድመ ዝግጅት እና መከላከል ሥራዎች ሳይሰሩ ስለቀሩ አገሪቱን በሰው ሕይወት እና በንብረት ዋጋ አስከፍሏታል። የአገሪቱን ወቅታዊ ችግር እና ሁኔታ የሚመጥን የፖለቲካ አመራር ለመስጠትም ሆነ የገጠሟትን መልካም እድሎች በሰዓቱ ተጠቅሞ ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል የፖለቲካ ብቃት በአመራሩ ላይ አይታይም። ከዛ ይልቅ ድርጅታቸው በገጽታ ግንባታ እና ነገሮችን በማድበስበስ ያሳለፈው ጊዜ የአመራሩን ብቃት ማነስ ያሳያል ይላሉ።

ምናልባት ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ እኔ እምነት ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች ውስጥ ችግሩ ያለው በሁለተኛው እና በሦስተኛው አስተሳሰብ ዙሪያ ይመስለኛል። በአንደኛነት የተቀመጠውን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የምጋራው አይደለም። እኔን የሚያሳምን ምክንያት እስከ አሁን አላገኘሁበትም። ከብዙ ሰዎች ጋርም ተሟግቼበታለሁ። እርሶስ ምን ይላሉ?

ለማንኛውም ይህ አገራችን የተጋረጠችውን ፈተና ለማለፍ በእኔ በኩል መፍትሔ የሚመስሉኝን ነገሮች ልጠቁም እና ሃሳቤን ልቋጭ።

  • ዶ/ር አብይ ያሉባቸው ድርጅታዊ ጫናዎች እንዳለ ሆነው በቅን ልቦና ይህን ለውጥ ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ለመምራት እና አገሪቱንም ወደተሻለ አቅጣጫ ለማሻገር ከፈለጉ በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበላቸውን የአገራዊ መግባቢያ መድረግ አዘጋጅተው የባለድርሻዎች ምክክር ጉባኤ ቢፈጥሩ ጥሩ ነው። ለውጡን ለመቀልበስ ሌት ተቀን የሚጥሩትን ኃይሎች ብቻቸውን ተጋፍጠው ይወጡታል የሚል እምነት የለኝም። ለውጡን የሚያግዛቸው ብሔራዊ ንቅናቄ ሳይዘገይ ቢፈጥሩ የማሻገር ህልማቸው እውን ይሆናል።
  • በመንግስታዊ አስተዳደራቸው ውስጥ ለሕግ የበላይነት ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ሰፊ ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል። የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ የምርጫ ነገር ህልም ይሆናል። ለውጡም ነውጥ ይወልዳል። አገርም አደጋውስጥ ትወድቃለች።
  • በድርጅት ደረጃ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች እንደገና በጠረምጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ በየአደባባዩ የሚያደርጉትን መወነጃጀል አቁመው በጋራ ለውጡን ወደፊት እንዴት በጥንቃቄ መምራት እንዳለባቸው መነጋገር እና አንድ አይነት የስምምነት ሃሳብ ይዘው መውጣት አለባቸው። እንደ ኦዴፓ እና አዴፓ ካድሬ ሹማምንት የሚዘላብዱ ባለስልጣኖቻቸውም ላይ የሥነ ሥርዓት እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
  • በብሔረሰቦች እኩልነት እና አንድነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እንድትኖር እና ኢትዮጵያዊነትን፣ ቅርሷን፣ ታሪኳን እና መገለጫዎቿን ከማናቸውም ጥቃት እና ከፕሮፓጋንዳ ዘመጃ የሚታደግ አንድ ሰፊ የሲቪክ ንቅናቄ ያስፈልጋል። ያለ ምንም ልዩነት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያቅፍ እና ለዚህ አቃፊ ማንነት የሚቆረቆር ንቅናቄ በመፍጠር አክራሪ ቤሔረተኞች በኢትዮጵያ ላይ እና ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰነዝሩትን ማንኛውንም ጥቃት በተደራጀ መልኩ መመከት ይቻlአል።

          ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic